Sunday, June 4, 2023

ጦርነቱና ውስጣዊ ችግሮች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

መስከረም 14 ቀን 2015 ዓ.ም. የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው መግለጫ፣ ኦነግ ሸኔ የተባለውን በአሸባሪነት የተፈረጀ ቡድን በወለጋ እያደረሰ ነው ያለውን የሽብር ጥቃት ይዘረዝራል፡፡ ከሰሞኑ በአማራ ክልል የፋኖ አመራሮች ላይ የእስር ዕርምጃ ተወሰደ በሚል በአንዳንድ አካባቢዎች የሕዝብ ተቃውሞዎች ሲከናወኑ ነበሩ፡፡ መስከረም 13 ቀን 2015 ዓ.ም. ደግሞ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ረድኤት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት (UNOCHA) ባወጣው መግለጫ በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች የሚፈናቀሉና ለተረጂነት የሚዳረጉ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን ይገልጻል፡፡

በየዕለቱ አዳዲስ ተጨማሪ ቀውሶች የሚከሰትባት ኢትዮጵያ፣ በሰሜኑ አካባቢ ከባድ ጦርነትም እየተከናወነባት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ጦርነቱ መቼ እንደሚቋጭ በማይታወቅበት በዚህ ወቅት ግን በየአቅጣጫው ያሉ ውስጣዊ ቀውሶች የአገሪቱን ሸክም ሲያከብዱት ይታያል፡፡

በደቡብ ክልል ከማንነትና ከአስተዳደር ጥያቄዎች ጋር በተገናኘ የተቀሰቀሰው የፖለቲካ ትኩሳት አሁን ተዳፍኖ ቢሆን እንጂ ጭራሽን የተቋጨ አይመስልም፡፡ የአፋርና የሶማሌ ክልሎች የወሰን ግጭቶች ቆመው እንደሆን እንጂ ያበቁ አይመስሉም፡፡ የአልሸባብ ጥቃት በምሥራቅ ኢትዮጵያ ቆሞ እንደሆን እንጂ ሥጋቱ ከእነ አካቴው አልተወገደም፡፡

ከእነዚህ ሥጋቶች በተጨማሪ ሰው ሠራሽና ተፈጥሮአዊ ምክንያት ያላቸው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶችም፣ በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች በሰፊው ሥጋት ሆነው ይታያሉ፡፡ ድርቅ፣ የምግብ እጥረት፣ የኑሮ ውድነትና የኢኮኖሚ አለመረጋጋት አገሪቱን ተጭነዋታል፡፡ ይህ ሁሉ ደግሞ ዞሮ ዞሮ አገር በሚመራው መንግሥት ላይ የሚያርፍ ሸክም ነው፡፡

የተለያዩ ውስጣዊ ቀውሶችን ጨምሮ ጦርነቱ እየፈጠረ ላለው ችግር መፍትሔ የማፈላለግ ዋነኛ ኃላፊነት ያለበት መንግሥት፣ በአሁኑ ወቅት ለችግሮቹ ዕልባት ለመስጠት ዘዴና ብልኃቱ ብቻ ሳይሆን አቅምና ፍላጎቱ አለው ወይ የሚለው አሁንም ይነሳል፡፡

‹‹የአሸባሪዎች ጥቃት የኢትዮጵያን ብልፅግና ከማረጋገጥ አያስቆመንም፤›› የሚል መግለጫ ከሰሞኑ ያወጣው መንግሥት በንፁኃን፣ በአካባቢ ሚሊሻዎችና የአስተዳደር አካ ላት ላይ በወለጋ የበቀል ግድያ እየፈጸመ ነው ባለው ኦነግ ሸኔ ላይ በፀጥታ ኃይሎች ጠንካራ ዕርምጃ እየወሰደ መሆኑን ገልጿል፡፡ ከዚህ ቀደምም ዕርምጃ እየተወሰደበት ነው ሲባል የነበረው ኦነግ ሸኔ አሁንም ድረስ የሰላም ሥጋት መሆኑ በአንዳንዶች ዘንድ ጥያቄ ይነሳበታል፡፡

ባለፉት አራት ዓመታት በኦሮሚያ በተለይም በወለጋ ለቀጠለው ቀውስ መፍትሔ ለማፈላለግ የተለየ መንገድ መከተል እንደሚያስፈልግ የሚያሳስቡ አሉ፡፡

የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ዋና ጸሐፊ አቶ ጥሩነህ ገምታ፣ በኦሮሚያ ላለው ቀውስ ብቻ ሳይሆን በመላው ኢትዮጵያ ለተደራረቡ ችግሮች መፍትሔው አስጨናቂ አለመሆኑን ይናገራሉ፡፡

‹‹መፍትሔው ብዙም አያስጨንቅም መወያየት ነው፤›› የሚሉት አቶ ጥሩነህ፣ በጠመንጃ ጥያቄያቸውን ለማስመለስ የሚታገሉ አካላትን አካታች የሆነ ውይይት  እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ፡፡

‹‹የእኔ ህልውና በሌላው መጥፋት ላይ የተመሠረተ ነው ካልተባለ በስተቀር፣ የአንድ አገር ልጆች ምንም በጠላትነት ቢተያዩ ተቀራርበው መወያየት አያቅታቸውም፡፡ ስለጠፋው የሰው ሕይወትም ሆነ ንብረት ዋና ተጠያቂ የሆኑ ግለሰቦችንም ሆነ ድርጅቶችን በሕግ መጠየቅ ይቻላል፡፡ የሚያዋጣ እስከሆነ ድረስ ለአገር ሲባል ይቅር መባባልም ይቻላል፤›› ሲሉም አቶ ጥሩነህ ያክላሉ፡፡

ባለፉት 32 ዓመታት በኢትዮጵያ ብዙ ጥፋቶች ደርሰዋል ያሉት አቶ ጥሩነህ፣ እነዚህን ጥፋቶች ለማረም የተሄደበት መንገድ የጥፋት አዙሪት መፍጠሩን ነው የሚገልጹት፡፡

እነዚህን የተደራረቡ ያሏቸውን ጥፋቶች በአንድ ጊዜ ለመፍታት አገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ተቋማዊና ኢኮኖሚያዊ አቅም አላት ወይ ተብለው የተጠየቁት አቶ ጥሩነህ፣ ግዴታ ጦርነቱ እስኪቋጭ ድረስ መባል እንደሌለበት ነው የጠቀሱት፡፡ ‹‹ገና ለገና አቅም የለንም ተብሎ የአገሪቱን አቅም በሙሉ ጦርነቱ ላይ ከማዋል፣ በየአቅጣጫው ያሉ ቀውሶችን እኩል ትኩረት ሰጥቶ ለመፍታት መሞከር ያዋጣል፤›› በማለት ነው የተናገሩት፡፡

‹‹ታሪካዊ ጠላቶቻችን በተለያዩ ቦታዎች ዓላማቸው ሲሰናከልባቸው በንፁኃን ላይ የሚፈጽሙት የጭካኔ ድርጊት እጅግ አሳዛኝ ነው፤›› በማለት ያስታወቀው ኦነግ ሸኔን የተመለከተው የመንግሥት መግለጫ፣ ለውስጣዊ ቀውሶች አንዱ ምክንያት ታሪካዊ ጠላቶች መሆናቸውን ነው ያመለከተው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ለመስቀል በዓል መልካም ምኞታቸውን ባሠፈሩበት መግለጫም፣ ይህንኑ በሌላ መንገድ አስተጋብተውታል፡፡ ‹‹በአስቸጋሪና በፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ አልፈን እዚህ ደርሰናል፡፡ መንገዳችን ጨለማ፣ እግራችን ቄጤማ እንዲሆን ብዙ ተሠርቶብናል፡፡ ከድጡ ወደ ማጡ እንድንወርድ ያልተፈተለ ሴራ የለም፡፡ እንጀራችንን የበሉ ተረከዛቸውን አንስተውብናል፡፡ ወንዙ እንዲሞላብን፣ ጎርፉ እንዲደርስብን፣ ናዳ እንዲወርድብን ብዙ ተሠርቶ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ አምላክ ግን አሳልፎ አልሰጠንም፤›› ያሉት ዓብይ (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያ የገጠሟትን ፈተና ዘንድሮ የምትሻገርበት ዓመት እንደሚሆን አረጋግጥላችኋለው ሲሉ ቃል ገብተዋል፡፡

መንግሥት በተደጋጋሚ ጊዜ ኢትዮጵያ የገጠማትን ፈተናዎች እንደምትሻገር ቃል ከመግባት ተቆጥቦ አያውቅም፡፡ ይሁን እንጂ ባለፉት አራት ዓመታት ችግሮቹ መላልሰው መከሰታቸውን የታዘቡ ወገኖች፣ መንግሥት ለእነዚህ ችግሮች መፍትሔ ለመስጠት አቅሙ ብቻ ሳይሆን ፍላጎቱስ አለው ወይ? ሲሉ ጭምር ነው የመንግሥትን ፖለቲካዊ ቁርጠኝነትን ጥያቄ ምልክት ውስጥ የሚከቱት፡፡

አገሪቱ ሰፊ ችግር እንዳለባት፣ በሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ ምክንያቶች በየአቅጣጫው ብዙ ቀውሶችን ለመሸከም እንደተገደደች የሚናገሩት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ፓርቲ የሕግ መምርያ ኃላፊ ሙሉዓለም ተገኝ ወርቅ (ዶ/ር)፣ አብዛኞቹ ችግሮችም በመንግሥት ትከሻ ላይ እንደሚወድቁ ያስረዳሉ፡፡

‹‹በታሪክ ውስጥ ካየነው መንግሥት የሚያስፈልገው የዜጎችን ደኅንነት፣ የአገር ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት መጠበቅ ለመሳሰሉ ከፀጥታ ጋር የተያያዙ ሥራዎችን ለማከናወን ነው፡፡ እኛ እንደ ኢዜማ ግን የመንግሥት ሚና ከዚህ የሰፋ መሆን አለበት ነው የምንለው፡፡ አገራችን የምትገኝበት ወቅታዊ ሁኔታ እንደ መደበኛው ጊዜ ሳይሆን ከፍተኛ ውጥረት የሚታይበት ነው፡፡ የአገር አንድነትና ሉዓላዊነት፣ እንዲሁም የዜጎች ደኅንነት በከፍተኛ ደረጃ አደጋ ውስጥ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ መደበኛ የፖለቲካ ሥራ ለመሥራትም የሚያስችል ምኅዳርም በአገሪቱ የለም፤›› ሲሉ ነው ሙሉዓለም (ዶ/ር) የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ የገለጹት፡፡

መደበኛ የፖለቲካ ሁኔታ መፍጠር ከሁሉ የሚቀድም ሥራ መሆኑን የሚጠቅሱት ሙሉዓለም (ዶ/ር)፣ ‹‹ፖለቲካ ለመሥራት የሚያስችል አካባቢያዊ ሁኔታዎችን ከፈጠርን በኋላ ለሥልጣን መፎካከርም ሆነ መቃወም የመሳሰሉ ነገሮችን ማካሄድ ይቻላል፤›› ይላሉ፡፡ ፓርቲያቸውም ሆነ እሳቸው ለአገር ህልውና ገንቢ ሚና መጫወት የሚለውን ጉዳይ እንደሚያምኑበት የሚናገሩት ሙሉዓለም (ዶ/ር)፣ በዚህ የተነሳ ነገሮች ወደ መደበኛ ሁኔታ እስኪመለሱና ለአገር ህልውና ሲሉ አሁን ያለውን መንግሥት መደገፍ የተሻለው ምርጫ ሆኖ እንዳገኙት አስረድተዋል፡፡

የኦፌኮ ዋና ጸሐፊ አቶ ጥሩነህ ገምታ በበኩላቸው በመንግሥት ላይ ተቃውሞ የሚቀርበውም ሆነ ለችግሮች ሰላማዊ መፍትሔ ካልፈለገ የሚል ጫና የሚደረገው፣ አገሪቱ የገባችበትን ችግር ካለመረዳት አለመሆኑን ይናገራሉ፡፡ አቶ ጥሩነህ የአገሪቱ የፖለቲካና የፖለቲካ ልሂቃኑ የጎደላቸው ሆደ ሰፊነት መሆኑን በመጥቀስ፣ አሁን ባለንበት ሁኔታም ቢሆን ችግሮችን በሰላም መፍታት እንደሚቻል ያሰምሩበታል፡፡

‹‹በናይጄሪያ ልክ እንደ እኛ የእርስ በርስ ውጊያና ቁርሾ በነበረ ጊዜ ተፋላሚዎች ጠላት ተባብለው አይፈራረጁም ነበር፡፡ እዚህ እኛ ዘንድ ግን አንዱ ሌላውን በሽብር ይፈርጃል፡፡ የማይታወቅ ስምም ይሰጣል፡፡ ከመፈራረጅ ይልቅ ሥርዓቱን የተቃወሙ ኃይሎች ብሎ መጥራት ይቻላል፡፡ ይህ ዓይነቱ ችግር የሚመነጨው ደግሞ ከመልካም አስተዳደር፣ ከአሳታፊነትና ከዴሞክራሲ ዕጦት ነው፡፡ በሆደ ሰፊነት መነጋገር ቢቻል የገባንበት ቀውስ መፍትሔ ሊገኝለት ይችላል ብዬ አምናለሁ፤›› በማለት ይበጃል የሚሉትን ሐሳብ ያብራሩት፡፡

ከዚህ ቀደም መንግሥትም በተደጋጋሚ እንደሚያነሳው በአገሪቱ ፖለቲካዊ ቀውሶችን የፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት ሰላማዊ ጥረቶች ተሞክረዋል ይባላል፡፡ ኦነግ ሸኔ መንግሥት የሚለውን ወይም የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊትን ትጥቅ ለማስፈታትና ወደ ሰላማዊ የትግል ሜዳ ለማስገባት፣ ሽምግልናና የድርድር ጥረቶች መሞከራቸው ተደጋግሞ ይነገራል፡፡ አባገዳዎች ጉዳዩን በሽምግልናና ዕርቅ እንዲጨርሱት በተደጋጋሚ ወደ ወለጋ ቢላኩም ጥረቱ አለመሳካቱ ይነገራል፡፡ ይህን የሚያጣቅሱ አንዳንድ ወገኖች በኦሮሚያ ክልል ቀውስ እየፈጠረ ያለው የኦነግ ሸኔ ጉዳይ፣ መንግሥት ለሰላም ጥረት ካለማድረጉ ጋር መያያዝ እንደሌለበት ይናገራሉ፡፡

በሌላም በኩል በሰሜን ኢትዮጵያ ዋና የቀውስ ምንጭ ሲሆን ለሚታየው የሕወሓት ጉዳይም ቢሆን፣ መንግሥት በሰላም ለመፍታት በቂ ዕድል መስጠቱን በርካታ ወገኖች ያነሳሉ፡፡ የኑሮ ውድነቱንና የኢኮኖሚ ቀውስን ለመፍታት የሚያስችሉ ፖሊሲዎችንና ዕቅዶን መንግሥት ተግብሯል በሚል ይነሳል፡፡ ድርቅና የተፈጥሮ አደጋዎችን ለመቋቋም መንግሥት ለፍቷል የሚሉት እነዚህ ወገኖች፣ ከዚያ ይልቅ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች የተደራረቡት መንግሥት ዕድለኛ ካለመሆኑ ጋር በተያያዘ ነው  የሚሉም አሉ፡፡

አገሪቱ አሁን የገጠሟት የህልውና ፈተናዎች የመንግሥት ወይም የአንድ ፓርቲ ጉዳይ ብቻ እንዳልሆኑ የሚያስረዱት ሙሉዓለም (ዶ/ር)፣ ኢዜማ በወሳኝ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ከመንግሥት ጎን ሆኖ ለመሥራት የተነሳው የአገሪቱን ሁኔታዎች በጥንቃቄ በመተንተን መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

‹‹አንደኛው ትንተና ከብሔር ፖለቲካ ጋር የተያያዙ ውጥረቶች በአጭር ጊዜ እስካልተገቱ ድረስ የአገሪቱ ችግሮች ይቀረፋሉ ብለን አናምንም፡፡ በአንዴ ይቀረፋሉ ብለን ባናምንም ከብሔር ፖለቲካ ውጥረት በጥንቃቄ ከወጣን ችግሮቹ ቢያንስ ይቃለላሉ፤›› በማለት፣ በአገር ህልውና ላይ የተቃጡ አደጋዎችን የቅድሚያ ቅድሚያ በመስጠት መፍታት እንደሚያስፈልግ ያሳስባሉ፡፡

የኦፌኮ ዋና ጸሐፊ በበኩላቸው መንግሥት በአገሪቱ እየሆነ ላለው ሁሉ ‹‹ዋነኛ ኃላፊነትና ተጠያቂነት›› የተሸከመ ኃይል ነው ይላሉ፡፡ ‹‹ሥልጣንን ከማስቀደም ተላቆ ራስን በማሸነፍ የሐሳብ ልዩነትን በጠላትነት ለመፈራረጅና ለመተላለቅ ከማዋል ወጥቶ ወደ ሰላም መምጣት ይቻላል፤›› ሲሉም ይናገራሉ፡፡ ከኦነግ ሸኔ፣ ከሕወሓትም ሆነ ከሌሎች ለሰላም እንቅፋት ሆነዋል ከሚባሉ ኃይሎች ጋር መንግሥት ቁጭ ብሎ መነጋገር አለበት የሚሉት አቶ ጥሩነህ፣ እሳቸውም ሆኑ ፓርቲያቸው ከሰላማዊ መንገድ ውጪ ሌላ መፍትሔ እንደማይታያቸው ነው የተናገሩት፡፡

መንግሥት በበኩሉ በተደጋጋሚ ጊዜ ለሰላማዊ መፍትሔዎች እጁን መዘርጋቱን ይናገራል፡፡ ይህን የመንግሥትን አቋም የሚደግፉ ወገኖች ትግራይም ሆነ ወለጋ ሽማግሌዎች መላካቸውን ይናገራሉ፡፡

የድርድር አማራጮች መፍትሔ እንደሚሆኑ በመቀበልም ብሔራዊ የድርድር ኮሚቴ መሰየሙን፣ በሌላ በኩልም አገራዊ ቀውሶችን ለመፍታት የሚረዳ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን እንዲቋቋም ማድረጉንም ያስታውሳሉ፡፡ ይሁን እንጂ መንግሥት ከዚህ በላይ የሆነ ርቀት መሄድ አለበት የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡

ከሰሞኑ በአማራ ክልል የፋኖ አመራሮች ላይ ተወሰደ በተባለው እስር ምክንያት የተፈጠሩ ተቃውሞዎችና አለመረጋጋቶች የመንግሥት የተሳሳተ ዕርምጃ የፈጠረው ነው ያሉ በርካቶች ናቸው፡፡ በሽምግልናና በንግግር አለመግባባቱ ይፈታል ተብሎ ሲጠበቅ መንግሥት የፋኖ ሰዎችን ማሰሩ ለአንድ የአማራ ክልል ፖሊስ ባልደረባ ግድያ መንስዔ እንደሆነም ያክላሉ፡፡ ክልሉ ከጦርነት ሳይላቀቅ ተጨማሪ አለመረጋጋት እንዲፈጠርበት ምክንያትም ሆኗል ይላሉ፡፡

ይህን በተወሰነ ደረጃ የሚጋራ አስተያየት የሚሰጡት የኢዜማ የሕግ መምርያ ኃላፊ ሙሉዓለም (ዶ/ር)፣ ‹‹በመንግሥት ውስጥም ቢሆን ከብሔርና ከጎጥ ፖለቲካ ያለ መላቀቅ ችግር አለ፤›› ይላሉ፡፡ በአንድ አገር ውስጥ ኃይል የመጠቀምም ሆነ ትጥቅ አንግቦ የመንቀሳቀስ ሥልጣን ያለው መንግሥት ብቻ መሆኑን አስረድተው፣ ‹‹በአንድ አገር የሚኖሩ ዜጎች እኩል የመዳኘትና እኩል የመታየት ዕድል እስካላገኙ ድረስ ሰላም በቀላሉ ይገኛል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ለዚህ በዋናነት የእኔ ወገን ተጠቃ፣ እገሌ በደለኝ የሚል ልዩነትና የእርስ በርስ ጠላትነት እየፈጠረ ያለው ሥር የሰደደ የዘር ፖለቲካ ዋና የችግር ምንጭ ነው፤›› ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -