Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናኦፌኮ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን ጨምሮ ስምንት አመራሮች እንደታሰሩበት አስታወቀ

ኦፌኮ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን ጨምሮ ስምንት አመራሮች እንደታሰሩበት አስታወቀ

ቀን:

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለክልሉ ደብዳቤ ጽፏል

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ከጳጉሜን 1 ቀን እስከ መስከረም 13 ቀን 2014 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ ሁለት የፓርቲ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን ጨምሮ፣ ስምንት የወረዳና የዞን አመራሮች እንደታሰሩበት አስታወቀ፡፡ ፓርቲው በሐምሌና በነሐሴ ወራትም ሦስት አመራሮች እንደታሰሩበት፣ በአጠቃላይ ሦስት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በእስር ላይ  መሆናቸውን ገልጿል፡፡

ከሐምሌ ጀምሮ በእስር ላይ የሚገኙት 11 ከፍተኛ፣ መካከለኛና ዝቅተኛ አመራሮች በሙሉ ፍርድ ቤት እንዳልቀረቡና ክስ እንዳልተመሠረተባቸው የኦፌኮ ዋና ጸሐፊ አቶ ጥሩነህ ገምታ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ፓርቲው በእስር ላይ የሚገኙ አመራሮችን ጉዳይ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማቅረቡን፣ ምርጫ ቦርድ በበኩሉ ስለእስሩ ማብራሪያ ለማግኘት ለኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ደብዳቤ ጽፎ ምላሽ በመጠባበቅ ላይ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ዋና ጸሐፊው እንደገለጹት፣ ‹‹ሰሞነኛው›› የፓርቲው አመራሮች እስር በተለይ የዞንና የወረዳ አመራሮች ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡ ዋና ጸሐፊው ይህንን ሲያስረዱም፣ ‹‹ሰሞኑን ምን እንደተፈጠረ አናውቅም፣ በተለይ በዞንና በወረዳ የሚገኙ አመራሮቻችንና አባላት በስፋት እየታሰሩ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ፓርቲው ከሰሞኑ እንደታሰሩበት ከጠቀሳቸው መካከለኛና ዝቅተኛ አመራሮቹ ውስጥ አራቱ የሚገኙት ቡኖ በደሌ ዞን መሆኑን፣ አራቱ ግለሰቦች ከጳጉሜን 1 እስከ 3 ቀን  2014 ዓ.ም. ባሉት ተከታታይ ቀናት ለእስር መዳረጋቸውን አቶ ጥሩነህ አስረድተዋል፡፡ አቶ ፈቀደ ኢዶሳ የተባሉት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባልን ጨምሮ አቶ ናስር አባመጋል፣ አቶ መዝገቡ ለገሰና አቶ ተመስገን ለገሰ የተባሉት አመራሮች በዞኑ በደሌ ከተማ ውስጥ በእስር ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

አቶ ጉቶ ዋቆ የተባሉት የፓርቲ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል  ከመስከረም 11 ቀን 2015 ዓ.ም. አንስቶ በአርሲ ዞን መርቲ ወረዳ አቦምሳ ከተማ እንደታሰሩ፣ አቶ ደራሮ ዱቤ የተባሉ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ደግሞ ከነሐሴ 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በሻሸመኔ ከተማ በእስር ላይ እንደሚገኙ ዋና ጸሐፊው ተናግረዋል፡፡

ፓርቲው በባሌ ዞን በሚገኙት ዶሎ መናና መደወላቡ ወረዳዎች ዝቅተኛ አመራር የሆኑት አቶ ሙባረክ ሁሴንና አቶ ካሊድ አብዶ የተባሉ ግለሰቦችም፣ ከመስከረም 7 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ታስረውብኛል ብሏል፡፡ አቶ ጥሩነህ እንደገለጹት፣ በምሥራቅ ወለጋ ዞን የፓርቲው ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ታደሰ ሆርዶፋ የተባሉ ግለሰብ ከጳጉሜን 2 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በወረዳው ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ ታስረዋል፡፡

ፓርቲው በተጨማሪም አቶ አብዲሳ መኮንንና አቶ ግርማ ኃይሉ የተባሉ ዝቅተኛ አመራሮች ከሐምሌ 15 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በኢሉአባቦር ዞን አሌ ወረዳ ጎሬ ከተማ እንደታሰሩበት አስታውቋል፡፡

አቶ ጥሩነህ እንደሚናገሩት፣ በእስር ላይ የሚገኙት የፓርቲው አባላት እስካሁን ፍርድ ቤት አልቀረቡም፡፡ ክስም አልተመሠረተባቸውም፡፡ የፓርቲው አባላት ያለ ክስ ታስረው የመቆየታቸው ጉዳይ የተመለደ መሆኑን የተናገሩት ዋና ጸሐፊው፣ አቶ ወንድሙ አባተ እና አቶ ሀማዶ ሀሚ የተባሉ አመራሮች ለ38 እና ለ67 ቀናት ታስረው ቆይተው ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ መለቀቃቸውም በምሳሌነት አቅርበዋል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት ይካሄዳል የተባለው የአካባቢ ምርጫ ጉዳይ  የፓርቲ አመራሮች ከሰሞኑ በተከታታይ ለመታሰራቸው ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡ ‹‹አሁን ጦርነትና ግጭት በየቦታው ስላለ ይህንን ሽፋን በማድረግ ወደፊት ተፎካካሪ ሊሆኑ ይችላሉ ተብለው የታሰቡን  እያሰሩ ነው፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮሙዩኒኬሽን ዲፓርትመንት ምክትል ኃለፊ አቶ አንዋር አብራር ፓርቲው ስለታሰሩበት አመራሮችና አባላት ጉዳይ አቤቱታ ማቅረቡን ለሪፖርተር አረጋግጠዋል፡፡ ይህንን አቤቱታ ተከትሎም ቦርዱ ስድስት የፓርቲው አመራሮችን ስም ጠቅሶ ለኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ደብዳቤ በመጻፍ ማብራሪያ እንዲሰጠው መጠየቁን አስረድተዋል፡፡

ሪፖርተር የተመለከተው የቦርዱ ደብዳቤ እንደሚያሳየው፣ ምርጫ ቦርድ ኮሚሽኑ ማብራሪያ እንዲሰጠው የጠየቀው እስካለፈው ሳምንት ዓርብ መስከረም 13 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ ነው፡፡

ይሁንና ኮሚሽኑ እስከ ሰኞ መስከረም 16 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ ምላሽ አለመስጠቱን አቶ አንዋር ተናግረዋል፡፡

ሪፖርተር በጉዳዩ ላይ ምላሽ ለማግኘት ወደ ኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን የስልክ ጥሪዎችና የጽሑፍ መልዕክቶች ቢልክም ምላሽ ለማግኘት አልተቻለም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...