ስድስት ቡድኖችን ያሳተፈው የዘንድሮ የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ፣ እሑድ መስከረም 15 ቀን 2015 ዓ.ም፣ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡ ከአንድ ዓመት መቋረጥ በኋላ ጅማሮውን ቀዝቀዝ አድርጎ የጀመረው 16ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ፣ በፈረሰኞቹ ወጣቶች አሸናፊነት መጠናቀቁ፣ ኢትዮጵያ ምን ያህል ዕምቅ የባለ ተሰጥዖ ወጣቶች ምድር ስለመሆኗ ያመላከተ ዓይን ገላጭ አጋጣሚ ሆኖ ስለማለፉ ጭምር እየተነገረ ይገኛል፡፡
አንጋፋው ቅዱስ ጊዮርጊስ (ፈረሰኞቹ) የዓምናው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ መሆኑን ተከትሎ ዋናው ቡድን ለአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ በዝግጅት ላይ ስለነበር፣ በዘንድሮ የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ላይ የቀረበው የወጣት ቡድኑ ነው፡፡
በቀድሞ የክለቡ ተጫዋች ሳምሶን ሙሉጌታ የሚሠለጥነው ወጣት ቡድኑ ለአሸናፊነት የበቃው፣ በግማሽ ፍፃሜው ጨዋታ በኢትዮጵያ ቡና የገጠማቸውን ጠንካራ ፉክክር በመለያ ምት ያገኙትን አጋጣሚ ተጠቅመው ቢሆንም፣ በፍፃሜው ጨዋታ ላይ የገጠሙት መቻል (ቀድሞ መከላከያ) በመደበኛው የጨዋታ ጊዜ 1 ለ 0 በሆነ ውጤት አሸንፈው ነው፡፡ ውጤቱም ቅዱስ ጊዮርጊስ የከተማውን ዋንጫ ዘንድሮ ለሰባተኛ ጊዜ ከፍ እንዲያደርግ አስችሎታል፡፡
ለዘንድሮ የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ቅድመ ግምት አግኝቶ የነበረውና በአሠልጣኝ ተመስገን ዳና የሚሠለጥነው ኢትዮጵያ ቡና፣ ከለገጣፎ ለገዳዲ ጋር ለደረጃ ተጫውቶ እንደ ፍፃሜ ጨዋታው ሁሉ 1 ለ 0 አሸንፎ ውድድሩን ሦስተኛ ሆኖ አጠናቋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫና አሸናፊዎቹ የቅዱስ ጊዮርጊስ ወጣቶች፣ ተምሳሌትነታቸው ለዋናው የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን ብቻ ሳይሆን፣ ለሁሉም ክለቦች ነው፡፡
ጥያቄው ግን ቅዱስ ጊዮርጊስን ጨምሮ ስንቶቹ ክለቦች፣ አሠልጣኞችና ባለሙያዎች የመታየት ዕድሉን ላላገኙ ሌሎችም ባለ ተሰጥዖ ወጣቶች በአገሪቱ መኖራቸውን አምነው ከነባር አስተሳሰባቸው ተላቀው ለምን ያህሉ ዕድል ይሰጧቸዋል? የሚለው ይሆናል፡፡
ሌላው የቅዱስ ጊዮርጊስ ወጣቶች አሸናፊነት ከወትሮው ለየት የሚያደርገው፣ የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ላይ ተሳትፎ ከነበራቸው ቡድኖችና አሠልጣኞች አንፃር ሲታይ እንደሆነ የሚናገሩ አሉ፡፡
ምክንያቱን አስመልክቶ አስተያየት ሰጪዎቹ፣ የቅዱስ ጊዮርጊስ ወጣቶችን የሚያሠለጥነው ሳምሶን ሙሉጌታ፣ ከኢትዮጵያ መድኑ አሠልጣኝ ገብረ መድኅን ኃይሌና ከኢትዮጵያ ቡናው አሠልጣኝ ተመስገን ዳና አንፃር ብዙም ልምድ የሌለው በመሆኑ ነው፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ የዘንድሮውን ጨምሮ በ2002፣ በ2003፣ በ2004፣ በ2006፣ በ2010 እና በ2015 ዓ.ም የተዘጋጀውን የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ለሰባት ጊዜ ከፍ በማድረግ ቀዳሚ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ቡና አራት ጊዜ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሦስት ጊዜ እንዲሁም ኢትዮጵያ ንግድ ባንክና በዘንድሮ ውድድር ያልተሳተፈው ባህር ዳር ከተማ እኩል አንድ አንድ ጊዜ ማንሳት የቻሉ ክለበች ናቸው፡፡
ከአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እንደተገኘው መረጃ ከሆነ፣ የከተማው ዋንጫ በ2000 እና በ2013 ዓ.ም. የውድድር ዘመን አልተካሄደም፡፡
በሌላ በኩል የሁለቱን ቡድኖች ማለትም የኢትዮጵያ ቡናና የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ (ሸገር ደርቢ) ውድድር ላይ የተገኙት ከንቲባ አዳነች አበቤ፣ ከጨዋታው በፊት ውድድሩን አስመልክተው ባደረጉት ንግግር ላይ ከተማ አስተዳደሩ ለሁለቱ ቡድኖች ለእያንዳንዳቸው 10 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ ያደረገ መሆኑ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
ከንቲባ አዳነች የተቀሩት የከተማዋ ክለቦች ማለትም ኢትዮጵያ መድን፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክና መቻል የገንዘብ ድጋፍ ያላደረጉበት ምክንያት፣ ሦስቱ ክለቦቹ የመንግሥት ድጋፍ ይደረግላቸዋል ከሚል መነሻ እንደሆነ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ቢናገሩም፣ ክለቦቹ ግን ለእኛስ ለምን በሚል ቅሬታ አቅርበው እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ጉዳዩ በአብዛኛው የስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ መነጋገሪያ ሆኖም ነበር፡፡
ከቅሬታ አቅራቢዎቹ ክለቦች አንዱ የሆነው የመቻል እግር ኳስ ክለብ፣ የገንዘብ ድጋፉ እንደ ኢትዮጵያ ቡናና ቅዱስ ጊዮርጊስ ሁሉ ‹‹ይገባኛል›› በሚል ቡድኑ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የሚያደርገውን የፍፃሜ ጨዋታ ‹‹አልሳተፍም›› የሚል አቋም ነበረው፡፡ ይሁንና የመቻል እግር ኳስ ክለብ በመጨረሻው ሰዓት በፍፃሜው ለመጫወት ከመስማማቱ በስተቀር፣ ላቀረበው ቅሬታ ያገኘው መልስ ካለ የሚለውን ለማወቅ ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡