ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ከ151 ሺሕ በላይ አባላት ላሉት የአማራ ክልል ነጋዴ ሴቶች ማኅበር ከፋይናንስ አቅርቦት ጋር በተያያዘ በጋራ ለመሥራት የሚያስችለውን የስትራቴጂክ አጋርነት የስምምነት ተፈራረመ፡፡
በባሕር ዳር ከተማ ሰሞኑን ስምምነቱ በተፈረመበት ወቅት እንደተገለጸው፣ ከማኅበሩ ጋር እንዲህ ያለውን ስምምነት ያደረገው የማኅበሩ አባላት ንግዳቸውን ለማካሄድና ለማስፋፋት ትልቅ እንቅፋት የሆነባቸውን የፋይናንስ አቅርቦት ለመቅረፍ ነው፡፡
የፋይናንስ አቅርቦቱ ብቻ ሳይሆን ለንግድ እንቅስቃሴዎች የሚፈልጉትን ገንዘብ ከባንክ ለማግኘት ማስያዣና የብድር ወለድ ምጣኔ ከፍተኛ ማነቆ እንደሆነባቸው በጥናት ላይ የተመሠረተ መረጃ ከማኅበሩ በማቅረቡ፣ በዚሁ መነሻነት ማኅበሩን ለማገዝ እንደሆነ ባንኩ አስታውቋል፡፡ ማኅበሩ ባደረገው ጥናት መሠረትም 82.2 በመቶ የሚሆኑት አባላት ለንግድ እንቅስቃሴያቸው የሚሆን ብድር ማግኘት አለመቻላቸውን የሚያመለክት እንደሆነም ባንኩ ገልጿል፡፡ በመሆኑም ንብ ባንክ በአነስተኛ ወለድና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ማስያዣን በተመለከተ ባለው ሕግ መሠረት ፋይናንስ ለማቅረብ ለአምስት ዓመታት የሚቆይ የስትራቴጂካዊ አጋርነት ስምምነት ከማኅበሩ ጋር ሊፈርም መቻሉን ጠቅሷል፡፡
ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በአማራ ክልል ተደራሽ ለመሆን እየሠራ ሲሆን፣ ይህንንም ዕውን ለማድረግ እንዲቻል ባሕር ዳር ከተማ የዲስትሪክት ቢሮና በርካታ ቅርንጫፎች በክልሉ ከፍቶ በመሥራት ላይ ይገኛልም ተብሏል፡፡
ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች የተሟላ የባንክ አገልግሎት በመስጠት ለዜጎች ተስፋ መሆን ከመቻሉም በተጨማሪ፣ ለበርካታ ኢትዮጵያውያን የሥራ ዕድል በመፍጠር ዜጎችን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን የሚገልጸው የባንኩ መረጃ፣ የአማራ ክልል ነጋዴ ሴቶች ማኅበር ጋርም በዚህ የባንኩ ዓላማ አንፃር አብሮ ለመሥራት ተስማምቷል ተብሏል፡፡ አዋጭ በሆኑ ቢዝነሶች ሁሉ ባንኩ ለማኅበሩ አባላት በሙሉ ለሚሰጠው ብድር አነስተኛ የሚባለውን የድብር ወለድ ምጣኔ በመወሰን ብድሩን እንደሚያቀርብም ባንኩ ገልጿል፡፡
የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ አቅም ለማጎልበትና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸውን ለማረጋገጥ የተመሠረተው የአማራ ነጋዴ ሴቶች ማኅበር ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ትቅደም ወርቁ፣ የማኅበሩ አባላት ሥራቸውን እንዳይሠሩ እንቅፋት ሆኖ የቆየውን የብድር አቅርቦት ለማቅረብ ከንብ ባንክ ጋር የተደረገው ስምምነት ተስፋ ሰጪ ነው ብለዋል፡፡
አባሎቻቸው የፋይናንስ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማኅበሩ ለተለያዩ ባንኮች ጥያቄ አቅርቦ ሦስት ባንኮች አዎንታዊ ምላሽ እንደሰጡትና የጀመረው ስምምነትም ከንብ ባነክ ጋር መደረጉ ተገልጿል፡፡
የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ስትራቴጂና ትራንስፎርሜሽን ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ልዑል ሰገድ ንጉሤና የአማራ ክልል ነጋዴ ሴቶች ማኅበር ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ትቅደም ወርቁ ስምምነቱን መፈረማቸውን ከባንኩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
የአማራ ክልል ነጋዴ ሴቶች ማኅበር በ1980 ዓ.ም. የተቋቋመ ሲሆን በአሁኑ ወቅት 151,106 ንቁ አባላት፣ 32 የገንዘብና ቁጠባ ማኅበራት፣ በ102 ከተሞች ቅርንጫፎች እንዲሁም ከ106 አገር በቀልና ዓለም አቀፍ የልማት አጋር ድርጅቶች ጋር በመሥራት ላይ እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡
በተጨማሪም ማኅበሩ በጎንደር፣ በባሕር ዳር፣ በደብረ ማርቆስና በደሴ ከተሞች መሥሪያ ቤቶች ያሉት ሲሆን 151,106 ንቁ አባላት ያሉት መሆኑ ተገልጿል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 51 በመቶ ሴቶች መሆናቸው ከማኅበሩ የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡
ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ በአሁኑ ወቅት ከአራት መቶ በላይ ቅርንጫፎች፣ ከሰባት ሺሕ በላይ ሠራተኞች እንዲሁም እ.ኤ.አ. እስከ ሰኔ 2022 ከሁለት ሚሊዮን አንድ መቶ ሰማንያ ሺሕ በላይ ደንበኞች ያሉት ሲሆን፣ የባንኩ አጠቃላይ ሀብትም ከ61.2 ቢሊዮን ባላይ መድረሱንና በቀጣይም አገልግሎቱን የበለጠ ዘመናዊ በማድረግ ተደራሽነቱን ለማስፋት እየሠራ መሆኑ ተገልጿል፡፡