በጎንደር አዘዞ የተወለደው ድምጸ ሰረቅራቃው ማዲንጎ ሕይወቱ ማለፉ የተሰማው ዛሬ መስከረም 17 ቀን 2015 ዓም ከሰዓት አካባቢ ነው።
ማዲንጎ አፈወርቅ ወላጆቹ ያወጡለት ስም “ተገኔ” የሚል ቢሆንም፣ ማዲንጎ የሚለውን ስም ያገኘው በደርግ ዘመነ መንግስት ወታደር ቤት ውስጥ እየሰራ እያለ መሆኑንና ከዛ በኃላ መጠሪያው ሆኖ መቀጠሉን የቅርብ ጓደኞቹ ይናገራሉ።
በልጅነቱ የሙዚቃ ፍቅር እንዳደረበት የሚነገረው ማዲንጎ፣ ከደብረ ታቦር ወደ አዘዞ በተመለሰበት ወቅት በሰባተኛ ክፍለ ጦር ካምፕ በ603ኛ ኮር ውስጥ ከነበረ የሙዚቃ ቡድን ጋር ልምምድ እንዲያደርግና ዘፈን እንደሚችል በመግለፅ እድል እንዲሰጠው ጠይቆ እድል ሲሰጠው የኤፍሬም ታምሩን ዘፈን ከተጫወተ በኃላ አድናቆት በማግኘቱ ተቀባይነት አግኝቶ በዛው ሊቀጥል እንደቻለም ይነገራል።
ማዲንጎ ከውትድርና ከወጣ በኃላ በባህር ዳር የሙዚቃ ስራዎችን በማቅረብ ድምፃዊ የመሆን ህልሙን መስመር ያስያዘበትና ገቢ በማግኘት እራሱንና ቤተሰቦቹን ማገዝ የቻለበትን ሁኔታ መፍጠር መቻሉንም የቅርብ ጓደኞቹ ይናገራሉ።
ማዲንጎ ከባህር ዳር ወደ አዲስ አበባ ከመጣ በኃላ በተለያዩ የሙዚቃ ክበቦች የተለያዩ አንጋፋ ድምፃዊያንን ስራዎች ሲያቀርብ የነበረ ሲሆን፣ በኋላም የራሱን ስራዎች (ነጠላና የአልበም ስራዎች) ለአድናቂዎቹ አቅርቧል።
ማዲንጎን በስራዎቹ የሚያውቁት ወዳጆቹ ዜማ የመያዝ ችሎታ፣ ሙዚቃን አሳምሮ በመጫወትና የአድናቂዎቹን ቀልብ በመሳብ የተካነ፣ በማህበራዊ ህይወቱም ተግባቢ፣ ቅንና ተጫዋች እንደነበር ይመሰክሩለታል።
ተወዳጁ ድምፃዊ ማዲንጎ አፈወርቅ ዛሬ ከዚዓለም በድንገት ሕይወቱ ከማለፉ በስተቀር ምክንያቱ እንዳልታወቀና አስከሬኑ ለምርመራ ወደ ሐኪም ቤት መወሰዱ ተሰምቷል።