- ዋና ሥራ አስኪያጁን ከሥራ አሰናብቷል
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በብሔር ስምና ሃይማኖታዊ ይዘት ያላቸውን ስያሜዎች የሚጠቀሙ ክለቦች ከ2015 የውድድር ዘመን አንስቶ የስም ቅያሬ መመርያ ማውጣቱ ይታወሳል፡፡ አዲሱ መመርያ መውጣቱን ተከትሎ፣ ከቀናት በፊት ወላይታ ድቻ እግር ኳስ ክለብ ‹‹ድቻ›› ተብሎ እንደሰየመ በደብዳቤ ቢያሳውቅም፣ መስከረም 25 ቀን 2015 ዓ.ም. ስያሜውን መሻሩን አስታውቋል።
ክለቡ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በላከው ደብዳቤ መሠረት ከቀናት በፊት የክለቡ ሥራ አስኪያጅ የጻፉት ደብዳቤ የአሠራር ሥርዓትን የጣሰ፣ በግለሰብ ስሜት የተጻፈና የተፈረመ ከመሆኑም በላይ፣ ሰፊውን የወላይታ ሕዝብና የክለቡን ደጋፊ ክብር ከግምት ያላስገባ መሆኑን ለፌዴሬሽኑ በላከው ደብዳቤ አብራርቷል።
ከዚህም ባሻገር በዞኑ ሥራ አስፈጻሚና በክለቡ ቦርድ አባላት ውይይት ያልተደረገበትና ያልተወሰነ በመሆኑ በዋና ሥራ አስኪያጁ የተወሰነው ውሳኔ መሻሩን ገልጸዋል።
በዚህም መሠረት ክለቡ በቀድሞ ስሙ ወላይታ ድቻ እግር ኳስ ክለብ በሚለው ስያሜ እንደሚቀጥል አስታውቋል። ክለቡ ዋና ሥራ አስኪያጁንም ከሥራ ማባረሩን ይፋ አድርጓል።
እንደ ክለቡ ማብራሪያ ከሆነ ‹‹ወላይታ›› የሚለው የብሔር ስም አለመሆኑንና ይልቁንም የወላይታ ማኅበረሰብ አንድነት የሚጠቅስ ስያሜ ነው የሚል መከራከሪያ አቅርቧል፡፡
ሆኖም መረጃዎች እንደሚያስረዱት የስያሜ ለውጡን የሚሽረው ደብዳቤ የደረሰው ፌዴሬሽኑ፣ ክለቡ በቀድሞ መጠርያው “ወላይታ ድቻ ስፖርት ክለብ” በሚለው ስያሜው እንደሚቀጥል መወሰኑ ተሰምቷል፡፡
ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እየተሳተፉ ለሚገኙ ክለቦች የሃይማኖትና የብሔር ስያሜ ያላቸውን ክለቦች፣ ስያሜያቸውን የሚቀይሩበት መመርያ ለሁሉም ክለቦች መላኩ ይታወሳል፡፡ በዚህም በውድድሩ ላይ እየተካፈሉ ከሚገኙ ክለቦች መካከል ሀዲያ ሆሳዕና፣ ሲዳማ ቡናና ወላይታ ድቻ የክለብ ስያሜያቸውን መቀየር ካለባቸው ክለቦች ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው፡፡