Tuesday, October 3, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ ያለው ሦስተኛው ከግል ባንክ ሆነ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ማድረስ የቻለ ሦስተኛው የግል ባንክ ሆነ፣ አጠቃላይ የሀብት መጠኑም ከ121 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱ ተጠቆመ፡፡

የ2015 የመጀመርያ የሩብ ዓመት አፈጻጸሙን የሚያመለክተው ከባንኩ የተገኘው መረጃ ፣ በዘንድሮው ሩብ ዓመት የባንኩ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ የደረሰ ሲሆን፣ ለዚህም ባለፉት ሦስት ወራት ከስድስት ቢሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ መቻሉ አስተዋጽኦ አድርጓል። ይህም በሩብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ ባንኩ የደረሰበት ጠቅላላ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን 102 ቢሊዮን ብር እንዲሆን አስችሏል። ባንኩ እስከ ሰኔ 2014 ዓ.ም. ድረስ ጠቅላላ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑ 96.77 ቢሊዮን ብር እንደነበር የሚያመለክተው የባንኩ መረጃ፣ የተቀማጭ ገንዘብ በማሰባሰቡ ረገድ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ ከቀዳሚዎቹ ሦስት የግል ባንኮች አንዱ እንዳደረገው አመልክቷል፡፡ 

የባንኩ ምክትል ፕሬዚዳንት (የስትራቴጂ ማርኬቲንግ) አቶ ታደለ ጥላሁን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ተቀማጭ ገንዘብ በማሰባሰቡ ሥራም ሆነ በሌሎች የባንክ አፈጻጸሞች ባንካቸው ከግል ባንኮች ሦስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል። ከዚህም ባለፈ እስከ ሩብ ዓመቱ መጨረሻ (September 30/2022) ድረስ በነበረው አፈጻፈም የባንኩ አጠቃላይ የሀብት መጠን 121 ቢሊዮን ብር መድረሱን ጠቅሰዋል፡፡ ይህ የሀብት መጠን በሦስት ወራት ውስጥ ከሰባት ቢሊዮን ብር በላይ መጨመሩንም አመልክተዋል።

ባንኩ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ የነበረው ጠቅላላ የሀብት መጠን 114.3 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ በሦስት ወራት  ውስጥ ከሰባት ቢሊዮን ብር በላይ በመጨመር የሀብት መጠኑን ወደ 121 ቢሊዮን ብር ማድረስ ችሏል፡፡

ከኢትዮዮጵያ ንግድ ባንክ ቀጥሎ በአገሪቱ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አስቀማጭ ደንበኞች ያሉት የኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ፣ በሩብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ አጠቃላይ የቁጠባ ሒሳብ የከፈቱ ደንበኞች ብዛት 9.3 ሚሊዮን ደርሰዋል፡፡ ይህ አኃዝ ባንኩ ከግል ባንኮች ከፍተኛ ቁጥር ያለው አስቀማጮች በመያዝ በአንደኛነት ይዞት የቆየውን ደረጃ ማስቀጠሉን አቶ ታደለ ገልጸዋል። የባንኩ ጠቅላላ የብድር ክምችትም የመጀመርያው ሩብ ዓመት ላይ 86 ቢሊዮን ብር መድረሱ ታውቋል፡፡ የባንኩ የብድር ክምችት ሰኔ 2014 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ 55.7 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በአዲስ አበባ ቦሌ ሩዋንዳ አካባቢ ከምድር በታች አራትና ከምድር በላይ 16፣ በጥቅሉ 21 ወለሎች ያሉትን የመሸጋገሪያ ዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ  ግንባታ በማጠናቀቅ ላይ መሆኑን አስታውቋል፡፡ አቶ ታደለ እንደገለጹት፣ ይህ የመሸገገሪያ ሕንፃ ለዋና መሥሪያ ቤትነት የሚያገለግል ሲሆን፣ ወደ እዚህ ሕንፃ ለመግባት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት ይህንን ሕንፃ ‹‹ቻይዊ›› የተባለ የኮንስትራክሸን ኩባንያ በማገባደድ ላይ ነው፡፡  ከዚሁ ጋር ተያይዞ የኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ በአዲስ አበባ ‹‹የፋይናንስ መንደር›› በመባል በሚታወቀው ሠንጋ ተራ አካባቢ ባለ 47 ወለል የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ግንባታ ለመጀመር ዳር አል ሃንዳሳህ የተባለውን የውጭ አማካሪ ድርጅት መምረጡ ይታወሳል፡፡

ባንኩ ሰሞኑን ከዳር አል ሃንዳሳህ ኮንሰልታንት ጋር የኮንትራት ውል በተፈራረሙበት ወቅት እንዳስታወቀው፣ ወደ ግንባታው ለመግባት በቅድሚያ መሠራት የሚኖርባቸውን የዲዛይን ጥናትና የግንባታ ጨረታ ሰነድ የማዘጋጀት ሥራ የዚሁ አማካሪ ድርጅት ይሆናል፡፡ ከዚህም ሌላ  የግንባታ ውል ማስተዳደርና ተያያዥ ሥራዎችን በሙሉ ይኼው አማካሪ ድርጅት እንዲሠራ በባንኩና በአማካሪ ኩባንያው መካከል የተፈረመው ውል ያመለክታል፡፡ ከዲዛይን ሥራው ጀምሮ ባንኩ የሚያስነገባውን ሕንፃ እስከ መጠናቀቂያው ጊዜ ድረስ የመቆጣጠር ኃላፊነት ጭምር የተሰጠው አማካሪ ድርጅቱ፣ በገባው ውል መሠረት የዲዛይን፣ ጥናቱንና የጨረታ ዘነድ ዝግጅቱን በስድስት ወራት ማቅረብ ይኖርበታል ተብሏል፡፡ 

የኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ደርቤ አስፋው እንደገለጹት፣ አማካሪ ኩባንያው በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን ልምድ በመጠቀም ዘመናዊ ሕንፃ ለመገንባት ያስችላል፡፡ የዚህ ሕንፃ ግንባታ በብሔራዊ ቴአትር አጠገብ ባለ ቦታ ላይ የሚገነባ ሲሆን፣ አጠቃላይ የሕንፃው ዲዛይን ለአዲስ አበባ ከተማ ገጽታ ግንባታው ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሏል፡፡

በባንኩ መረጃ መሠረት የፋይናንስ ተቋማት እየተሰባሰቡበት ባለው አካባቢ የሚገነባው ባለ 47 ወለል ሕንፃ አራቱ የሕንፃ ወለል ከምድር በታች የሚገነቡ ናቸው፡፡ 

ለማማከር ሥራው የተመረጠው ኩባንያ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በርካታ ሥራዎችን የሠራ፣ መቀመጫውን ባህሪን ያደረገ ኩባንያ ነው፡፡ በዕለቱ የተደረውን ስምምነት ዳር አል ሃንዳሳህ ኩባንያ ተወካይ ሚስተር ታሪቅ አልኳኒ እና የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ድርቤ አስፋው ፈርመዋል፡፡  

የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ የሀብት መጠኑን ከፍ ለማድረግ፣ የተለያዩ ግንባታዎችን እያካሄደ መሆኑን ያመለከተ ሲሆን፣ ተመሳሳይ የሕንፃው ግንባታዎቹን ከአዲስ አበባ ከተማ ውጭ በተለያዩ ከተሞች እያካሄደ እንደሚገኝ ተጠቁሟል። ባንኩ 12,500 ጊዜያዊና ቋሚ ሠራተኞች ያሉት ሲሆን፣ የቅርጫፎቹን ቁጥርም 611 አድርሷል፡፡

 

   

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች