Friday, June 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ምርት ያላስቆጠሩ የቅባትና የጥራጥሬ እህል ላኪ ድርጅቶች ፈቃድ ሊከለከሉ ነው

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ምርቶችን ለማስቆጠር እስከ ጥቅምት መጀመሪያ ድረስ ገደብ ተቀምጧል

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ለቅባትና ጥራጥሬ ምርቶች ላኪ ድርጅቶች መስከረም 12 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣው ማስታወቂያ፣ ድርጅቶቹ በመጋዘኖቻቸው የሚገኙትን ምርቶች ከመስከረም 13 ቀን 2015 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት 2 ቀን 2015 ዓ.ም እንዲያስቆጥሩ ሲል አሳሰበ፡፡ ምርታቸውን ያላስቆጠሩ ላኪ ድርጅቶች የባለቤትነት ማረጋገጫና የመላኪያ ፈቃድ እንደማያገኙ፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በማስታወቂያው ገልጿል፡፡

በተቀመጡት ተከታታይ 20 ቀናት ቆጠራውን ለማካሄድ ያቀደው ሚኒስቴሩ፣ ምርቶቹን ያከማቹ ላኪዎች ለቆጠራ በሚያመች ሁኔታ በመደርደር እንዲያሳውቁ ሲል ጥሪ አቅርቧል፡፡ በሦስት ቡድኖች በመክፈል የተለያዩ ባለሙያዎችን ለቆጠራው ማሰማራቱን ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡

በመጀመሪያው ቡድን ለመተማ፣ ለጎንደር፣ ለደብረ ማርቆስ፣ ለቡሬና ለባህር ዳር ከተሞች ባለሙያዎችን ያሰማራ ሲሆን፣ በሁለተኛው ቡድን ደግሞ ለአዳማ፣ ለሻሸመኔ፣ ለሐዋሳና ለወላይታ ሶዶ ከተሞች ባለሙያዎችን መድቧል፡፡ ለዓለምገና፣ ለቡራዩ፣ ለለገጣፎ፣ ለገላን፣ ለሰበታና ለአዲስ አበባ ደግሞ ሦስተኛ ምድብ ቡድን አሰማርቷል፡፡

የሚኒስቴሩ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ኃላፊ፣ ይህ ማስታወቂያ የወጣው ባለፈው ዓመት ሳይላኩ የቆዩ ምርቶችን ላከማቹ ላኪዎች መሆኑን፣ ሚኒስቴሩም ከዚህ በፊት እስከ ማሸግ ድረስ የሄዱ ዕርምጃዎችን ይወስድ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

የላኪ ድርጅቶች ተወካዮች ወይም ኃላፊዎች ምርቶቹ የሚገኙበት መጋዘኖች የግለሰብ ከሆኑ የባለቤትነት ማረጋገጫ፣ ተከራይተው ከሆነም የኪራይ ውል ሰነድ ይዘው ለቆጠራው መቅረብ እንዳለባቸው ማሳሰቢያው ያስታውቃል፡፡ በተጠቀሱት ከተሞች የሚገኙ ላኪዎችም ራሳቸው የቆጠራ ቡድን አስተባባሪዎችን በመጥራት፣ ምርት የተከማቸባቸውን መጋዘን አድራሻ በመንገር ማስቆጠር እንዳለባቸው ማስታወቂያው አሳስቧል፡፡

በባለፈው ዓመት በሚያዝያ ወር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ባደረገው ድንገተኛ ማጣራት፣ ከ235 ሺሕ ሜትሪክ ቶን በላይ ወደ ውጭ ገበያ መቅረብ የነበረበት ጥራጥሬና የቅባት እህል በመጋዘኖች ተደብቆ ማግኘቱን መግለጹ የሚታወስ ነው፡፡ ይህም ተከማችቶ የተገኘው እህል በቃሊቲ፣ በገላን፣ በአዳማና በቡራዩ ከተሞች ብቻ እንደነበርም ተገልጾ ነበር፡፡ በገላን ከተማ ተከማችቶ ተገኝቶ የነበረው ትልቁ ሲሆን፣ 57,274 ሜትሪክ ቶን የቅባት እህልና 177,514 ሜትሪክ ቶን የጥራጥሬ እህሎች ነበሩ፡፡ በቡራዩ ከተማም 43,569 ሜትሪክ ቶን የቅባት እህሎችና 116,844 ሜትሪክ ቶን የጥራጥሬ እህሎች ተከማችተው ነበር፡፡

መጋዘኖቹ ከሦስት ወር እሸጋ በኋላ ባለፈው ዓመት በሐምሌ ወር የተከፈቱ ሲሆን፣ በድጋሚ አበጥረው ምርቶቹን እንዲልኩም የምርቶቹ ባለቤት የሆኑት 26 ላኪዎች ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው እንደነበር አይዘነጋም፡፡

‹‹ባለፈው እኛ የደረስንባቸውና የተያዘባቸው ተለቆላቸዋል፡፡ አሁን እነሱም በድጋሚ፣ እኛም ያልደረስንባቸውን ነው አስቆጥረው የመላኪያ ፈቃድ እንዲያገኙ ማሳሰቢያ የወጣባቸው፤›› ሲሉ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ኃላፊ የገለጹት፡፡

ኢትዮጵያ ባለፈው በጀት ዓመት በአጠቃላይ ወደ ውጭ ከላከቻቸው ምርቶች 4.1 ቢሊዮን ዶላር የተገኘ ሲሆን፣ የቡናን 1.4 ቢሊዮን ዶላር ጨምሮ የግብርና ምርቶች 72 በመቶ ነበር የሸፈኑት፡፡ የቅባትና የጥራጥሬ እህሎች የወጪ ንግድ አፈጻጸም ዝቅተኛ ውጤት ያመጣ ሲሆን፣ ከዕቅዱ 69 በመቶ ብቻ ነበር፡፡

የብሔራዊ ባንክ ባፈው ዓመት ባወጣው ከወጪ ንግድ የሚገኝ የውጭ ምንዛሪ ግኝት መመርያ መሠረት መንግሥት 70 በመቶ የሚወስድ ሲሆን፣ ላኪዎችና ባንኮች ደግሞ እያንዳንዳቸው 20 እና 10 በመቶውን የሚካፈሉት እንደሆነ ይደነግጋል፡፡ ላኪዎችም ይህ መመርያ ይሻሻላል በማለት መላክ የነበረባቸውን ምርቶች ያከማቹ እንደነበር፣ ባለፈው ዓመት በሐምሌ ወር የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ደኤታ አቶ ካሳሁን ጎፌ በሰጡት መግለጫ ተናግረው ነበር፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች