- ኩባንያው በአራት ዓመት ውስጥ 1.1 ቢሊዮን ዶላር ዕዳውን ከፍሏል
በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነትን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩ የፀጥታ ችግሮች በዓመታዊ ገቢ ላይ ተፅዕኖ አሳድረውበት እንደነበር ያስታወቀው ኢትዮ ቴሌኮም፣ ከግጭት አካባቢዎች የሚታጣውን ገቢ ለመተካት አማራጭ የገቢ ምንጮችን እንደሚያሰፋ ተገለጸ፡፡
ኩባንያው ባለፉት ሦስት ዓመታት ድልድይ (BRIDGE) የተሰኘ ስትራቴጂ ቀርፆ ሲተገብር መቆየቱ የሚታወስ ሲሆን፣ አዲስ ባዘጋጀው የሦስት ዓመት ዕቅድ በተለይም የፀጥታ ችግር ካለባቸው አካባቢዎች፣ እንዲሁም ከተወዳዳሪ የቴሌኮም ኦፕሬተር አገልግሎት አቅራቢ ጋር በተገናኘ የሚታጣ ገቢን ለመተካት አማራጭ የገቢ ማስፊያ ስትራቴጂ ተግባራዊ እንደሚያደርግ ታውቋል፡፡
የአገልግሎት ጊዜው ባበቃው ብሪጅ ስትራቴጂ ኩባንያው በሦስት ዓመታት ውስጥ 202.4 ቢሊዮን ብር ገቢ፣ 532.6 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ገቢ፣ እንዲሁም 86.6 ቢሊዮን ብር ታክስ መክፈሉ ተጠቁሟል፡፡ ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ ከውጭ አበዳሪዎች ለመሠረተ ልማት ማስፋፊያና ግንባታ ከተበደረው ገንዘብ 1.1 ቢሊዮን ዶላር ወይም 67 በመቶ መክፈሉን ኩባንያው አስታውቋል።
ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ ለሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት የሚያገለግለውንና መሪ (LEAD) የተሰኘ አዲስ ስትራቴጂ ቀርፆ ወደ ሥራ መግባቱን ያስታወቀው ኢትዮ ቴሌኮም፣ ዕቅዱን ወደ ተግባር በመቀየር ሒደት ውስጥ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚከሰቱ የፀጥታ ችግሮች የኔትወርክ ማስፋፊያንም ሆነ ነባር አገልግሎቶችን ለማቅረብ እንቅፋት ይሆናሉ የሚለውን ታሳቢ መደረጉን የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ታምሩ ተናግረዋል፡፡
እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ገለጻ፣ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 45 በመቶ የሞባይል ጣቢያዎቹ አገልግሎት ሳይሰጡ ቆይተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ወደ ጣቢያዎቹ 15 በመቶ ዝቅ እንዳሉ፣ በበጀት ዓመቱ ገቢን ከማሳደግ አኳያ ኩባንያው የገቢ ምንጮችን የማስፋት ሥራዎች ይከናወናሉ ብለዋል፡፡
የገቢ ምንጭን ለማስፋት ተግባራዊ ይደረጋሉ ተብለው ከተቀመጡ ሥራዎች አንደኛው እሴት የሚጭምሩ (Value Added) አገልግሎቶች ሲሆኑ፣ ከእነዚህም ውስጥ አዳዲስና የተሻሻሉ የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ አገልግሎቶችን ለገበያ ማቅረብ፣ የቴሌ ብር ተደራሽነትና የአገልግሎት ዓይነቶች እንዲሁም አጋሮችን ማሳደግ ተጠቃሾቹ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
ኩባንያው በመሠረተ ልማት ጉዳት ብቻ ሳይሆን በገበያ ውስጥ የገባው ሌላው ተፎካካሪ የቴሌኮም ኦፕሬተር ገበያውን ስለሚጋራው በዚህ ምክንያት የሚቀንሰውን ገቢ ታሳቢ በማድረግ፣ ኢትዮ ቴሌኮም የገቢ ምንጮቹን ማስፋትና ማሳደግ የተሻለው ምርጫ አድርጎ መውሰዱን ወ/ሪት ፍሬሕይወት አስታውቀዋል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም የገነባውን ዓቅም መሠረት በማድረግ የገቢ ምንጩን ለማስፋት ከአገር ውስጥ በሻገር በጎረቤት አገሮች መሥራት አንዱ ዕቅዱን መሆኑን የተናገሩት ወ/ሪት ፍሬሕይወት፣ ለአብነትም በጂቡቲ ለማከናወን የታቀደው ዕቅድ በሦስት ዓመት ስትራቴጂው ከተያዙ ዕቅዶች ውስጥ እንደሚገኝበትና ወቅቱን ጠብቆ ለሕዝቡ ይፋ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡
በተያዘው በጀት ዓመት የደንበኞችን ቁጥር በአሥር በመቶ አሳድጎ ስምንት ሚሊዮን አዲስ ደንበኞችን በማፍራት የአጠቃላይ ደንበኞቹን ቁጥር 73.5 ሚሊዮን ለማድረስ ያቀደው አንጋፋው ኢትዮ ቴሌኮም፣ ዓምና በውጭ ምንዛሪ ካቀረበው አገልግሎት ያገኘውን 146.6 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ወደ 153 ሚሊዮን ዶላር ለማሳደግ መታቀዱ ታውቋል፡፡ በተጨማሪም በተያዘው የበጀት ዓመት ኩባንያው 75 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ ለማግኘት አቅዷል ተብሏል፡፡
የገቢ አማራጮችን ከማስፋት ባሻገር አላስፈላጊ ወጪዎችን ለማስወገድና ኩባንያውን ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል የወጪ ቁጠባ ስትራቴጂ ቀርፆ ተግባራዊ በማድረግ፣ በበጀት ዓመቱ ከ4.5 እስከ አምስት ቢሊዮን ብር ወጪ ለመቀነስ ዕቅድ መያዙን ኩባንያው አሳውቋል፡፡