ሰሞኑን መንግሥት 38 ዓይነት ምርቶች ላልተወሰነ ጊዜ ከውጭ እንዳይገቡ አግዷል፡፡ በምርቶቹ ላይ ጊዜያዊ ዕገዳ የተጣለው ቅድሚያ የማይሰጣቸው በመሆናቸው እንደሆነም ተነግሯል፡፡ ከዚህ በዘለለም ለውጭ ምንዛሪ ተመን መናርና ለሕገወጥ ገንዘብ ዝውውር ምክንያት እንደሆኑ፣ በጉምሩክ ኮሚሽን አማካይነትም በጥናት ላይ በመመሥረት አስፈላጊ እንዳልሆኑም ተመላክቷል፡፡ እርግጥ ነው መንግሥት እዚህ ደረጃ ላይ ሲደርስ ምን ያህል አጣብቂኝ ሁኔታ ውስጥ እንዳለ ለመረዳት አያቅትም፡፡ ዕርምጃው እንደ የፕላስቲክ አበባ፣ ከረሜላ፣ ማስቲካ፣ ሲጋራ፣ የአልኮል መጠጦች፣ የመዋቢያ ዕቃዎች፣ ሰው ሠራሽ ፀጉሮችና ሌሎች ምርቶች ላይ ነው የተወሰደው፡፡ አንዳንዶቹ ጊዜያዊ ዕገዳ የተጣለባቸው ምርቶች አስመጪዎችና አከፋፋዮች በደንበኞቻቸው የተጨናነቁ ሲሆን፣ በተለይ የአልኮል መጠጦች ላይ የተስተዋለው ግርግር ቀላል አይደለም፡፡ ከታገዱት ምርቶች ውስጥ ከወዲሁ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ የተደረገባቸው ሲኖሩ፣ ከያሉበት እየተሰባሰቡ የሚከማቹም መኖራቸው ታውቋል፡፡ ይህ ሁሉ የሚያሳየው ኢኮኖሚው ውስጥ በከፍተኛ መጠን የተበተነ ገንዘብ መኖሩን ነው፡፡ ኢኮኖሚው ውስጥ ከመጠን በላይ የተበተነው ገንዘብ ፈር ካልያዘ፣ ገበያው ብቻ ሳይሆን አገርም ትበጠበጣለች፡፡
በጥቁር ገበያው ውስጥ የሚስተዋለው የዶላር ምንዛሪ ከሚገባው በላይ መናር አንዱ ማሳያ፣ ኢኮኖሚው ውስጥ ገንዘብ በከፍተኛ መጠን መበተኑ ነው፡፡ የጥቁር ገበያው ንግድ ከአሜሪካ እስከ ዱባይ በሰፊው የተዘረጋ ስለሆነ፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን የሚያስመጡ የበረከቱ ተሳታፊዎች ለመሆናቸው ብዙ የተባለበት ነው፡፡ የጥቁር ገበያው ጦስ ተሸካሚ ግን የፈረደበት ደሃ ሕዝብ ነው፡፡ በከፍተኛ የዋጋ ግሽበት እየተመታም ነው፡፡ መንግሥት ለጊዜው እንደ ማስታገሻ ከሚወስዳቸው ጊዜያዊ ዕርምጃዎች በላይ፣ ዘለቄታዊና አስተማማኝ መፍትሔዎች ላይ ማተኮር አለበት፡፡ አሁን እየተወሰዱ ያሉ ዕርምጃዎች እንደ ሕመም ማስታገሻ እያገለገሉ፣ ችግሩን እስከ ወዲያኛው ለማስወገድ የሚያግዙ መፍትሔዎች ያስፈልጋሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የውጭ ምንዛሪ ችግር መነገር ከጀመረ ብዙ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ አንዱ ጥያቄ መሆን ያለበት የውጭ ምንዛሪ ችግር ምክንያቱ ምን ይሆን የሚለው ሲሆን፣ ሌላው ጥያቄ ደግሞ በአገር ውስጥ ምርቶች በብዛት ተመርተው ለምን የዋጋ መረጋጋት አይፈጠርም ነው፡፡ ብዙዎቹ ጊዜያዊ ዕገዳ የተጣለባቸው ምርቶች በአገር ውስጥ መመረት የሚችሉ በመሆናቸው፣ ለምን የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ እንደሚያባክኑ ግራ ያጋባል፡፡
በቀላል ተሽከርካሪዎችም ሆነ በአልኮል መጠጦች ንግድ አካባቢ የሚስተዋለው ከመጠን ያለፈ ስግብግብነት፣ የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ መጫወቻ ከማድረጉም በላይ ለጥቁር ገበያ መንሰራፋት ራሱን የቻለ አስተዋጽኦ አለው፡፡ የደረሰኝ ዋጋ በማሳነስ (አንደር ኢንቮይሲንግ) አማካይነት በሚፈጸመው ሸፍጥ፣ ከፍተኛ ብር እየተንቀሳቀሰ ጥቁር ገበያውን እንዳደራው ፀሐይ የሞቀው ሀቅ ነው፡፡ ለዶላር አደን የተሰማራው ከፍተኛ መጠን ያለው ብር ገበያው ውስጥ ሲተራመስ የምግብ፣ የግንባታ፣ የመለዋወጫና የሌሎች ምርቶችን ዋጋ በየቀኑ እያናረው ነው፡፡ ለዚህ እንደ ምሳሌ የሚወሰደው በሲሚንቶ ዋጋ ላይ የታየው አስደንጋጭ ክስተት ነው፡፡ መንግሥት ዕርምጃው በጥናት ላይ የተመሠረተ ሲሆን ግን፣ ግራና ቀኙን እያገናዘበ ከጊዜያዊ ባሻገር ዘለቄታዊ መፍትሔዎች ላይ ያተኩራል፡፡ አሁን መሬት ላይ የሚታየው እውነታ ከምርቶቹ ጊዜያዊ ዕገዳ በላይ ስለሆነ፣ መንግሥት በራሱ የሚያካሂዳቸውን ፕሮጀክቶች ወጪ መልክ እያስያዘ፣ የማስተካከያ ዕርምጃዎችን ማሰብ አለበት፡፡ በሰሞኑ የምርቶቹ ዕገዳ ምክንያት የሚከሰቱ አዳዲስ የዋጋ ጭማሪዎችንና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን እያስተዋለ፣ ኢኮኖሚው ውስጥ የተዘራው ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ፈር እንዲይዝ ያስብበት፡፡
እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ከተወሰኑት በስተቀር ብዙዎቹ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች አገር ውስጥ መመረት የነበረባቸው ናቸው፡፡ ከአገር ውስጥ ቡና፣ የቀንድ ከብቶች፣ ወርቅና የመሳሰሉ የኤክስፖርት ምርቶች በኮንትሮባንድ እንዲወጡ ይደረጋል፡፡ በተመሳሳይ የአገሪቱን ሱፐር ማርኬቶች የሚያጨናንቁ ምርቶች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ይገባሉ፡፡ በሃዋላ መገኘት የሚገኝበት የውጭ ምንዛሪ በኮንትሮባንድ አቀናባሪዎች አማካይነት እየተጠለፈ፣ ጦር መሣሪያን ጨምሮ የሌሎች ምርቶች ኮንትሮባንድ ይስፋፋል፡፡ ቶጎ ጫሌ በምትባል አነስተኛ የጠረፍ ከተማ የአገሪቱ ባንኮች ቅርንጫፎች የሚገኙበት ምክንያት ምን ይሆን ሲባል የሚናገር የለም፡፡ በባንኮች አካባቢ የሚስተዋለው ጤናማ ያልሆነ እንቅስቃሴ ላይ ትኩረት ቢደረግ ደግሞ ጉዱ ይዘረገፋል፡፡ ኢኮኖሚው ውስጥ የተበተነው ገንዘብ መጠኑ በጣም ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ፣ ሕገወጥ የውጭ ምንዛሪ ንግዱም ሆነ ኮንትሮባንዱ እንዲስፋፋ ምክንያት ለመሆኑ ብዙም ልፋት አያስፈልገውም፡፡ ዱባይና አሜሪካ ሆነው ከአገር ውስጥ ሸሪኮቻቸው ጋር ኢኮኖሚውን የሚያሽመደምዱት አካላት መላ ይፈለግላቸው፡፡
የመንግሥት የሰሞኑ ዕርምጃ የከፋ አደጋ ለመከላከል የተወሰደ እንደሆነ ይታመናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በተሽከርካሪዎች ገበያ ውስጥ ከዕገዳው በተጨማሪ የሚስተዋለው ሕገወጥነትም አደብ መግዛት አለበት፡፡ ተሽከርካሪዎቹ አገር ውስጥ ሲገቡ አስመጪዎቹ የገዙበት ደረሰኝና የመሸጫ ዋጋቸው የንግድ አሠራርን የሚቃረን ነው፡፡ በመቶዎች ዶላር የግዥ ደረሰኝ የቀረበበት አንድ ተሽከርካሪ በትንሹ ሦስት ሚሊዮን ብር የመሸጫ ዋጋ ሲጠየቅበት (ቀረጡ በጣም ዝቅተኛ በሆነበት በዚህ ጊዜ)፣ ገበያው ምን ያህል መረን እንደተለቀቀ አመላካች ነው፡፡ ሌተር ኦፍ ክሬዲት ተከፍቶላቸው በዝቅተኛ የደረሰኝ ዋጋ የሚገቡት ተሽከርካሪዎች ከፍተኛ የመሸጫ ዋጋ ሲጠራባቸው፣ ንግዱ የሚቀላጠፈው በጥቁር ገበያ ተመን እንደሆነ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ ጥቁር ገበያው እየደራ ያለው ደግሞ ከባንክ ውጪ የሚደረገው የገንዘብ ዝውውር በመጧጧፉ እንደሆነ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ይህንን ዓይነቱን ሥርዓተ አልበኝነት ዓይተው እንዳላየ መሆን ማቆም አለባቸው፡፡ ኢኮኖሚው ውስጥ ከመጠን በላይ የተበተነው ገንዘብ ሕገወጥ ንግዱን ከማድራት በተጨማሪ፣ የኑሮ ውድነቱን እያባባሰው የዜጎችን ሕይወት እያመሰቃቀለ ነው፡፡
በሌላ በኩል መንግሥት ከውጭ በሚገቡ የተወሰኑ ምርቶች ላይ ጊዜያዊ ዕገዳ ሲጥል፣ በአገር ውስጥ ያሉ አምራቾች ተነቃቅተው ሌሎች ምርቶችን ጭምር የሚተኩ ሥራዎች ላይ እንዲሰማሩ ዕገዛ ማድረግ ይገባል፡፡ ለምሳሌ የማምረቻ ቦታዎች፣ የባንክ ብድሮችና ሌሎች ድጋፎች እንዲያገኙ ዕድሎችን ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ላይ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር፣ ይህንን አጋጣሚ መጠቀም ይኖርበታል፡፡ ‹‹ችግር የፈጠራ እናት ናት›› እንደሚባለው በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ዜጎች ፈጠራዎቻቸው እንዲደገፉ ጥረት ማድረግ ይገባል፡፡ ክህሎት እያላቸው በፋይናንስ ዕጦት ለሚቸገሩ ዕድሉን በመስጠት መፈተን ተገቢ ነው፡፡ የየትኛውም የበለፀገ አገር ታሪክ እንደሚያስረዳው ክህሎት ያላቸው ግለሰቦች ናቸው አውሮፕላን፣ ስልክ፣ መኪና፣ ባቡር፣ መርከብና መሰል ፈጠራዎችን ያስገኙት፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥም በርካታ የተፈጥሮ ፀጋዎችን በመጠቀም ታሪክ መሥራት የሚችሉ ዜጎች እንዳሉ ምልክቶች እየታዩ ነው፡፡ በቴክኖሎጂው መስክ የሚስተዋለው መነቃቃት ተስፋ ሰጪ ነው፡፡ በዛሬዋ ኢትዮጵያ ምንጩ የማይታወቅ ገንዘብ ኢኮኖሚው ውስጥ ተበትኖ ግራ ሲያጋባ ለምን መባል አለበት!