Thursday, June 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለአራት ዓመታት ተቋርጦ የነበረው የሊዝ ጨረታ በ109 መሬቶች ሊጀመር ነው

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ወቅታዊ የሊዝ መነሻ ዋጋ ከ2000 ብር እስከ 39,000 ብር መሆኑ ተጠቁሟል

የአዲስ አበባ ከተማ መሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ ከአራት ዓመታት በላይ አቋርጦት የነበረውን የመሬት ሊዝ ጨረታ፣ በድጋሚ ለማስጀመር 109 መሬቶችን አዘጋጅቶ ለጨረታ ሊያቀርብ ነው፡፡

በመሬትና መሬት ነክ አገልግሎቶች የተንሰራፋው ብልሹ አሠራር እስከሚስተካከል ድረስ፣ የመሬት አቅርቦትም ሆነ አገልግሎት አሰጣጥ እንዲቆም ተወስኖ እንደነበር አይዘነጋም፡፡

ለአልሚዎች ተላልፈው ለበርካታ ዓመታት ታጥረው የተቀመጡ ይዞታዎችን በመንጠቅ ወደ አስተዳደሩ የመሬት ባንክ የመመለስ ሥራዎች ሲከናወኑ፣ እንዲሁም መሬት ለአዲስ አልሚዎች በጨረታ የሚተላለፍበት ሥርዓት ላይ ያለው የአሠራር ችግር ተጠንቶ እስኪቀረፍ ድረስ፣ መሬት በጨረታ እንዳይቀርብ ዕግድ ተጥሎ ነበር፡፡

በዚህ መሠረት ሐምሌ 21 ቀን 2010 ዓ.ም. የወጣውና በሒደት ላይ የነበረው 30ኛው የሊዝ ጨረታ ታግዶ የቆየ ሲሆን፣ ከ2011 ዓ.ም. በፊት በነበሩት ሁለት ዓመታትም ቢሆን በከተማ አስተዳደሩ ዕቅድ መሠረት አንድም መሬት ለጨረታ አልቀረበም፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በየወሩ መሬት በሊዝ ጨረታ ለማቅረብ ቢያቅድም፣ ከ2009 ዓ.ም. ጀምሮ ለጨረታ የቀረበው ሦስት ጊዜ ብቻ ነው፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ መሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ አማካይነት፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተሰጠ ትዕዛዝ መሠረት፣ በሁሉም ክፍላተ ከተሞች 109 የተዘጋጁ መሬቶችን ለሊዝ ጨረታ መዘጋጀቱን ለሪፖርተር የደረሰው መረጃ ያሳያል፡፡

የመሬት ሊዝ ጨረታ በሁለት ዓይነት መንገድ ማለትም በማንዋልና በአውቶሜሽን የሚዘጋጅ መሆኑን፣ የዘንድሮው የተዘጋጀው በማንዋል እንደሆነ ታውቋል፡፡

የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ከሚቀጥለው ሳምንት መጨረሻ ጀምሮ የመሬት ሊዝ ጨረታውን በጋዜጣ አሳትሞ እንደሚያወጣ የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባደረገው ጥናት በየክፍለ ከተማው የመሬት የሊዝ መነሻ ዋጋዎች በአራት ደረጃ በመከፈል ይለያያሉ፡፡ መሀል ከተማ የሚገኙ ደረጃ አንድ መሬት በካሬ ሜትር 2,213 ብር ድረስ ሲሆን፣ ከርቀት የሚገኙ አካባቢዎች በካሬ ሜትር 748 ብር ነው፡፡

በወቅታዊ የሊዝ ጨረታ ዋጋ አንድ ካሬ ሜትር ከ2,800 እስከ 39 ሺሕ ብር መሆኑን ለሪፖርተር የደረሰው ዝርዝር ያሳያል፡፡

በአሁኑ ጨረታ ይወጣሉ ተብለው የሚጠበቁ መሬቶች ለመኖሪያ፣ ለንግድና ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ናቸው፡፡

የመሬት ሊዝ ጨረታ ዋነኛ ግብ ፍትሐዊ ጥቅም ማስገኘት፣ ጥቅምን ማስከበር፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥና ለተጠቃሚዎች ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ይናገራል፡፡

የከተማ ቦታ በሊዝ ስለመያዝ የሚደነግገው አዋጅ ቁጥር 721/2004 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካወጣቸው ደንብና መመርያዎች ጋር የሚጣረስ በመሆኑ ታግዶ መቆየቱ አይዘነጋም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች