Thursday, June 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ18 ቀናት ግዢ መፈጸሚያ ብቻ እንደሚሆን አይኤምኤፍ ተነበየ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ0.6 ወር ወይም ለ18 ቀናት የውጭ ግዥዎችን (ኢምፖርት) ለመፈጸም ብቻ እንደሚሆን ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ተነበየ።

አይኤምኤፍ ሰሞኑን ይፋ ባደረገው የዓለም የኢኮኖሚ ዕድገትና ሁኔታ ሪፖርቱ እንደገለጸው፣ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2022 የያዘችው የውጭ ምንዛሪ ክምችት የ0.7 ወር ወይም ለ21 ቀናት የውጭ ግዥዎች ክፍያን ለመፈጸም ብቻ የሚበቃ እንደሆነ የገለጸ ሲሆን፣ ይህ ሁኔታ በቀጣዩ 2023 ሊያሽቆለቁል ይችላል የሚል ትንበያውን አስቀምጧል።

ይህ ሁኔታ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም ሊከሰት የሚችል እንደሆነ ያመለከተው አይኤምኤፍ፣ ለዚህም የዶላር የመግዛት አቅም መጨመሩ (የዶላር እጥረት መከሰት)፣ የሩሲያና ዩክሬን ጦርነትና ዓለም አቀፍ የሆነ የዋጋ ንረት መከሰትን በዋና ምክንያትነት አስቀምጧል። 

በመሆኑም እ.ኤ.አ. የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ0.6 ወር የሚሆን የውጭ ግዥዎች ክፍያ ለመፈጸም ብቻ የሚበቃ እንደሚሆን የድርጅቱ ትንበያ ያመለክታል።

ይኸው የአይኤምኤፍ መረጃ ላለፉት አምስት ዓመታት የነበረውን የኢትዮጵያ አማካይ ዓመታዊ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ያሚጠቁም ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. በ2021 የነበረው የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለአንድ ወር ከግማሽ የውጭ ግዥዎች ክፍያ የሚበቃ ነበር። ትልት የውጭ ምንዛሪ ክምችት በኢትዮጵያ የተያዘው እ.ኤ.አ. በ2019 ሲሆን፣ በወቅቱም የነበረው የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ2.2 ወራት የሚበቃ እንደነበር መረጃው ያመለክታል። እ.ኤ.አ. ከ2010 እስከ 2018 በነበሩት ዓመታት የነበረው አማካይ ዓመታዊ የውጭ ምንዛሪ ክምችት፣ ለሁለት ወራት የውጭ ግዥዎች ክፍያ የሚበቃ እንደነበር የአይኤምኤፍ መረጃ ያመለክታል።

የአፍሪካ አገሮችን የኢኮኖሚ ዕድገትና ሁኔታ ትንበያ በተመለከተ መግለጫ የሰጡት የአይኤምኤፍ የአፍሪካ ዳይሬክተር የሆኑት ኢትዮጵያዊው አበበ አዕምሮ እ.ኤ.አ. በ2023 በርካታ የእኅጉሪቱ አገሮች ፈተና እንደሚጠብቃቸው ገልጸዋል። በተለይም የዶላር መጠናከር ለአፍሪካ ቀጣና አገሮች ላይ ከባድ የማክሮ ኢኮኖሚ ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችል ገልጸዋል። የአፍሪካ ቀጣና በዩክሬን ጦርነትና በተለያዩ ዓለም አቀፍ አለመረጋጋቶች ሳቢያ የሚገጥመው የገበያ መዘጋት የአፍሪካ አገሮች ባለባቸው ከፍተኛ የውጭ ዕዳ ክምችት ላይ ሲደመር ትልቅና የተወሳሰበ የማክሮ ኢኮኖሚ አደጋ ውስጥ እንደሚከታቸው ገልጸዋል።

የአሜሪካ ዶላር እ.ኤ.አ. ከ2000 ጀምሮ ከፍተኛ መጠናከር ያሳየ ሲሆን ከ2022 ዓመት መጀመሪያ ጀምሮ ከአውሮፓ የመገበያያ ገንዘብ ዩሮ በ13 በመቶ፣ ከጃፓን መገበያያ ገንዘብ የን ደግሞ በ13 በመቶ እንዲሁም በማደግ ላይ ካሉ አገሮች የመገበያያ ገንዘብ በስድስት በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን የአይኤምኤፍ መረጃ ያመለክታል። እንዲህ ዓይነቱ የዶላር መጠን በወራት ውስጥ መጠናከር ዶላር በዓለም አቀፍ ንግድና ፋይናንስ ሥርዓት ውስጥ ካለው የበላይነት አንፃር በተጠቀሰው መጠን በወራት ውስጥ መጠናከሩ በሁሉም የዓለም አገሮች ላይ ትልቅ የማክሮ ኢኮኖሚ አንድምታ እንደሚኖረውም ያመለክታል።

የዶላር መጠናከር የሌሎች አገሮችን የመገበያያ ገንዘብ የሚያዳክም ከመሆኑ አንፃር የዋጋ ንረትን ለማውረድ የሚታገሉ በርካታ አገሮችን ትግል ከባድ እንደሚያደርገውም አይኤምኤፍ ገልጿል። 

ዶላር በአማካይ በአሥር በመቶ መጠናከር የአንድ በመቶ የዋጋ ግሽበት እንደሚፈጥር ይገመታል የሚለው የድርጅቱ ሪፖርት፣ ይህም ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ ጥገኛ ለሆኑ አገሮች፣ በተለይም ከፍተኛ የውጭ ዕዳ ጫና ያለባቸው ታዳጊ አገሮች ላይ በጣም ከባድ ጫና እንደሚፈጥር አስታውቋል።

በመሆኑም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ዕዳ ያለባቸው አገሮች የካፒታል ፍሰት አስተዳደርን ወይም ጥንቃቄ የተሞላበት የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን በመጠቀም የውጭ ምንዛሪ መዛነፎችን ሊቀንሱ ይገባል፡፡ በተጨማሪም የብድር አስተዳደር ስትራቴጂ በመቅረጽ ጤናማ የዕዳ ክፍያ ሁኔታዎችን እንዲቀይሱ መክሯል።

የኢትዮጵያ የውጭ ዕዳ ክምችት ከአጠቃላይ አገራዊ ምርት (ጂዲፒ) 25 በመቶ መድረሱን የአይኤምኤፍ መረጃ ያመለክታል። የኢትዮጵያ ገንዘብ ሚኒስቴር ባለፈው መስከረም ወር ያወጣው የአገሪቱ አጠቃላይ የውጭ ዕዳ መጠን 27.9 ቢሊዮን ዶላር መድረሱንና ይህም ከጂዲፒው 25 በመቶ መሆኑን ያመለክታል።

የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ገቢ እንዲሁም የውጭ ምንዛሪ ክምችት ቀውስ ውስጥ ከወደቀ ዓመታት የተቆጠሩ ሲሆን፣ መንግሥትም ይህንን ችግር ሳይሸሽግ በይፋ የሚናገረው ጉዳይ ነው። በሰኔ ወር 2014 ዓ.ም. የፌዴራል መንግሥት የ2015 ዓ.ም. በጀትን ለማቅረብ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገኙት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ‹‹የውጭ ምንዛሪ ክምችታችን ያን ያህል የሚያዝናና አይደለም›› ብለው ነበር። 

ከውጭ ምንዛሪ ጋር በተገናኘ ያሉትን መዋቅራዊ ችግሮች ለመፍታት ዕርምጃዎች በመወሰድ ላይ የነበሩ ቢሆንም፣ ጥረቶቹ የተሟላ ፍሬ ሳያፈሩ በአገሪቱ የሚገኙ የማምረቻ ተቋማት ተጨማሪ ተግዳሮቶችን በማስተናገዳቸው ምርቶቻቸውን በሚፈለገው ደረጃ አምርተው ለውጭ ገበያ እንዳያቀርቡ በማድረጋቸው የሚጠበቀውን ያህል ምርት ወደ ውጭ ልኮ ከሁሉም የምርት ዓይነቶች ሊገኝ የሚገባውን ያህል የኤክስፖርት ገቢ ባለፉት ዓመታት ማግኘት እንዳልተቻለ ገልጸው ነበር። 

‹‹በተለይም ተጨማሪ እሴት ፈጥሮና ምርቶችን በማስፋት ከኤክስፖርት የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ የተደረገው ጥረት ብዙም ርቀት አልተጓዘም፡፡ ይህም የውጭ ምንዛሪ ክምችት ችግራችንን በአስተማማኝ ምንጭ ላይ ለማድረግ የተያዘውን ተስፋ አፈጻጸሙ ከሚጠበቀው በታች እንዲሆን አድርጎታል፤›› ብለው ነበር፡፡

የመንግሥት ዕዳ ክምችትን የሥጋት ደረጃ ከከፍተኛነት ወደ መካከለኛ ብሎም ዝቅተኛ ደረጃ እስከሚሻሻል ድረስ አዳዲስ የንግድ የውጭ ብድሮች እንዳይወስዱ የሚከለክለውን መመርያ ተግባራዊ ከማድረግ ጀምሮ የዕዳ ሽግሽግ ድርድሮችን በማካሄድ የውጭ ዕዳ ክምችት እንዳይጨምር ማድረግ የሚያስችሉ ጥረቶች የተደረጉ ቢሆንም፣ ካለፈው ዓመት ጀምሮ የአገር ውስጥ ዕዳ ካምችትና የብድር ክፍያ ፍላጎት እየጨመረ ጫናው ወደ ኢኮኖሚ ሥጋትና አደጋነት እንዳይቀየር ክትትል በማድረግ አስፈላጊ እንደሆነም ተናግረዋል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች