የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት በሕገወጥ የገንዘብ ማስተላለፍ ድርጊት ተሰማርተዋል ያላቸው አራት ተቋማትና የውጭ ምንዛሪ በማስቀረት በአገር ውስጥ በብር የሚከፍሉ ሌሎች አካላት፣ ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ በማሳሰብ ሕጋዊ ዕርምጃም እንደሚወስድ አስታወቀ፡፡
የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት ሰኞ መስከረም 16 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ በሕገወጥ ገንዘብ ማስተላለፍ ድርጊት መሰማራታቸውን አረጋግጫለሁ ብሎ የጠቀሳቸው አዶሊስ፣ ሸጌ፣ ሰላምና ሬድ የተባሉ የገንዘብ አዘዋዋሪዎች ናቸው፡፡ በተመሳሳይ ድርጊት የተሰማሩ ሌሎች አካላት እንዳሉም መረጃው አለኝ ብሏል፡፡
ተቀማጭነታቸውን በውጭ አገሮች ያደረጉና በገንዘብ ማስተላለፍ ድርጊት የተሰማሩ አካላት፣ በሕጋዊ መንገድ ውደ ኢትዮጵያ መግባት የነበረበትን የውጭ ምንዛሪ ለኢትዮጵያ ባንኮች የላኩ በማስመሰል፣ የውጭ ምንዛሪ እዚያው ሲያስቀሩ እንደነበር አስታውቋል፡፡
ሐሰተኛ ደረሰኝ ጭምር በማዘጋጀትና በመጠቀም የውጭ ምንዛሪውን በውጭ አገሮች በማስቀረት፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የውጭ አገሮች ገንዘብ ምንዛሪና የኑሮ ውድነት እንዲባባስ በማድረግ ላይ መሆናቸውንም፣ ባገኘው መረጃ ማረጋገጡን ገልጿል፡፡፡
በተለይ በስም የጠቀሳቸው አራቱ ገንዘብ አስተላላፊዎች፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ ግብረ አበሮቻቸው ከሆኑ ከ600 በላይ የሒሳብ ምንጮች፣ በኢትዮጵያ ብር ክፍያ ሲፈጽሙ እንደነበር ደርሼበታሁ ያለው የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት፣ እነዚህ አካላት በሕጋዊ መንገድ መግባት የነበረበት ገንዘብ የኮንትሮባንድ ንግድን ጨምሮ ለተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች መፈጸሚያ እንዲውል አድርገዋልም ብሏቸዋል፡፡
በኢትዮጵያ የፋይናንስ ሥርዓት ላይ ጉዳት በማድረስ ጭምር የፈረጃቸው አገልግሎቱ፣ ሕገወጥ ገንዘብ ማስተላለፍን ጨምሮ መሰል የፋይናንስ ወንጀሎችን የሚፈጽሙ አካላትንም ሆነ ግብረ አበሮቻቸውን በሕግ ተጠያቂ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡