ኢትዮጵያ ችግሮቿን የሚቀርፉ አገር በቀል መፍትሔዎች ላይ ማተኮር ይኖርባታል፡፡ ከዚህ ኢፍትሐዊ ዓለም መፍትሔ ይገኛል ብሎ መጠበቅ የማይቻልበት ጊዜ ላይ እየተደረሰ ነው፡፡ የዓለምን ሚዛን ያስጠብቃሉ የሚባሉ ተቋማት ሚዛናቸውን መጠበቅ አቅቷቸዋል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያጋጥሙ ችግሮችን የመፍታት ኃላፊነት ያለባቸው እንደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ)፣ የአውሮፓ ኅብረትና የመሳሰሉ ተቋማት፣ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት አቅቷቸው የኃያላኖች መጠቀሚያ ሆነዋል፡፡ ፍትሐዊ ሆነው መሥራት ሲገባቸው የጉልበተኞች ጉዳይ አስፈጻሚ ከመሆን የዘለለ ሚና የላቸውም፡፡ በተለይ በኢትዮጵያም ሆነ በሌሎች ታዳጊ አገሮች የሚስተዋሉ ችግሮች በፍትሐዊ መንገድ እንዲፈቱ ከማገዝ ይልቅ፣ ቀውሶችን በማባባስ አገሮች ሰላም እንዳያገኙ የሚሠሩ ነው የሚመስሉት፡፡ ሰላም ለማስፈን የሚረዱ ተግባራትን በማከናወን ፈንታ በእሳት ላይ ቤንዚን የማርከፍከፍ ድርጊቶች ውስጥ በመሰማራታቸው፣ ዓለማችን ለመግለጽ የሚያዳግት አደገኛ ሁኔታ ውስጥ እየገባች ናት፡፡ በኢትዮጵያም ጦርነቱ ተጠናቆ ሰላም እንዲሰፍን ከማገዝ ይልቅ፣ ሰላም አደፍራሽ ነገሮች ላይ በማተኮር ችግሮችን እያባባሱ ነው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያውያን ለአገራቸው መፍትሔ ይፈልጉ፡፡ በማንም መተማመን አያዋጣም፡፡
በኢትዮጵያ ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሦስተኛ ዙር አውዳሚ ጦርነት ተጀምሮ ማቆሚያው መቼ እንደሆነ የሚታወቅ አይመስልም፡፡ በዚህ በተፋፋመ ጦርነት ውስጥ ከተዋጊዎቹ በተጨማሪ ንፁኃን ወገኖች ለዕልቂትና ለመፈናቀል መዳረጋቸው ይታወቃል፡፡ ከዚህ ቀደም በተከናወኑ ሁለት ዙር ጦርነቶች መቶ ሺዎች አልቀው በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ከመፈናቀላቸውም በላይ፣ መጠኑን ለመግለጽ የሚያዳግት የደሃ አገር ሀብት ወድሟል፡፡ በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች ውስጥ የሚካሄደው ጦርነት ሁነኛ ገላጋይ በማጣቱ ሊቆም አልቻለም፡፡ የአገር ህልውና ጉዳይ የሚያሳስባቸው ወገኖች በዚህ ጦርነት ምክንያት በርካታ ጥያቄዎችን ያነሳሉ፡፡ ከጥያቄዎቹ መሀል ቀዳሚው ጦርነቱ መቼ ነው የሚቆመው የሚለው ሲሆን፣ ተከታዩ ጥያቄ ደግሞ ይህንን ጦርነት ለማስቆም ኢትዮጵያውያን ምነው ዝም አሉ የሚለው ነው፡፡ እንደሚታወቀው በኢትዮጵያ ከሚታወቁ በርካታ አኩሪ እሴቶች መካከል አንደኛው ግጭቶችን በሽምግልና መፍታት ነው፡፡ ይህንን የመሰለ ዘመን ተሻጋሪ የሚያኮራ እሴት ባለባት ኢትዮጵያ በርካታ ለሽምግልና የሚበቁ የእምነት መሪዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ታዋቂ ሰዎችና ቅን አሳቢ ዜጎች መኖራቸውም ይታወቃል፡፡ በእጃቸው ላይም አገር በቀል መፍትሔ አለ፡፡
ምንም እንኳ ከዚህ ቀደም በሠለጠነ መንገድ በሕጋዊና በፖለቲካዊ መፍትሔዎች ዕልባት ማግኘት የሚገባቸው ጉዳዮች፣ ከቁጥጥር ውጪ ወጥተው እጅግ አሰቃቂ ለሆነ ደም መፋሰስና ለውድመት ቢያበቁም አሁንም ቆም ብሎ ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ ጦርነት በተራዘመ ቁጥር ዕልቂቱና ውድመቱ ይቀጥላል፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነቱ እንደገና ሲያገረሽ ጋብ ብሎ የነበረው የኦነግ ሸኔ እንቅስቃሴ ሲያንሰራራ፣ አገር ወዴት አቅጣጫ ልታመራ እንደምትችል ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ ትግራይ ውስጥ የመሸገው ሕወሓት ራሱን ከጦረኝነት አባዜ አላቆ ለሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ሲል የሰላም መንገድ መምረጡን በተግባር ያረጋግጥ፡፡ የፌዴራል መንግሥትም በበኩሉ እየተዘጋጀበት የነበረውን የሰላም ሒደት ያጠናክር፡፡ ጦርነቱ መቼ እንደሚደመደም ካልታወቀ ይዞት የሚመጣው ጦስ ከባድ እንደሚሆን መገንዘብ ይገባል፡፡ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጥቅሙን ብቻ እያሰላ ከአንዱ ወገን ጋር እየተሠለፈ፣ ኢፍትሐዊ ውሳኔዎችን ሲያሳልፍና ቀውሱን ሲያባብስ ነው የሚታወቀው፡፡ በግርግር አጋጣሚውን ሊጠቀሙበት የሚፈልጉ ታሪካዊ ጠላቶችም ጦርነቱ ሲራዘም ሠርግና ምላሻቸው ነው፡፡ በዚህ መሀል የሚጎዱት ግን የመፍትሔ ያለህ የሚሉ ኢትዮጵያና ሕዝቧ ብቻ ናቸው፡፡
ለዚህም ነው ምን መደረግ አለበት ማለት የሚገባው፡፡ ጦርነት ተካሂዶ አንዱ ኃይል በሌላኛው ላይ የበላይነት ሲያገኝ፣ ኃይል የከዳው ደግሞ ከበፊት አቋሙ ሸብረክ ብሎ ወደ ሰላማዊ የድርድር ጠረጴዛው ይመጣል፡፡ ይህ ዓይነቱ ሁኔታ የሚፈጠረው ጦርነቱ ባለበት ግለት ከቀጠለ የሚያስከትለው መዘዝ ስለሚታወቅ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ እየሰጠመ ያለ ጀልባ ውስጥ ሆኖ ማዕበሉ ፀጥ ይላል ብሎ መጠበቅ ራስን በራስ ከማጥፋት አይተናነስም፡፡ በተለያዩ ጎራዎች ውስጥ የተሠለፉ ኢትዮጵያውያን በጥቂቶች የፖለቲካ ፍላጎት በተቃኘ አስተሳሰብ ውስጥ ሆነው እርስ በርስ ከሚናጀሱ፣ እውነተኛ ሰላም ሰፍኖ አገር ከገባችበት ቀውስ እንድትወጣና መከራ ውስጥ ያለው ሕዝብም ዕፎይታ እንዲያገኝ ውለታ ይዋሉ፡፡ አሁን የሚስተዋለው አጠቃላይ ሁኔታ በታሪክና በመጪው ትውልድ ጭምር የሚያስጠይቅ መሆኑን ይገንዘቡ፡፡ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ለኩርፊያ እንኳ የማያበቃ ልዩነትን የመጨራረሻ ጦርነት ድረስ ወስዶ ቂምና በቀል ውስጥ መዘፈቅ፣ ከማሳፈር አልፎ መቼም ቢሆን ይቅርታ ለማይደረግለት ፀፀት እንደሚዳርግ መገንዘብ ይገባል፡፡ የሚያዋጣው አገር በቀል መፍትሔ ላይ ማተኮር ነው፡፡
ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ አካባቢ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛ ታዬ አፅቀ ሥላሴ (አምባሳደር) በፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ‹‹…ምግብ ከመለመን በላይ የባሰ ምንም ዓይነት አሰቃቂ ነገር የለም፣ በአሁኑ ጊዜ በጣም ከቸገራቸው ወገኖች አፍ እየነጠቅን ለራባቸው ምግብ እያቀረብን ነው…›› ማለታቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ መነጋገሪያ ርዕስ ነበር፡፡ እውነት ነው በዚህ ዘመን ኢትዮጵያ ከዛሬ ሰላሳ ምናምን ዓመታት በኋላ በጦርነትና በድርቅ ምክንያት ሚሊዮኖች ምግብ ይለመንላቸዋል፡፡ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ ከዚያም በሩሲያና በዩክሬን ጦርነት ሳቢያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በምግብና በነዳጅ ላይ ባጋጠመ ከፍተኛ ጭማሪ ምክንያት ሌሎች የተቸገሩ አገሮችን ለመርዳት ወገቤን እያለ ነው፡፡ በአውሮፓም ሆነ በአሜሪካ መንግሥታቱ የገጠማቸው ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ለዜጎቻቸው ብቻ እንዲያስቡ እያደረጋቸው ነው፡፡ በአገር ውስጥ መንግሥት በጀቱ የማያወላዳ ከመሆኑም በላይ፣ በዜጎች ኑሮ ላይ እየደረሰ ያለው የዋጋ ግሽበት የሚቋቋሙት ዓይነት አይደለም፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ መቼ እንደሚቆም የማይታወቀው አውዳሚ ጦርነት ከፍተኛ ሥጋት ስለደቀነ፣ በጋራ ለመፍትሔ መረባረብ ይገባል፡፡
የአገሬው ሁሉ ትኩረት ጦርነት ላይ ሲሆን ገበያውን እንዳሻቸው የሚዘውሩ ኃይሎችም ሃይ ባይ ያጡ መስለዋል፡፡ አንደኛው በጥቁር ገበያ የውጭ ምንዛሪ ላይ የተሰማሩ ኃይሎች የብርን ዋጋ በየቀኑ እየናዱት ነው፡፡ አንድ ዶላር ከ90 ብር በላይ እየተመነዘረ በባንክ ውስጥ ገንዘብ ያላቸው ሰዎች በመንግሥት ላይ እምነት እንዲያጡ እየተደረገ ነው፡፡ በዚህም ሳቢያ የጥቁር ገበያው ተዋንያንና የመኪና ነጋዴዎች እየተመሳጠሩ በፈጠሩት ሴራ፣ ሰዎች በስሜት እየተነዱ ገንዘባቸውን ከባንክ በማውጣት በአጭር ጊዜ ውስጥ በሚሊዮን ብር ልዩነት መኪኖችን እንዲገዙ እያደረጉ ነው፡፡ የመኖሪያ ቤት ያላቸውን ሰዎች ደግሞ ከቤቱ ወቅታዊ ዋጋ በእጥፍ በማቅረብ ንብረታቸውን እየተረከቡ ነው፡፡ ጥቁር ገበያው ውስጥ የደራው የዶላር ንግድ እንዲህ መረን የተለቀቀው ዶላሩ ከየት እየመጣ ነው ተብሎ ምርመራ ካልተደረገ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ከጦርነቱ ጎን ለጎን ራሱን የቻለ ኢኮኖሚውን በአፍ ጢሙ የመድፋት ሴራ ላለመኖሩ ምንም ማስተማመኛ አይኖርም፡፡ በአጠቃላይ የአገር ጉዳይ አሳሳቢ በመሆኑ መፍትሔ ላይ ይተኮር፡፡ መፍትሔ አልባ ጉዞ የትም አያደርስም!