የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩ በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ላይ ያተኮረ ታዳሽ ኃይል የ‹‹ትራንስፖርት ትምህርት›› በድኅረ ምረቃ ደረጃ ሊሰጥ መሆኑ ተገለጸ፡፡ ዲፓርትመንቱ ከዚህ ዓመት ጀምሮ ክፍት እንደሚሆን ተገልጿል፡፡
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሯ ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ መስከረም 15 ቀን 2015 ዓ.ም. በዩኒቨርሲቲው በኤሌክትሪክ እንቅስቃሴ ላይ በተደረገ ዓውደ ጥናት ላይ እንደገለጹት፣ በቅርቡ የፀደቀውን የኤሌክትሪክ መኪና አገራዊ ፖሊሲ በመደገፍ የዩኒቨርሲቲው ዕርምጃ ቀዳሚ መሆኑንና ሌሎችም ዩኒቨርሲቲዎች የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲን ፈለግ መከተል እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ኤሌክትሪካልና ኮምፒዩተር ኢንጂነሪንግ ፋኩልቲ ዲን ረዳት ፕሮፌሰር ቴዎድሮስ ጌራ እንደገለጹት፣ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ኮርስን በማስተርስ ደረጃ ለመስጠት የካሪኩለም ቀረፃና ግምገማ መጠናቀቁንና ከዓውደ ጥናቱ የተወሰዱ ግብዓቶች እንደሚካተቱ ገልጸዋል፡፡
በዓውደ ጥናቱ ላይ የማራቶን ሞተርስ ባለቤት ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ፣ የኮረንቲ ሞተርስ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሚካኤል አስረሳኸኝ የኤሌክትሪክ መኪናን በተመለከተ ጥናቶችን አቅርበዋል፡፡
መስከረም 6 ቀን 2015 ዓ.ም. የገንዘብ ሚኒስቴር የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ከተጨማሪ እሴት ታክስ፣ ከኤክሳይስ ታክስና ከሱር ታክስ ነፃ ገብተው እንዲገጣጠሙ የሚፈቅድ መመርያ ማውጣቱ፣ ለዓመታት ሲጠብቁት የነበረና በእጅጉ እንዳበረታታቸው ኢንቨስተሮቹ ገልጸዋል፡፡
ጂአይዜድና ሌሎችም ተቋማት በአዲሱ ትምህርት መሳካት አስተዋጽኦ እንዳደረጉ ተገልጿል፡፡