በአፍሪካ ኅብረት አመቻችነት የሚደረገው የመንግስትና የሕወሃት የሰላም ንግግር ለመጭው ሰኞ ጥቅምት 14 ቀን 2015 ዓ.ም መጠራቱን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደህንነት አማካሪ ሚንስትር ሬድዋን ሁሴን (አምባሳደር) በይፋዊ ማህበራዊ ትስስር ገፃቸው አስታውቀዋል፡፡
በቀረበው የሰላም ውይይት ላይ መንግስት ለመሳተፍ ቁርጠኛ መሆኑን ያረጋገጡት ሚንስትሩ፣ ሆኖም አንዳንዶች መንግስት በሚወስደው “ራስን የመከላከል እርምጃ” ላይ ሃሰተኛ ውንጀላዎችን በማሰራጨት የተጀመረውን የሰላም ውይይት ለማደናቀፍ እየጣሩ መሆኑን በመግለፅ ወቅሰዋል፡፡
የሰላም ንግግሩ ለመጪው ሰኞ የተቀጠረው ከዚህ ቀደም የአፍሪካ ህብረት ከሁለት ሳምንት በፊት ንግግሩን ለማስጀመር ያስተላለፈው ቀጠሮ ከተሰረዘ በኋላ ነው፡፡
ህብረቱ የመጀመሪያውን ጥሪ አስመልክቶ በላከው ደብዳቤ፣ ንግግሩ የሚመቻቸው በአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆና ሌሎች ስመጥር አፍሪካውያን መሆኑን አስታውቆ ነበር፡፡
ከኦሉሴጉን ኦባሳንጆ በተጨማሪ ንግግሩን እንደሚያመቻቹ የተገለፁት የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታና የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ምክትል ፕሬዝዳንትና በአሁኑ ወቅት የሕብረቱ የሰላምና ደህንነት ምክር ቤት አማካሪ (ፓነል ኦፍ ዘ ዋይዝ) አባል የሆኑት ፉምዙሌ መላምቦ ንጉካ ናቸው፡፡