- እሺ ተቃውሞ ሰማሁ ነው ያልከኝ?
- አዎ ክቡር ሚኒስትር። እንዳይገቡ ከተከለከሉት ምርቶች በተወሰኑት ላይ ተቃውሞ ሰምቻለሁ።
- በየትኞቹ ምርቶች ላይ?
- በተለይ አርቴፊሻል ፀጉር በመከልከሉ በርካታ ተቃውሞና ትችት በማኅበራዊ ድረገጾች ሲዘዋወር ነበር።
- የኡጋንዳዋ ምክትል ፕሬዚዳንት የተናገሩትን ሰምተው ቢሆን ይቃወሙም ነበር።
- የኡጋንዳ ምክትል ፕሬዚዳንት?
- አዎ። ሰሞኑን በባህርዳር በተካሄደው የጣና ፎረም ላይ ንግግር አድርገው ነበር።
- አዎ። እርስዎም እዚያ ነበሩ። እና ሴትየዋ ምን አሉ?
- የኡጋንዳ ወጣት ሴቶች በፀጉራቸው ማጠር ደስተኛ አለመሆናቸውን በቀልድ መልክ ይናገራሉ አሉ።
- ምን ብለው ይናገራሉ አሉ?
- ማነው ከአቢሲኒያ ያመጣን! ወደ ኡጋንዳ ባያመጡን ኖሮ እንደ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ፀጉራችን ያምር ነበር እንደሚሉ ተናግረው ነበር።
- [ሳቅ] የሚገርመው ግን አርቴፊሻል ፀጉር እንዳይገባ መከልከሉን የተቃወሙት ሴቶቻችን አይደሉም ክቡር ሚኒስትር።
- እንዴ! እና ማነው የተቃወመው?
- ሸኔ፡፡
- [እየሳቁ] አንተ ደግሞ ቀልድና ቁምነገርህ አይለይም።
- ምን ላድርግ ብለው ነው ክቡር ሚኒስትር።
- ልክ ነህ እንደዚህ ቁምነገር ያዘሉ ቀልዶች ያዝናናሉ።
- ልክ ነው ክቡር ሚኒስትር።
- ሌላ የሰማኸው ተቃውሞ ነገር የለም?
- ልሂቃኑን ጨምሮ አብዛኛው የማኅበረሰብ ክፍል ውሳኔያችንን በከፍተኛ ደረጃ ነው የደገፈው። ግን ደግሞ…
- ግን ምን?
- ያው ተቃውሞ ጨርሶ አይጠፋም። በተለይ ተቃውሞው ከራሳችን መዋቅር መመንጨቱ በጣም ያበሳጫ።
- ከራሳችን ስትል? ከሕዝብ ክንፍ ነው?
- አይደለም። በየደረጃው ከሚገኙ የፓርቲና የመንግሥት መዋቅሮቻችን ማለቴ ነው።
- አትለኝም?
- እውነቴን ነው ክቡር ሚኒስትር።
- እንዴት?
- በተለይ ውስኪ እንዳይገባ መከልከል የለበትም የሚሉት መብዛታቸው አስገራሚ ነው።
- ይህ አስገራሚ አይደለም!
- እ…
- አሳፋሪ ነው!
- አዎ፣ ያበሳጫል ክቡር ሚኒስትር።
- ግን ውስኪ እንዳይገባ በመከልከሉ ብቻ ሲሉ ነው የተቃወሙት?
- ውስኪ ይበሉ እንጂ ምክንያታቸው እሱ እንዳልሆነ ይታወቃል።
- ምንድነው ምክንያታቸው?
- ጊዜ ነው
- የምን ጊዜ?
- በእኛ ጊዜ እንዴት ይከለከላል ነው የሚሉት ክቡር ሚኒስትር
- እነዚህን ነው በጊዜ ማለት!
- በጊዜ ማለት ሲሉ?
- በጊዜ መሸኘት!
[የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ መንግሥት የሰሜኑ ጦርነትን በተመለከተ መረጃ መስጠት ከጀመረ እኔም አንዳንድ ጉዳዮችን ልረዳ ብሎ በጠዋት ክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ ገብቶ እየጠየቀ ነው]
- እንደምን አደሩ ክቡር ሚኒስትር?
- ሰላም።
- እንኳን ደስ አልዎት።
- ለምኑ?
- የሰሜኑ ጉዳይ ወደ መደምደሚያው እየተጠጋ ይመስላል።
- በዚህ ጉዳይ ላይ አትጠይቀኝ አላልኩህም?
- መንግሥት ዝምታውን ሰብሯል ብዬ ነው ክቡር ሚኒስትር?
- መንግሥት የተናገረው ነገር አለ እንዴ?
- አዎ። ትላንት መግለጫ አውጥቶ ሦስት ከተሞችን መቆጣጠሩን ይፋ አድርጓል። ከዚያ በፊትም የአየር ማረፊያዎችን እንደሚቆጣጠር ገልጿል።
- ለነገሩ ከዚህ በኋላ ዝም ማለት ጠቀሜታ የለውም።
- አዎ፣ ትክክል ነው። የውጭ አጋሮቻቸው ዝምታውን ተጠቅመው ጫና ለመፍጠር እየሞከሩ ነው።
- እኮ። እዚህ ደረጃ ሲደርስ መናገር ተገቢ ነው። ለዚያም ነው መንግሥት የተናገረው።
- ቢሆንም ያልገባኝ ነገር አለ ክቡር ሚኒስትር?
- ምንድነው?
- መንግሥት በይፋ አየር ማረፊያዎችን እቆጣጠራለሁ ማለቱ ትክልል ነው? የውጭ አጋሮቻቸውን አያስቆጣም?
- ለምን ያስቆጣል? አየር ማረፊያዎቹ እኮ የፌዴራል መንግሥት ንብረቶች ናቸው።
- እሱስ ልክ ነው።
- በተጨማሪም የውጭ ኃይሎች አየር ማረፊያዎቹን ሊጠቀሙ እንደሚችሉ በምዕራባዊያኑ ጭምር የተረጋገጠ ተጨባጭ ማስረጃ በመኖሩ ነው።
- በራሳቸው የተረጋገጠ መረጃ አለ?
- አዎ። ራሳቸው ያረጋገጡትና በይፋም የተናገሩት ነው።
- እንደው ግን ክቡር ሚኒስትር መንግሥት ከአየር ማረፊያዎቹ ውጪ ወደ ዋና ከተማዋ አይገባም?
- በዋና ከተማ አየር ማረፊያ የለም እንዴ?
- አለ?
- ስለዚህ ይገባል። በዚያ ላይ አየር ማረፊያዎችን ብቻ አይደለም መንግሥት ለመቆጣጠር የወሰነው።
- ሌላ ምን አለ?
- የፌዴራል መንግሥት መሠረተ ልማቶችንም ይቆጣጠራል።
- የትኞቹን ማለት ነው?
- ለምሳሌ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን፣ የኃይል ማመንጫና ማከፋፈያ ጣቢያዎችን፣ አገር አቋራጭ የትራንስፖርት መንገዶችን ይቆጣጠራል።
- ዩኒቨርሲቲዎችም አሉ።
- እዎ። የመከላከያ ሠራዊቱ ይጠቀምባቸው የነበሩ የማዘዣ ማዕከላትንም ይቆጣጠራል።
- አሁን የገለጿቸው በሙሉ እኮ በዋና ከተማዋ ይገኛሉ።
- ስለዚህ ይቆጣጠራቸዋል።
- እነዚህን ሁሉ ተቋማት ከሚቆጣጠር ሌላ ነገር ቢያደርግ አይሻለውም?
- ምን?
- ከተማዋን መቆጣጠር!