የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በክፍያ ሰነድ አውጪነትና በክፍያ ሥርዓት ኦፕሬተርነት ሥራ ውስጥ የሚገቡ የውጭ አገር ድርጅቶችን ‹‹የኢንቨስትመንት ከለላ›› የተባለ ተጨማሪ ክፍያ ሊያስከፍል እንደሚችል የሚደነግግ የብሔራዊ የክፍያ ሥርዓት ረቂቅ የማሻሻያ አዋጅ ተዘጋጀ፡፡
የውጭ አገር ድርጅቶች በረቂቅ አዋጁ ላይ የተቀመጠውን ክፍያ የሚፈጽሙት የሚገቡበት ዘርፍ ከዚህ ቀደም ለውጭ ገበያ ያልተከፈተና አዲስ ዘርፍ ስለሆነ መሆኑን ሪፖርተር ከብሔራዊ ባንክ ምንጮቹ ተረድቷል፡፡ በዚህም መሠረት ከአዋጁ መፅደቅ በኋላ የብሔራዊ ባንክ በሚያወጣው መመርያ መሠረት እንደ ኤምፔሳ ያሉ በክፍያ ሰነድ አውጪነት የሚመደቡ የኤሌክትሮኒክ ገንዘብ አገልግሎት ሰጪ ኩባንያዎች አዲስ ዘርፍ ላይ ለመግባታቸው ብቻ ለባንኩ ክፍያ እንደሚፈጽሙ ይጠበቃል፡፡
በዚህ ዘርፍ ላይ የሚሰማሩ የውጭ ድርጅቶች ለኢንቨስትመንት ከለላ የሚከፍሉት፣ በክፍያ ሰነድ አውጪነትና (ሞባይል መኒ) በክፍያ ሥርዓት ኦፕሬተርነት ፈቃድ ለማግኘት ለብሔራዊ ባንክ ከሚከፍሉት የፈቃድ ማግኛ ክፍያ በተጨማሪ ነው፡፡
የብሔራዊ የክፍያ ሥርዓት ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ትናንት ማክሰኞ ጥቅምት 7 ቀን 2015 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ፣ ወደ ዕቅድ በጀትና ፋይናስን ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል፡፡ ረቂቅ አዋጁ በ2012 ዓ.ም. መጨረሻ የፋይናንስ ተቋም ያልሆኑ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች እንዲሠሩ በተፈቀደበት የክፍያ ሰነድ አውጪነትም ሆነ በክፍያ መፈጸሚያ ዘርፍ የውጭ ድርጅቶችም እንዲሰማሩ የሚፈቅድ ነው፡፡
በክፍያ ሰነድ አውጪነትና በክፍያ ሥርዓት ኦፕሬተርነት የሚሰማሩ የውጭ ድርጅቶችም ሆነ ሙሉ በሙሉ በውጭ ዜጎች የተያዙ የኢትዮጵያ ድርጅቶች፣ ፈቃድ ለማግኘት ብሔራዊ ባንክ በሚያወጣው መመርያ የሚወሰነውን ካፒታል ሙሉ በሙሉ በውጭ ምንዛሪ መክፈል እንደሚኖርባቸው ረቂቅ አዋጁ አስቀምጧል፡፡
በከፊል በውጭ ዜጎች የተያዙ የውጭ ድርጅቶች ደግሞ የውጭ አገር ዜጎች በድርጅቱ ውስጥ የያዙት ጠቅላላ ድርሻ በመቶኛ ተሠልቶ በውጭ ምንዛሪ መክፈል ይጠበቅባቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በ2003 ዓ.ም. የወጣውን የብሔራዊ ክፍያ አዋጅ ላይ በመመሥረት በ2012 ዓ.ም. የክፍያ ሰነድ አውጪነት ፈቃድ የሚሰጥበትን መመርያ ማውጣቱ ይታወሳል፡፡ ይህ መመርያ የባንኮችን የክፍያ ሥርዓት ብቻ ሲያሳልጡ የነበሩ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በራሳቸው የኤሌክትሮኒክ ገንዘብ አገልግሎትን እንዲሰጡ ያስቻለ ነው፡፡ በዚህም መሠረት የኢትዮ ቴሌኮሙ የፋይናንሰ ተቋም ሳይሆን የኤሌክትሮኒክ ገንዘብ አገልግሎት ፈቃድ አግኝቶ ቴሌ ብርን ሥራ አስጀምሯል፡፡ ከግሉ ዘርፍ ደግሞ ካቻ ዲጂታል ፋይናንሺያል ሰርቪስ አክሲዮን ማኅበር የመጀመርያውን ፍቃድ ሐምሌ 2014 ዓ.ም. ማግኘቱ ይታወሳል፡፡
የክፍያ ሰነድ አውጪነት ፈቃድ ያለው ቴሌ ብር በቴክኖሎጂ ሥርዓቱ ላይ የኤሌክትሮኒክ ገንዘብ ማስቀመጥ፣ መቀበል እንዲሁም ክፍያ መፈጸም ያስችላል፡፡ የክፍያ ሰነድ አውጪነት ፈቃድ የሚያገኙ ድርጅቶች በተጨማሪነት የአነስተኛ ብድር፣ አነስተኛ መድኅን፣ ወደ አገር ውስጥ የሚላክ ዓለም አቀፍ ሃዋላና ሌሎች ተዛማጅ አገልግሎቶችንም ከፋይናንስ ተቋማት ጋር በመሆን መሥራት ይችላሉ፡፡
በክፍያ ሥርዓት ኦፕሬተርነት ፈቃድ ያገኙት እንደ ‹‹ኢቲ ስዊች›› ያሉት ኩባንያዎች ሥራቸው የሚያተኩረው በክፍያ ሰነድ አውጪ የፋይናንስ ተቋማት መካከል የገንዘብ ዝውውሩን ማሳለጥ ላይ ነው፡፡
በክፍያ ሰነድ አውጪነት ዘርፍ ለመጀመርያ ጊዜ ፈቃድ ያገኘው ቴሌ ብር ሥራ ከጀመረ ገና ሁለት ዓመት ያልሞላው ሲሆን ይህም ዘርፉ በኢትዮጵያ አጭር ጊዜ ብቻ ያለውና ያልተነካ ለመሆኑ ማሳያ ሆኖ ይነሳል፡፡
ዘርፉ ክፍት ሳይደረግ በመቆየቱ ከውጭ ለሚገቡ ኩባንያዎች ‹‹ትልቅ ዕድል›› እንደሆነ ለሪፖርተር የገለጹ የብሔራዊ ባንክ ኃላፊ፣ በዚህም ምክንያት ከብሔራዊ ክፍያ ሥርዓት ረቂቅ የማሻሻያ አዋጅ መፅደቅ በኋላ ፈቃድ ሲያገኙ ‹‹የኢንቨስትመንት ከለላ ክፍያ›› በተጨማሪነት እንዲከፍሉ መታቀዱን አስረድተዋል፡፡ ከፈቃድ ማግኛ ክፍያ በተጨማሪ የሆነው ይህ ክፍያ ለአንድ ጊዜ የሚከፈል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የክፍያው መጠን ምን ያህል እንደሚሆንና ሌሎች ዝርዝሮች ከአዋጁ መፅደቅ በኋላ ባንኩ በሚያወጣው መመርያ እንደሚገለጹ ተናግረዋል፡፡
የክፍያ ሰነድ አውጪነትን በተመለከተ የመጀመርያው የውጭ ኩባንያ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው የሳፋሪ ኮሙ ኤምፔሳ ፈቃድ እንደሚያገኝ ከመንግሥት ቃል ተገብቶለታል፡፡ ሳፋሪ ኮም በአገር አቀፍ ደረጃ ሥራ መጀመሩን በአዲስ አበባ ይፋ ባደረገበት ሥነ ሥርዓት ላይ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ለኤም ፔሳ ፈቃድ ለመስጠት ስምምነት ላይ መደረሱን ይፋ አድርገዋል፡፡
ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ፣ በኢትዮጵያ የቴሌኮም ኦፕሬተርነት ፈቃድ ለማግኘት 850 ሚሊዮን ዶላር ክፍያ መፈጸሙ ይታወሳል፡፡
ሪፖርተር ያነጋገራቸው የብሔራዊ ባንክ ኃላፊ ኤምፔሳ ‹‹የኢንቨስትመንት ከለላ ክፍያ›› የመክፈሉን ጉዳይ በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ‹‹ሳፋሪኮም የቴሌኮም ኦፕሬተርነት ፈቃድ ሲያገኝ ከመንግሥት ጋር ምን ዓይነት ንግግር እንዳደረገ አላወቅንም፣ ቀድመው የፈጸሙት ክፍያም ስላላ መመርያው ሲወጣ የሚታይ ይሆናል፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡