Sunday, July 21, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ብረት አምራቾች ከመንግሥት ጋር ባለድርሻ ሆነው በማዕድን ፕሮጀክት ላይ ኢንቨስት ለማድረግ እየተነጋገሩ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

 

Keywords:- ዜና፣ የመሠረታዊ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪዎች ማኅበር፣ ኢንቨስትመንት፣ የማዕድን ሚኒስቴር       ለመጀመሪያ ጊዜ በአገሪቱ በሚቋቋመው የብረት ማዕድን ማውጫ ፕሮጀክት ውስጥ ከመንግሥት ጋር ሆኖ መዋዕለ ንዋይ ለማፍሰስ፣ የብረት አምራቾች በንግግር ላይ እንደሆኑ ተገለጸ፡፡

ሰባ ስድስት ያህል ከሚሆኑት የኢትዮጵያ መሠረታዊ ብረት ብረትና ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪዎች ማኅበር አባላት ውስጥ፣ ሃያ የሚሆኑት ከፍተኛ ፍላጎት ማሳየታቸውንና የፕሮጀክት መረጣ በማዕድን ሚኒስቴር ተሠርቶ እስኪጠናቀቅ እየተጠባበቁ መሆናቸው ታውቋል፡፡

‹‹በሐሳቡ ላይ ከመንግሥት ጋር ሆነን እየተነጋገርንበት ነው፡፡ ብዙ ኢንዱስትሪዎች ከመንግሥት ጋር ሆነው ኢንቨስት ለማድረግ ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው፡፡ የብረት ማዕድን ከፍተኛ ገንዘብ፣ መሠረተ ልማትና ፀጥታ ስለሚፈልግ፣ የግሉ ዘርፍ ለብቻው መወጣት አይችልም፡፡ ስለዚህ ሐሳቡ ከመንግሥት በመምጣቱ እጅግ የሚደገፍ ነው፤›› ሲሉ የማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰሎሞን ሙሉጌታ ገልጸዋል፡፡

የማዕድን ሚኒስቴር ከሁለት ሳምንት በፊት ለብረት ማዕድን ማውጫ አዋጭነት ጥናት ለማስጠናት ዓለም አቀፍ ጨረታ ያወጣ ሲሆን፣ በዓመት 2.5 ሚሊዮን ቶን የብረት ማዕድን ማውጣት የሚችሉ የውጭ ኢንቨስተሮች በተናጠልም ሆነ በጋራ መሳተፍ እንደሚችሉ በጨረታ ሰነዱ ተመላክቷል፡፡

ፕሮጀክቱ ከተሳካ የአገር ውስጥ አምራቾች ገንዘብ በማዋጣት ኢንቨስት በማድረግ፣ የተጣራውን ብረት ተቀብለው ወደ ምርት በመቀየር ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሏል፡፡

ፕሮጀክቱ የኢትዮጵያን የብረት ፍላጎት ያሟላል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ በተለይ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ሁለት ከፍተኛ የብረት ማዕድን ፋብሪካዎች ይቋቋማሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በአማራ ክልል ኮምቦልቻ አካባቢ 50 ሚሊዮን ቶን፣ በኦሮሚያ ክልል ቢቂላ በሚባል ሥፍራ 32 ሚሊዮን ቶን ክምችት መኖሩን ከዚህ ቀደም የተሠሩ የጂኦሎጂካል ጥናቶች አመላክተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከ300 ሚሊዮን ቶን በላይ የብረት ማዕድን ያላት ሲሆን፣ ጥራቱ ግን ከቦታ ቦታ ይለያያል፡፡

‹‹ዓመታዊ ፍላጎታችን አሥር ሚሊዮን ቶን ነው፡፡ ይህም ከአምራች ዘርፉ፣ ከግንባታ፣ ከውቶሞቲቭ፣ ከመሠረታዊ ብረታ ብረት፣ ከኤሌክትሮኒክስና ሌሎች የብረት ውጤቶችን አካቶ ነው፤›› ሲሉ የኢትዮጵያ የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ልማት ማዕከል የዕቅድ ክፍል ኃላፊ አቶ ጥላሁን ዓባይ  ገልጸዋል፡፡

ከአምስት ዓመት በፊት ተቋሙ ባደረገው ጥናት መሠረት የብረት ማዕድን ማውጫ ለማቋቋም 15 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈለግ ይፋ አድርጎ ነበር፡፡

‹‹ይህ በአሁኑ ዋጋ እስከ 20 ቢሊዮን ዶላር ሊደርስ ይችላል፡፡ ነገር ግን እንዲህ ዓይነት ትልቅ የማዕድን ማውጫ ፕሮጀክት ላይ ብቻ ከማተኮር ባሻገር መካከለኛና አነስተኛ ማውጫዎች ላይ ኢንቨስት ማድረግ የሚያስችል ጥናትም ሠርተን ለማዕድን ሚኒስቴር ሰጥተናል፤›› ሲሉ  አቶ ጥላሁን አክለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በየዓመቱ አምስት ቢሊዮን ዶላር ያህል ብረትና የብረት ውጤቶችን ከውጭ ለማስገባት የምታውል ሲሆን፣ ይህም ከውጭ ምንዛሪ እጥረት ጋር ተያይዞ በኢኮኖሚው ውስጥ ትልቅ ጫና ማሳደሩ ይታወቃል፡፡ አገር ውስጥ ያሉት የብረት አምራቾች ከአሥር ሚሊዮን ቶን በላይ በዓመት የማምረት አቅም ቢገነቡም፣ በጥሬ ዕቃ እጥረት ምክንያት ከ20 ከመቶ በታች አቅማቸውን እየተጠቀሙ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

በአዲሱ ካቢኔ መዋቅር የብረት ማዕድን ማውጣት ኃላፊነት ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ወጥቶ ወደ ማዕድን ሚኒስቴር ከተዛወረ ወዲህ አበረታች ዕርምጃዎች መወሰዳቸውም ተገልጿል፡፡

የማዕድን ሚኒስቴር በጥቂት ዓመታት ከውጭ የሚገባውን ብረት በአገር ውስጥ ለመተካት ዕቅድ ይፋ ካደረገ ወዲህ፣ በዘርፉ ልምድ ያላቸው የውጭ ድርጅቶችን ለማምጣት ከፍተኛ ጥረት እየተደረ መሆኑ ተገልጿል፡፡ የቻይና፣ የጣሊያንና የደቡብ ኮሪያ ኩባንያዎች ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ውስጥ በብረት ማዕድን ለመሳተፍ ፍላጎት አሳይተው ነበር፡፡

ይሁንና አገር ውስጥ ያለው ጥሬ የብረት ማዕድን ይዞታ (Iron Ore Reserve) አስተማማኝ መሆኑ እስካሁን በጥናት ባለመረጋገጡ፣ ጥሬውን ከውጭ አምጥቶ ኢትዮጵያ ውስጥ ማጣራት እንደ አንድ አማራጭ የሚታይ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች