Wednesday, December 6, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አዲሱ የኤሌክትሮኒክ የግዥ ሥርዓት በዓመት አምስት ቢሊየን ብር ወጪ ይቀንሳል ተባለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • በአዲሱ አዋጅ መሠረት የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ይተገበራሉ በሳምሶን ብርሃኔ

በተያዘው በጀት ዓመት በ73 ተቋማት እየተተገበረ የሚገኘው የኤሌክትሮኒክ የመንግሥት ግዥ ሥርዓት፣ በዚህ ዓመት ብቻ አምስት ቢሊየን ብር ወጪ ሊቀንስ ይችላል ተብሎ እንደሚጠበቅ የመንግሥት ግዥ ባለሥልጣን አስታወቀ።

በ18 ሚሊየን ብር ወጪ የበለፀገው አዲሱ የግዥ ሥርዓት፣ ባለፈው በጀት ዓመት በዘጠኝ መሥሪያ ቤቶች ላይ በሙከራ ደረጃ ተተግብሮ የነበረ ሲሆን፣ ግዥ ሲከናወን የሚወጡ አላስፈላጊ ወጪዎችን ከመቀነስ ባለፈ፣ ብልሹ አሠራሮችን ለማስቀረት ትልቅ ሚና ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።

ከታኅሳስ 1 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲሱ ሶፍትዌር ላይ ያልተመዘገቡ አቅራቢዎች፣ የፌዴራል መንግሥት ቢሮዎች በግዥዎች መሳተፍ እንደማይችሉ ባለሥልጣኑ አስታውቋል፡፡ ይህንንም ለማከናወን ድጋፍ የሚሰጡ ሠራተኞች በእያንዳንዱ የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች ማሰማራቱን ገልጿል።

ለረዥም ጊዜያት የገንዘብ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር በመሆን ባገለገሉት ሃጂ ኢብሳ ዋና ኃላፊነት የሚመራው የመንግሥት የግዥ ባለሥልጣን፣ ከዚህ ቀደም የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ ኤጀንሲ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ተጠሪነቱም ለገንዘብ ሚኒስቴር ነው።

የኤሌክትሮኒክ የመንግሥት ግዥ ሥርዓትን በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት ሙሉ ለሙሉ መተግበር ከተሰጡት ዋነኛ ኃላፊነቶች መካከል ሲሆን፣ ይህንንም ለማከናወን ባለሥልጣኑ የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት አቋቁሟል።

የፕሮጀክቱ መሪ አቶ ታደሰ ከበደ ቅዳሜ መስከረም 14 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዳማ ከተማ ለጋዜጠኞች በተሰጠ ሥልጠና ወቅት እንደተናገሩት፣ አዲሱ አሠራር በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት ሙሉ ለሙሉ ሲተገበር፣ የግዥ ወጪን በ50 በመቶ ይቀንሰዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

‹‹የአቅራቢዎች ግንዛቤ መጨመርና ስለኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓት ያላቸውን የተንሸዋረረ አመለካከት ለማስተካከል፣ የተለያዩ ሥልጠናዎች እየተሰጡ ነው ያሉት አቶ ታደሰ፣ አዲሱ ሥርዓት በመንግሥት ግዥ ላይ የሚቀርቡ ተጫራቾችን ቁጥር ይጨምራል ብለዋል።

‹‹በመንግሥት ግዥዎች ላይ የሚቀርቡ የተጋኑኑ ዋጋዎች ፉክክር በሚኖርበት ወቅት እየቀነሱ ይመጣሉ፤›› ያሉት አቶ ታደሰ፣ ‹‹በተለይም አዲሱ አሠራር በዓለም አቀፍ ጨረታዎች ላይ የተሻሉ ዋጋዎችን ከማስገኘት አኳያ ትልቅ ሚና ይኖረዋል፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

የኮሪያን ልምድ ያጋሩት አቶ ታደሰ፣ የኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓት በመተግበሩ 30 ሰዓት ይፈጅ የነበረው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የግዥ ሒደት ወደ 30 ደቂቃ ከመቀነስ ባለፈ፣ ከ7.8 ሚሊየን በላይ ወረቀቶችን ማስቀረት መቻሉን ተናግረዋል። በተጨማሪም በዓመት ይወጣ የነበረን አላስፈላጊ የሆነ ከስምንት ቢሊየን ዶላር በላይ ወጪ ማዳን መቻሉን፣ ኢትዮጵያም ተመሳሳይ የሆነ ለውጥ ማምጣት ትችላለች ብለዋል።

እንደ አቶ ታደሰ ገለጻ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ይህን መሰል ሥርዓት እስከ አምስት በመቶ የግዥ ወጪን መቀነስ የሚችል ቢሆንም፣ በአገር ደረጃ ሙሉ ለሙሉ እስከሚተገበር ድረስ ያሉ ሥራዎች ከግምት ውስጥ በማስገባት በአንድ በመቶ ለመቀነስ መታቀዱን ጠቁመዋል፡፡

በየዓመቱ ለፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች ከሚመደበው በጀት ውስጥ 65 በመቶ የሚሆነው ለግዥ የሚውል ሲሆን፣ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዙት ለመንገድና ለሕንፃ ግንባታዎች፣ ለትምህርት ግብዓቶችና ለጤና የሚወጡ ወጪዎች ናቸው። ለ2015 በጀት ዓመት ወደ 786.6 ቢሊየን ብር የተመደበ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ከ511 ቢሊየን ብር በላይ የሚሆነው ለተለያዩ ግዥዎች ይውላል ተብሎ ታቅዷል።

ከተያዘው በጀት ውስጥ አንድ በመቶ የሚሆነው ይቀንሳል ተብሎ የሚጠበቀው አዲሱ ሲስተም ‹‹ቴራጎ ኢንፎርሜሽን ሲስተም›› በተባለ አገር በቀል ድርጅት የለማ ነው፡፡ ሁሉም የመንግሥት ተሿሚ መተግበሩን ማረጋገጥ ግዴታው መሆኑን ባለሥልጣኑ አስታውቋል።

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሃጂ ኢብሳ እንደተናገሩት፣ በቅርቡ በፓርላማ ይፀድቃል ተብሎ በሚጠበቀው አዲሱ የግዥ አዋጅ መሠረት አዲሱን አሠራርም ሆነ ሌሎች የግዥ ሥርዓቶችን በትክክል ያልተገበሩ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች ተጠያቂ እንደሚሆኑ ተቀምጧል።

አዲሱ የኢሌክትሮኒክ የግዥ ሥርዓት በሚተገበርበት ወቅት ከአንዳንድ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች በኩል ያለ መቀበል ችግር ነበር ያሉት አቶ ሃጂ፣ ጉዳዩን ወደ ፓርላማ አልያም ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በመውሰድ የተሰጠውን አነስተኛ ትኩረት ማስተካከል እንደተቻለ ተናግረዋል።

በበጀት ከሚተዳደሩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ባሻገር አዲሱን የግዥ ሥርዓት በመንግሥት ልማት ድርጀቶች ወደ ፊት ይተገበራል ያሉት አቶ ሃጂ፣ ‹‹በተለይም አዲሱ አዋጅ የእነዚህ ተቋማት ግዥ በማዕከል እንዲመራ ስለሚፈቅድ ይህን ማድረግ ያስችለናል፤›› ብለዋል። በተጨማሪ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተዘጋጀው አዲሱ ሲስተም በአማርኛ ቋንቋ እየተዘጋጀ መሆኑን አቶ ሃጂ ገልጸው፣ በሌሎች የኢትዮጵያውያን ቋንቋዎች ተተርጉሞ በክልል ደረጃ እንደሚተገበር ይፋ አድርገዋል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች