Saturday, December 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

መኖሪያ ሸጦ መዞሪያ!

እነሆ ከመካኒሳ ወደ ጀሞ ልንጓዝ ነው። ቀና ሲሉት እየጎበጠ ታጠፈ ሲሉት እየረዘመ መንገድ ጠመዝማዛው ዛሬም ያሸናል። ለአፍታ ባወጋንበት በዚህ ጎዳና ለዘመን በተወዳጀንበት በዚህ መንገድ ከስሜታችን የታለበ ማስረጊያ ዜማ ‘መለያየት ሞት ነው’ የሚለው ብቻ ነው። ትናንትን ዛሬ እየተካው በቀደም በትዝታ ወዲያ ወደኋላ እየጋለበ፣ ነገ የሥጋት ጦሩን ሰብቆ እያስጨነቀ ጊዜ ሲያልፍ ጊዜ ይተካል። መንገድ ሲያልቅ መንገድ ይጀመራል። ‹‹አንተ እባክህ መስኮቱን ዝጋው…›› ትነጫነጫለች የወያላው መከዳ ላይ አንገቷን ያንተራሰች ተሳፋሪ። ‹‹ዕውን መስኮቱ ነው እንዲህ የሚያስጮህሽ? ነገር ነው እንጂ…›› እያለ ወያላው መስኮቱን ይዘጋል። ‹‹ብርድ ብመታ ታሳክመኛለህ?›› ሙግት ጀመረች። ‹‹ብርድ የሚባል ነገር የለም። ምላስ እንጂ ንፋስ ጥሎን አያውቅም ማነሽ?›› ይላል ግንባሩን ቅጭም አድርጎ ሚስጥር አዘል ሥዕል እንደሚያጠና ሆኖ አጠገቧ የተቀመጠ ጎልማሳ። ‹‹ኧረ ሰማይ የሚባልም የለም። ዕድሜ ለህዋ ሳይንስ…›› ይላል መሀል መቀመጫ የተቀመጠ ወጣት፡፡ ወሬ በየዓይነቱ ደርቷል!

 ‹‹ሳይንስ አልከው? ምናለበት የማናውቀውን እያስጨበጡ አልላቀቅ ያልነውን ቢያስጥሉን?›› ይጠይቃል ሦስተኛው ረድፍ ላይ የተቀመጠ ወጣት። ቆያይቶ ደግሞ፣ ‹‹ለነገሩ እነሱ ምን አደረጉ? የአምላክን ሥራ ገለጡ እንጂ ምን አደረጉ? አለን እንጂ መሬት ክብ መሆኗን የሰማን ዕለት እምነትን ያህል ትልቅ ነገር እንደ ኳስ ልንጫወትበት የሚያምረን?›› ቢል፣ ‹‹እንኳን በክብነት አመንን እንጂ ግዴለም ዞረን ዞረን ከመሬት ነን…›› ትለዋለች አጠገቡ የተመቀጠች ወይዘሮ። ‹‹ምኑን ተመለስነው ወደ ሮቦት ዘመን እየገባን?›› ሲላት ክንብንቡን እያስተካከለ፣ ‹‹እህ እሱማ እንግዲህ ከአቅም በላይ ነው። መቼም በዚህ ጉዳይ ተመልካች እንጂ ውሳኔ ሰጪ እንድንሆን አልታደልን…›› ብላው ቅብጥብጥ የሚለውን ወያላ አተኩራ አየችው። የሮቦት ወያላ ታያት ይሆን እንዴ? ምን ይታወቃል እኛም በዓይናችን እናይ ይሆናል እኮ!

‹‹እኔ ምለው ግን?›› ይላል ጎልማሳው ወደ ወይዘሮዋና ወደ ባለክንብንቡ ዘወር ብሎ። ‹‹በተበከለ አየር ልቀት አየር ንብረቱን እንዲህ መፐዋወዛቸው ሳያንስ የሮቦት ማኅበረሰብ የሰው ልጆች መሀል ሊያሰማሩ ሲያስቡ ዝም ብለን ልናይ ነው?›› ከማለቱ አንዱ፣ የዚያን ሰሞን ብርድ በቁርጥማት አላመጠኝ ባይ፣ ‹‹አስበውማ ጨርሰዋል። ይልቅ በጊዜ ደህና ጥሩር ለብሰን መጠበቅ ነው። እንኳን ከሮቦት ጋር ከታክሲ ተጋፍተን እርስ በርሳችንም ወላልቀን አልቀናል…›› ብላ መጨረሻ ወንበር የተቀመጠች የዩኒቨርሲቲ ተማሪ የጨዋታው አባሪ ሆና ብቅ አለች። ‹‹ወይ የእኛ ሰው… አሁን እስኪ የሮቦት ነው የማጣት ታሪካችን ነው የሚቀድመው? በቃ ያልበላንን ዝም ብለን መፎከት?›› አለ በንዴት ከተማሪዋ አጠገብ የተቀመጠ ቸልተኛ መሳይ ወጣት። ‹‹ይቅርታ ‘መፎከት’ ምን ማለት ነው?›› ብላ ተማሪዋ ጥያቄ ስታቀርብ ሳቅ በሳቅ ሆንን። እንሳቀው እንጂ!

ልጁም ነገር ያማረው ነገር ነው መሰል፣ ‹‹ይቅርታ በእንግሊዝኛ የማብራራት አቅም ስለሌለኝ ለቀቅ አድርጊኝ። የዘንድሮ ምሩቃን እንደ ሆናችሁ የባጥ የቆጡን በጉራማይሌ እየቀየጣችሁ የምታደናብሩን ሳያንስ በገዛ ቋንቋችን ‘ሼም’ ልታስይዙን እንዲህ ያለ ጥያቄ ትጠይቃላችሁ?›› ብሎ መዳፉን አማታ። ‹‹ኧረ ተረጋጋ፣ እንዲያውም እሷ እግዜር ይስጣትና አለማወቋን አውቃ ጠይቃለች። ካልክስ አሉልህ በየሚዲያው አገር፣ ወገን፣ ዕድገትና ልማት እያሉ ሲያበቁ በመልካም ቋንቋ አጠቃቀም ችግር የመልካም አስተዳደር ችግራችንን የሚያባብሱት…›› ብሎ አጠገቤ የተቀመጠው ብሶቱን ሲናገር፣ ‹‹ኧረ እባካችሁ እንዳመጣልን አናውራ፡፡ እስኪ ላትጨርሱ ሳይንስን አንስታችሁ ሮቦቶችን አምታችሁ ስለቋንቋ ያነሳችሁት ምኑ ከምኑ ቢያያዝ ነው?›› ብላ የንፋስ ‹ፎቢያ› አለብኝ ያለችው ወጣት ዘው አለች። ይኼኔ ከጎኗ፣ ‹‹በቃ፣ ግራ የገባው እኮ ከዚህም በላይ ይቃብዛል። ለማኗኗርም አኗኗር ሲጠፋን ጨዋታስ ላይጠፋን ነው? እንዴት ነው ነገሩ?›› ብሎ ገላመጣትና አረፈው። የአየር ንብረቱ ብቻ ሳይሆን የንግግርና የወግ ሚዛናችን ጭምር ሳይዛባ አልቀረም መሰል ዘንድሮ፡፡ ኑሮ ከባድ ሚዛን ሆኖ!

ሾፌሩ ሙዚቃ ሊከፍት ማጫወቻውን ይጎረጉራል። ወያላው፣ ‹‹እስኪ ቅድም ያስጫንኳቸውን ዘፈኖች ክፈታቸው…›› ብሎ ‘ፍላሽ’ ያቀብለዋል። ‹‹ካልክስ እስኪ የጥላሁንን ጋብዘንማ ሾፌር…›› ብሎ ጎልማሳው አንገቱን እየወዘወዘ ከንፈሩን መምጠጥ ያዘ። አፍታ ሳይቆይ ደግሞ፣ ‹‹ምን ጥልቅ አድርጎኝ በሰዎች ነገር… ምንስ አግብቶኝ ምንስ ልናገር አለ አፈር ልብላለትና..››”  እያለ ሊቀጥል ሲል፣ ‹‹አያገባንም ብለንማ አገር ስትታመስ ቆመን እያየን ምን ተፈጠረ ልትሉ ነው…›› ብላ ወይዘሮዋ ጉድ አፈላች። ‹‹በሕግ አምላክ፣ መንግሥት ባለበት አገር አገር ታመሰ ብሎ ማውራት ወንጀል ነው የእኔ እመቤት…›› አላት ጎልማሳው ቆጣ ብሎ። ‹‹እህ ታዲያ ዋሸሁ? ዓይተን እንዳላየን ሰምተን እንዳልሰማን መሆናች መሰለኝ ያለ ሙያው፣ ያለ አቅሙና ያለ ችሎታው ትንሽ ትልቁ አናታችን ላይ ቁብ እያለ የተበጠበጥነው። አይደለም እንዴ? በሉ እንጂ አርሙኝ?›› ብላ ተሳፋሪዎችን ቃኘች። ጉድ እኮ ነው!

‹‹ግን ደግሞ ያገባኛል ይመለከተኛል ባይ ተቆርቋሪም ከመደቆስና ከመዳፈን ሌላ በለስ ሲቀናው አላየንም። ስለዚህ አርፈን ልጆቻችን ለማሳደግ የጥላሁንን ዓይነት ዜማ ሳንወድ በግድ እንደግፋለን። አይሞት ታዲያ? የሞተ ተጎዳ…›› ብሎ መጨረሻ ወንበር አካባቢ አንዱ ወጣት ፀጉሩን እየፈተለ አስተያየት ሰጠን። ‹‹ልክ ነው፣ ዕድሜ ለለውጡ መንግሥታችን መሀል ሰፋሪ በሁለት ጥይት ይመታል ብለን አንሥጋ።  ደግሞ ህም…  ከዝም ጭጭ በቀር ሌላ ዕድሜ ማራዘሚያ ዘዴ አለ እንዴ ጎበዝ? ስለዚህ ምን ጥልቅ አድርጎን?›› ብላ ሳትጨርስ ጋቢና የተቀመጠች ጠይም ቆንጆ፣ ‹‹እኮ ሰው በሰው ላይ ሲሠለጥን፣ ሲያሴር፣ ሲገድል፣ ሲሰርቅ፣ ሲያቄም፣ ሲያታልል ዝም? በቃ ይኼ ሆኖ ቀረ አትንኩኝ ባይነት?›› ብለው ከጎኗ ተቀምጠው የነበሩ አዛውንት በትዝብት አዩዋት። ኧረ አንዳንዱንስ እንኳን የትዝብት የአጥፍቶ ጠፊ ዓይንም አላስደነግጠው ብሏል። ምን እንደሚሻል እኮ እንጃ እናንተ!

ከወደ ጋቢና ደግሞ እነሆ ሌላ ጫዋታ ይደመጣል። ከዚህ ቀደም በደንብ የሚተዋወቁ ወዳጅ ቢጤ ናቸው። አንደኛው መምህር ሳይሆን አይቀርም። ‹‹ለመሆኑ አሁንም የምታስተምረው እዚያው ነው ወይስ ቀየሩህ?›› ይጠይቃል የወዲያኛው።  ‹‹ተቀይሬ ሌላ ትምህርት ቤት ተመድቤያለሁ። ምን ቦታ መቀያየር መሠረታዊ ለውጥ ያስከትል ይመስል ባለበት የሚረጋ እኮ ጠፍቷል…›› ይመልሳል መምህሩ። ‹‹ለዚያ ይሆን ሽግሽጉና የዘመኑ መለያ የሆነው?›› ይላል ወደኋላ መቀመጫ አንድ ወጣት። ‹‹በጣም እንጂ፣ ምን እንደሚሻለን ግራ ገብቶናል?›› ከጋቢና ጠያቂው ተናገረ። ‹‹እህል ቢያላምጡት ካልዋጡት ጥቅም የለውም። ሀቁን ተረድተው ካልሠሩበትና ሌሎች እንዲረከቡ ካልታገሉ እውነተኛ ለውጥ ማምጣት እንዴት ይቻላል?›› አለ መምህሩ መቼም መምህር ዘንድ ምሳሌ አይጠፋምና በምሳሌ እያብራራ። ከኋላ መቀመጫ የጋቢናው ጭውውት አንድ ሰበዝ ተመዞ ሌላ መልክ ይዟል። ‹‹ባለፈው ሰሞን የማይቀየር ተጫዋች ቀይረው መስሎን ጉድ የሠሩን? እንዲያው ይኼ ከቦታ ወደ ቦታ መለዋወጥ ምናለበት በጊዜውና በአግባቡ ተፈጻሚነት ቢኖረው?›› ሲል አንደኛው ሌላው ተቀብሎ፣ ‹‹ሰው ሆኖ የማይሳሳት እንጨት ሆኖ የማይጨስ የለም እኮ?›› ይላል፡፡ ‹‹ሰው ሲሠራ ነው የሚሳሳተው። አንዳንዴ ፋታ መስጠትና ዕድል አለመንፈግ ቢለምድብን እንዴት ጥሩ ነበር?›› ትላለች ከሴቶች ወገን። የነገራችን ብዛት መጥኔ ያሰኛል!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። አንድ አዛውንቱ ስልክ እየደዋወሉ ከዘመን ጓኞቻቸው ጋር ለመገናኘት ይወተውታሉ። የአንዱን ዘግተው ወደ አንዱ ሲሞክሩ፣ ‹‹በስተርጅና እስኪ አሁን ‘ቢዚ’ ነን ሲሉ አያፍሩም?  ምን መዓት ነው የመጣብኝ ልጄ? ዕድሜያችንን በቀልድ አሳልፈን ስናበቃ በማረፊያችን ሰዓት ተሰብስበን የጥንት የጠዋቱን በማውጊያችን እንዲህ ለእንጀራ ተጠምደን እንረፈው?›› እያሉ አንዴ ሾፌሩን አንዴ ወጣቷን ያያሉ። ያ ከሾፌሩ ጀርባ ፊቱ የማይፈታው፣ ‹‹ያኔማ ምን አለ አባት? ቫት የለ ታክስ የለ፣ በየወሩ የቤት ኪራይ አይጨምር፣ የእህል ዋጋ ሰማይ አልነካ። ሁሉም ያለውን ተካፍሎ ይኖራል…›› ብሎ ተግ ሲል፣ ‹‹አሁንስ?›› አሉት። የማያውቁትን እንደሚነግራቸው ሁሉ በምፀት እያጤኑት። ‹‹አሁንማ እንኳን የምናካፍለው የምንጎርሰውም በቅጡ አይገኝ። ያዩት የለም እንዴ? ትንሽ መንታፊው ይሻል እንደሆነ እንጂ ሠርቶ አዳሪውስ አልሆነለትም‹‹‹›› ብሎ ፊቱን ከሰከሰው። ምሬት!

‹‹እንዴ ግፉስ እናንተ? የድሮ ሰው እኮ ነው ይኼን ሁሉ ፍዳ ያመጣብን…››  ሲል ከጎኔ ያለው መዓት እንደመጣብኝ ተሸማቅቄ አየሁት። ‹‹የምን ግፍ?›› አለው ጎልማሳው። ‹‹የእህል የውኃው…›› ሳይጨርስ ጎልማሳው አቋርጦ፣ ‹‹ጡር አትልም ታዲያ? በተለያ ጉዳዮች ተሸናሽነን በዓይነ ቁራኛ የምንተያየው አንሶ ደግሞ በዕድሜ ልትለያየን ነው? ስንቱን እንገስጽ እናንተ?›› እያለ ያዙኝ ልቀቁኝ አለ። ‹‹ዝም አትለውም? ቋንጣ በጠጅ ተወራረደ፣ በፍሪዳ ደም በጮማ ስብ ታሪክ ተጻፈ ብሎ አባቶቻችንን ከሚወቅስ ፈጣኑ የኢኮኖሚ ዕድገታችን አምሮታችንን ገደበብን ብሎ አይገላገልም? ማንን ፈርቶ ነው? አህያውን ፈርቶ ዳውላው? ሆ…ሆ…›› ባዩዋ ወይዘሮዋ ናት። አዛውንቱ ግን፣ ‹‹እናንተ በጥቁር ገበያ ዶላር እንደ ዘር ተረጭቶ አዳሜ ቤቱንና መሬቱን እየሸጠ የጋሸበ ብር ሲሰበስብ ዝም ብላችሁ፣ ቤቱን የሸጠ ጉደኛ መኪና ገዝቶ ሲዘውር ምነው ዝም ብላችሁ ስትገርሙ…›› ሲሉ አንዱ፣ ‹‹ፋዘር ስለዞረብን መስሎን መኖሪያችንን ሸጠን መዞሪያችንን እየገዛን በጥሬ ሥጋና በአልኮል እየደለብን ያለነው…›› ሲለን ነበር መንገዳችን አልቆ የተለያየነው፡፡ መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት