የሰው ልጅ ጠብን በዕርቅ፣ በደልን በይቅርታ፣ ድህነትን በልማት፣ ክህደትን በሃይማኖት እያረመ መኖር ይኖርበታል ሲሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ አሳሰቡ፡፡
የ2015 ዓ.ም. የመስቀል በዓል፣ ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ በተገኙበት መስከረም 16 ቀን በመስቀል አደባባይ ደመራ በመለኮስ ሲከበር፣ መልዕክታቸውን ያስተላለፉት ቅዱስ ፓትርያርኩ፣ የመስቀሉን በዓል ችግሮቻችንን በዕርቅና በይቅርታ በመፍታት ማክበር አለብን ብለዋል፡፡
‹‹ሰው ይቅርና እግዚአብሔርም ከሰው ጋር የነበረውን ጥል የፈታው በዕርቅ ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው ይቅርታ በእግዚአብሔር ዘንድ ያለውን ተቀባይነት ነው፤›› ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡
ነገረ መስቀሉን በውል የተረዳ ፍጡር ይቅርታ ተጠይቆ ቀርቶ ወደ በዳይ በመሄድ ጭምር ዕርቅን ለመፈጸም አያዳግትም ሲሉም ተናግረዋል፡፡
‹‹በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠርን ሁሉ ለሰላምና ለዕርቅ መሸነፍ የለብንም፤›› በማለት፣ በአፅንኦት የተናገሩት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ማትያስ ቀዳማዊ፣ ‹‹በዕርቅ ላይ የተመሠረተ የጠብ መፍትሔ በመንፈሳዊ፣ በዓለማዊና በሞራላዊ ሕግጋት ሁሉ ተቀባይነት አለው፤›› ብለዋል፡፡
በክብረ በዓሉ ላይ ስለአገር ሰላም በብፁዕ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ዲዮስቆሮስ መሪነት የምሕላ ጸሎት ደርሷል፡፡
የመስቀል በዓል ከአራተኛው ምዕት ዓመት ጀምሮ መስከረም 17 ቀን ከደመራ ጋር የሚከበር ሲሆን በዋዜማው የቤተክርስቲያን መታነፅ ይከበራል፡፡
የመስቀል በዓል መለያው ደመራው ነው፡፡ ደመራ ንግሥቲቱ ቅድስት ዕሌኒ ክርስቶስ የተሰቀለበትን መስቀል በአይሁዶች ከተቀበረበት ለማውጣት፣ በኢየሩሳሌም ቀራንዮ በሚባል አካባቢ በጎልጎታ ቁፋሮ ያስጀመረችበትን ቀን ለማሰብ የሚከበር ሥነ ሥርዓት ነው፡፡
የደመራ ሥነ ሥርዓቱም ከቦታ ቦታ ይለያያል፡፡ በትግራይ፣ በላስታና ላሊበላ፣ በአክሱም፣ በሰሜንና በደቡብ ወሎ፣ በዋግ ሕምራ፣ በከፊል ጎጃምና በአዊ፣ በሽናሻ (ንጋት 11 ሰዓት) ደመራው የሚለኮሰው መስከረም 17 ቀን ንጋት ላይ ነው፡፡ በአንፃሩ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች መስከረም 16 ቀን ምሽት ነው፡፡ ምሽቱ በቤተክርስቲያን የሊጡርጊያ አቆጣጠር መሠረት የመስከረም 17 ቀን የመጀመርያ ክፍል ነውና፡፡
በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እንደሚተረከው፣ መስቀል ከሦስት መቶ ዓመት በላይ ተዳፍኖ ቆይቷል፡፡ በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን (327) የንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እናት ንግሥት ዕሌኒ ይህን ታሪክ ትሰማ ነበርና አስቆፍራ ለማውጣት ጉዞዋን ወደ ኢየሩሳሌም ቀጠለች፡፡ እዚያም ደርሳ ገብታ የሆነውን ሁሉ ብታስቆፍርም መስቀሉ ያለበትን አላገኘችውም፡፡ ሰውም ብትጠይቅ የሚያውቅላት አላገኘችም፡፡ በመጨረሻ ኪሪያኮስ የሚባል የዕሌኒን መቸገር አይቶ እንደሚከተለው ይመክራታል፡፡
‹‹አንችም በከንቱ አትድከሚ ሰውም አታድክሚ እንጨት አሰብስበሽ ከምረሽ ዕጣን አፍስሽበት በእሳትም አያይዥው የዕጣኑ ጢስ ወደ ላይ ወጥቶ ወደ ታች ሲመለስ አቅጣጫውን አይተሽ አስቆፍሪው በዚህ ምልክት ታገኝዋለሽ›› አላት፡፡ እሷም ያላትን ሁሉ አደረገች፡፡ የዕጣኑ ጢስ ወደ ላይ ወጥቶ ወደ ታች ሲመለስ መስቀሉ ያለበትን ቦታ በጣት ጠቅሶ እንደማሳየት ያህል አሳየ ያን ምልክት ይዛ አውጥታዋለች፡፡
በዛንታ እንደሚነገረው፣ የመስቀሉ አንድ ክንፍ (ግማደ መስቀል) ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ በግሸን ዐምባ ይገኛል፡፡ ግማደ መስቀሉ በአፄ ዳዊት ዘመን ከእስክንድርያ (ግብፅ) ሲመጣ ከመጨረሻ ስፍራው መስቀልያ ቅርስ ባለው ግሸን አምባ ከመድረሱ በፊት በሰሜን ኢትዮጵያ ልዩ ልዩ ስፍራዎች ተዘዋውሯል፡፡ በዚህ ዘመን በሃይማኖታዊና ባህላዊ ይዘት ከሚከበርባቸው የዓዲግራቱ ቀንደ ዳዕሮና የመቐለው እንዳ መስቀል (ጮምዓ) አምባዎች እንዲሁም በተጉለት መስቀለ ኢየሱስ ግማደ መስቀሉ ለወራት ተቀምጦባቸው እንደነበር ይወሳል፡፡