Sunday, March 3, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

‹‹የተካደው የሰሜን ዕዝ›› የመጽሐፍ ምረቃ ሒደትና ግምገማዊ አስተያየት

በተሾመ ብርሃኑ ከማል

‹‹የተካደው የሰሜን ዕዝ (የታፋኙ ወጥቶ አደር ማስታወሻ)›› በሚል ርዕስ በሃምሳ አለቃ ጋሻዬ ጤናው (ቻቻው) የተዘጋጀው መጽሐፍ ትልቅ ነው፡፡ 391 ገጾች አሉት፡፡ ትልቅነቱ የገጽ ብዛቱ ወይም መጠኑ ትልቅ ስለሆነ አይደለም፡፡ በትልቅነቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ገምጋሚ ሆነው ቀርበውለታል፡፡ አድንቀውለታል፡፡ በመጽሐፉ ምረቃም በዚህ ጽሑፍ ወደፊት እንደምንመለከተው የአገሪቱ ታላላቅ ሰዎች ተገኝተውበታል፡፡ በእርግጥም፣ በኢትዮጵያ ታሪክ አንድም ጠቅላይ ሚኒስትር ወይም ፕሬዚዳንት ወይም በከፍተኛ ደረጃ የሚገኝ ባለሥልጣን የመጽሐፍ ግምገማ ሰጥቶ ስለማያውቅ ከሌሎች የተለየ ያደርገዋል፡፡ ‹‹በተዘዋዋሪ መንገድ ተነክተናል፣ ተሰድበናል ተሽሟጠናል፣ መንግሥታችን ተነክቷል›› እየተባለ ጸሐፊ በታሰረበት፣ ፍዳውን ባየበትና ለግዞት በተዳረገበት አገር የተሰደበ መሪ ገምጋሚ ያውም አዎንታዊ ገምጋሚ ሆኖ ሲቀርብ ይህን አዲስ ክስተት ሚዲያው ለምን ቸል እንዳለው ሊገባኝ አልቻለም፡፡ አዲስ አድማስ ሚያዚያ 1 ቀን 2014 ዓ.ም. ‹‹ጥበብ›› በተሰኘ ዓምዱ በሔኖክ ሥዩም የተጻፈውን ውብ በሆነ መልኩ በአጭሩ ከማውጣቱ በስተቀር ሌላ ሥራ አላየሁም፡፡ ስለሆነም አስተያየቴን በሌላ አቅጣጫ ለመጻፍ ባቅድም በዚህ ጽሑፍ በማቀርበው መንገድ እንድቀጥልበት ሁኔታው አስገደደኝ፡፡

በመሠረቱ፣ መጽሐፉን ካነበብኩት በኋላ የዳሰሳ ጽሐፍ ለማዘጋጀት ስወጥን የደራሲ ጋሻው ጤናው (ቻቻው) የፌስ ቡክ ገጽን ቢያንስ መጽሐፉን ለንባብ ካቀረበበት ጊዜ ጀምሮ ፖስት ያደረገውን በጥንቃቄ ተመልክቻለሁ፡፡ ለጽሑፌ ጠቃሚ ይሆናል ብዬ የማስበውንም ቀድቻለሁ፡፡ መጽሐፉ ደራሲው እንዳለው ብዙ መከራ ዓይቶ ጻፈ፡፡ የመጽሐፉ አስተዋዋቂም ራሱ ሆነ፡፡ ያ ሁሉ በፕሪንት ሚዲያ፣ በኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ፣ በሶሻል ሚዲያ በጦርነት ሲያጋግል የነበረ ወፈ ሰማይ ጸሐፊ ጊዜ ወስዶ አስተያየት አለመስጠቱ ገረመኝ፡፡ እኔም እያንዳንዱን ጸሐፊው የኖረባቸውን፣ የተጓዘባቸውንና ሕዝቡን ስለማውቃቸው ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ያለ መታከት አንብቤዋለሁ፡፡ የሁቱንና የቱትሲን ታሪክ ስለማውቅና ‹‹ሰው ቁስሉ እየተነካካ እንዲያብድ ከተደረገና በተከፈተለት ቦይ ፈሶ ካበደ የሚያደርገውን አያውቅምና ሊሆን ይችላል›› በሚል እንጂ አንዳንዱን አሁንም ቢሆን ማመን ይቸግረኛል፡፡ ሌላውን ለጊዜው ላቆየውና የተከዜን ወንዝ የሚያሻግሩ ባለጀልባዎች፣… እየተራበ የተራበን የሚመግብ፣ እየጠማው ከአፉ ነጥቆ የሚሰጥ፣ እየታመመ የሚያስታምም፣ እየደከመ የሌላ ደካማን የሚሸከም፣ መንገድ ለጠፋበት ጉዞውን አቋርጦም ጭምር የሚያሳይ ሕዝብ ባለበት እንደዚያ ያሉ ጨካኞች መፈጠራቸው በእጅጉ ያስደነግጣል፡፡ ሆነም ቀረ፣ ይህን ጽሑፍ ለመጻፍ በፈለግሁበት መንገድ ሳይሆን ሁኔታው ባስገደደኝ መንገድ ጽፌዋለሁ፡፡ በዚህ መንገድ የቀረበበት ምክንያትም ስለመጽሐፉ መጠነኛም ቢሆን አስተያየት ለመስጠት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መጽሐፉን እንዴት እንደገመገሙት ሌሎች እንዲያውቅ ለማድረግ፣ መጽሐፉ ሲመረቅ ስለነበረው ድባብ ለማሳየት፣ እነማን እንደነበሩ ለመዘከር፣ የመጽሐፉ ውጤት ምን ሊሆን እንደሚችል ለመጠቆም ነው፡፡ በቅድሚያ መጽሐፉን ከዚህ ጽሐፍ አዘጋጅ ዕይታ በቅድሚያ እንየው፡፡

የመጽሐፉ ቅርጽና ይዘት በአጭሩ

መጽሐፉ 10 ምዕራፎችና ከ70 ያላነሱ አርዕስት አሉት፡፡ አጻጸፉ ለንባብ የሚማርክና ተነባቢ ፊደሎች አሉት፡፡ የአርዕስተ ጉዳዩ ብዛትና በቅደም ተከተል መቀመጥ ከአንድ ምዕራፍ ወደ ሌላው ምዕራፍ የሚደረገውን ሽግግር እንዳይሰለች አድርጎታል፡፡ እያንዳንዱ ምዕራፍ በቀኝ ገጽ ላይ ዝቅ ብሎ በማረፉ አንባቢው ቀለል ብሎት እንዲያነብ ረድቶታል፡፡ የመጽሐፉ ዲዛይን በአጠቃላይ መልኩ ሲታይ በጣም ጥሩ ከሚባሉት አንዱ ነው፡፡ የመጽሐፉ ሽፋን ቀለም ሦስት ሲሆን ቅንብሩ በጥንቃቄ መሠራቱን በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡ ሆህያቱም ቢሆኑ ተመርጠው የተቀመጡ  ናቸው፡፡ በመሆኑም እንደ ሀ፣ ሐ፣ ኀ፣ ኸ፣ ሠ፣ ሰ፣ አ፣ ዐ፣ ጸ፣ ፀ፣ ያሉት ፊደላት በሚቻል መንገድ ሁሉ በአግባቡ በጥቅም ላይ ውለዋል ማለት ይቻላል፡፡ ዓረፍተ ነገሮቹ የሰዋስውን ሕግ የተከተሉ ሲሆን የሐሳብ አንድነትና ፍሰት እንዲኖረውም ተደርጓል፡፡ በዚህ ረገድ ጸሐፊው ‹‹ጥሩ አርታኢ አግኝቷል›› ሊያሰኝም ይችላል፡፡

መጽሐፉ የሚያካትተው ከጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. እስከ ኅዳር 28 ቀን 2013 ያለውን የአንድ ወር ከአራት ቀኖችን ታሪክ ሲሆን ታሪኩን የሚከፍተው ‹‹ጥቅምት 24 ቀን 2013 ጁንታው በሰሜን ዕዝ ሠራዊት ላይ በደረቀው ሌሊት ተኩስ ከፈተ፡፡ ያኔ የተጀመረው ተኩስ ወደ ለየለት ጦርነት አድጎ አገራችን በጦርነት ስትናጥ፣ ውዱ የሰው ልጅ ሕይወትም እንደ ቅጠል ረገፈ፡፡ የዚህ ጦርነት ገፈት ቀማሽ ከሆነው የሰሜን ዕዝ ጀምሮ መላው ሠራዊትና ኢትዮጵያውያን ተነግሮ የማያልቅ መከራና ስቃይ ደረሰባቸው›› በሚል የመጀመሪያው የመጽሐፉ መግቢያ አንቀጽ ነው፡፡

በአራተኛው የመግቢያው አንቀጽም ከላይ በተጠቀሰው ቀን ጁንታው ጥቃት መፈጸሙን ይጠቅስና ‹‹ሠራዊቱ ጥቃቱን ለመመከት ያደረገውን ተጋድሎ፣ በጥቃቱ ላይ ሠራዊቱ የደረሰበትን በደል፣ ከጥቃቱ ማግስት የታፈነው ሠራዊት ያሳለፈው ውጣ ውረድ፣ ከጥቃቱ አምልጦ ወደ ጎረቤት አገር የሄደው ሠራዊት ተጋድሎ፣ በመጨረሻም የጁንታው የዓመታት ድንፋታ በሁለት ሳምንት ድባቅ ሲመታ ተበታትኖ የነበረው ሠራዊት እንደገና ተገናኝቶ፣ ፈርሶ የነበሩ ክፍለ ጦሮች ዳግም ሲወለዱ የነበሩ ሁነቶችን ይዳስሳል፤›› ካለ በኋላ መጽሐፉ ከጥቅምት 24 ቀን 2013 እስከ ታኅሣሥ 9 ቀን 2013 ዓ.ም. የነበረውንና ሠራዊቱ የተበተነበትንና ራሱን እንደገና ያደራጀበትን ጊዜ የሚሸፍን እንደሆነ ይገልጻል፡፡

መጽሐፉ ጥቅምት 24 ቀን 2014 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ በተገኙበት የተመረቀ ሲሆን፣ በዕለቱ የወጣው መርሐ ግብር እንደሚያመለክተው የታሪክ ምሁሩና ጸሐፊው መምህር ታዬ ቦጋለ መጽሐፉን  ከሙያቸው አንፃር ሰፋ ያለ የዳሰሳ ጥናት ያቀረቡ ሲሆን፣ ተጓዡ ጋዜጠኛ ሔኖክ ሥዩም በመጽሐፉ ውስጥ የሰሜን ዕዝ ሠራዊት የተጓዘባቸውን አካባቢዎች ከሙያቸው አንፃር አስቃኝተዋል። ከዚህም በተጨማሪ  ወዳጄነህ መሀረነ (ዶ/ር) የሠራዊቱን ሥነ ልቦና በሚመለከት ዳኛቸው አሰፋ (ዶ/ር) ስለመጽሐፉ ያላቸውን አተያይ አቅርበዋል፡፡ ገጣሚዎቹ ኤፍሬም ሥዩም፣ ገጣሚ ትንቢት ምናለ፣ በላይ በቀለ ወያ እና ዳግም ሄራል ግጥሞቻቸውን አቅርበዋል። ብርጋዲየር ጄኔራል ካሳዬ ጨመዳም ከረዥም የውትድርና ዘመናቸው ጨልፈው ስለመጽሐፉ ንግግር ያደርጋሉ። የሁሉንም ገጣሚያን ሥራዎች ማቅረብ ባይቻልም እንኳን ኤፍሬም ሥዩም ካቀረባቸው ግጥሞች አንዱን ቢቀርብ ይበቃል በሚል እምነት በዚህ ጽሐፍ ተካቷል፡፡

ገጣሚ ኤፍሬም ሥዩም ያቀረበው ግጥም ‹‹የዓድዋ ልጅነት ሁነኛው ምልክት›› በሚል ሲሆን ከግጥሙ በፊት ግን ምሥጋና ለደራሲው አቅርቧል፡፡ ምሥጋናውን ሲያቀርብም ‹‹ጋሻየ ጤናው እንኳን ደስ ያለህ ማለት በዚህ መጽሐፍ ከባድ ቃል ይመስላል፡፡ ምክንያቱም የሆነው ነገር ሁሉ ባይሆን ኖሮ የተሻለ በሆነ ነበር፡፡ ነገር ግን ያየኸውን፣ የሰማኸውን፣ የኖርከውን በዚህ በሚሊተሪ ሕይወት ያለውን እንድናነብ፣ እንድናውቅ፣ ስላሉትም ነገሮች እንድናስተውል፣ ካለፉትም እንማር ዘንድ ሁኔታዎች እንድናውቅ ይህን ዕድል ስለሰጠኸን፣ ስለረዳኸን፣ እግዚአብሔር ይስጥልኝ አመሠግናለሁ፤›› ካለ በኋላ ቀደም ሲል የተጠቀሰውን ግጥም በራሱ የጥበብ መንገድ አሰምቷል፡፡

በመጽሐፍ ምረቃው ሥርዓት የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ስለመጽሐፉ የሚከተለውን አስተያይ አቅርበዋል፡፡ (ማስታወሻ፡- ጽሑፉ ቃል በቃል የቀረበ ሲሆን የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ከአንቀጾች አቀማመጥ በስተቀር በዚህ ጽሑፍ ጣልቃ ለመግባት አልሞከረም፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተያየት

‹‹…ያው እንደምታውቁት የተባ ብዕር ያሸንፈኛል፡፡ ለዚህ ነው እዚህ  የተገኘሁት፡፡ ‹የተከዳው የሰሜን ዕዝ› የሚለው የቻቻ የሃምሳ አለቃ ጋሻው መጽሐፍ የግሉ ታሪኩ ብቻ ሳይሆን፣ የብዙዎች፣ የሁላችንም ታሪክ ሆኖ ስላገኘሁት በዚህ ጊዜ ተገኝቼ አምስት ደቂቃ ብናገር ወዳጀም አይከፋውም፡፡ እና ቻቻ እንኳን ደስ ያለህ፡፡ እጅግ በጣም ኮርቼብሃለሁ፡፡ ሃምሳ አለቃ ጋሻዬ ለዚህ ታሪክ በምስክርነት እንዲቆይ የተፈቀደለት ወታደር ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ሆለታ ለመቅረት የሚያስችል ሁኔታ ነበር፡፡ ጊዜውም ወደ ትግራይ ለመሄድ አያመችም፡፡ ያው መጽሐፉ ላይ እንዳለው ብዙ ጓደኞቹም ወደ ኤርትራ ተሻግረው ሄደው ነበር፡፡ እርሱም ያ ዕጣ ሊደርሰው ይችል ነበር፡፡ ይህም ሆኖ ይህን መጽሐፍ እንደገና ጻፈው፣ ድገመው ብንለው፣ ሄሊኮፕተር ብንሰጠውም አይደግመውም፡፡ አይደገምም በሌላ ጊዜ፡፡ በወቅቱ መራራ፣ አስጨናቂ ቢሆንም ማንም ደራሲ ለቀናት በጠላት ሥር ሆኖ ሳይበላ፣ ሳይጠጣ፣ የነገ ተስፋው ምን እንደሆነ ሳያውቅ፣ መጻፍ አይችልም፡፡ መጻፍ ራሱ ማሰብ ስለሚጠይቅ፣ ቻቻው ግን የሚደንቀው በዚያ ውስጥ ሆኖ ማስታወሻ ይይዛል፡፡ በጣም የሚያስደንቀው ብቃቱ እሱ ነው፡፡

እኛ አንተን የምንጋራው ታሪክ፣ በአጋጣሚ ቀደም ብሎ የነበረበትና በኋላ የጠቀሰው በመጀመርያ ከዚህ ወደ ትግራይ ስሄድ የነበረበት አካባቢ፣ ቢያራ ብሎ የጠቀሰው በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት፣ እኔ እዚያ አካባቢ ነበርኩ፡፡ እና ቢያራ ከዚያ አራትና አምስት ኪሎ ሜትር ብትሆን ነው፡፡ ስለፈቃድ፣ ሽራሮ ስለመሄድ፣ ስለግለ ነገሩ ያነሳቸው ነገሮች በሙሉ ወደኋላ መለስ ብዬ እንዳስታውስ ረድቶኛል፡፡ የቻቻውንም ድፍረት ለማድነቅ እፈልጋለሁ፡፡ እኔ ብሆን የሽራሮን ታሪክ መጻፌን እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ሁለተኛው የገረመኝ ነገር ከመጻሕፍት ጋር የተደረገው ግብግብ ነው፡፡ ከአድቡክራይ ወደ ዓዲ አምሓራ ስንሄድ ልክ እንዳንተ በርከት ያሉ መጻሕፍት ነበሩኝና ከመጻሕፍቱ በተጨማሪ ግን በርካታ ጋዜጦች በካርቶን ነበሩኝ፡፡ ከዚህ የሚመጣልኝ ጋዜጣ ነበርና ያንን ጋዜጣ እያነበብኩ ሳስቀምጥ፣ሳስቀምጥ ብዙ ካርቱን ሆነ፡፡ እና በአደራ መጽሐፉን ያስቀመጥኩበት ቤት ‹‹መጽሐፉን እናስቀምጥልሃለን ጋዜጣውን ግን ለግድግዳ መለጠፊያ እናደርገዋለን በዚያ ስምምነት መሠረት መጻሕፍቱን ያስቀመጥኩት፡፡ እና ያንተን መከራ በሚገባ ለማየት ችያለሁ፡፡

ሌላው ባንተ መጽሐፍ ውስጥ በተደጋጋሚ ሐሳብ ጦርነትን መከራን መሸቀጥ፣ በጦርነት፣ በችግር ውስጥ መነገድ፣ በእርግጥ ቻቻው ነጋዴዎቹን ያቀረበውን ያህል እርሱም ነግዷል፡፡ በጽሑፍ እንዳያችሁት በዚያ ጽሑፍ ውስጥ የጀሪካን ውኃ ለማጠጣት በመቶዎች የሚቆጠሩ ብሮችን የሚጠይቁ ሰዎች፣ ከሁሉም በላይ ከትግራይ ክልል ወጥተው አማራ ክልል ውስጥ ከገቡ በኋላ በጀልባ ለመሻገር የነበረው ዋጋ የማስጨመር ግብግብና ነዳጅ አልቋል የመሰለ ቅጥፈት እኔም ትግራይ በነበርኩበት ጊዜ አይቼዋለሁ፡፡ ጦርነቱ ሲነሳ ኤርትራውያን ወንድሞቻችንን ለማባረር የነበረው ፍላጎት፣ ቢኖሩ ጥቃት ያደርሱብናል የሚባሉ ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ ቢሄዱ ቁሳቁስ እናተርፋለን ተብሎ ታስቦ ብዙ እናቶች፣ አሮጊቶች ሲባረሩና ዕቃቸውን ሲከፋፈሉ አይቻለሁ፡፡ በችግር ውስጥ በመከራ ውስጥ መነገድ፣ መሸቀጥ አለ፡፡ ቻቻውም ‹ነግዷል› ያልኩት የቴዲን መተኛ ሰጥቶ ጸሎት የገዛበት መንገድ ሌላ ሽቀጣ ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡ እና ምንም እንኳን ሐሳቡ ቅንነት ያለበት ቢሆንም፣ ጸሎት በላስቲክ አይገዛምና በችግር ጊዜ የሚደረግ ሸቀጣ አድርጌ ነው የወሰድኩት እሱንም፡፡ ከዚህ በተለየ፣ ሰውየው የተለየ አደገኛ ጸሐፊ ነው፡፡ በጣም የተባ፣ የሰላ ብዕር የሚያነሳ፣ እውነትን በሚደንቅ ነገር የሚጽፍ፣ የሚያኮራ ዓይነት ደራሲ ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡ በዓይኑ ያየውን ጠይቆ የሰማውን፣ በሚያስደንቅ ቋንቋ ተርኳል፡፡ ስትጀምሩት ታዩታላችሁ፣ የሚያሳዝን የሚያስለቅስ፣ የሚያስተክዝ በርካታ ቦታዎች በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ እንግዲህ እኔ ያለኝ ሐሳብ ጽሑፉን ያያችሁ ሰዎች በቀላሉ ወደ ስክሪፕት ለመቀየር የሚያስችል ስለሆነ ቆንጆ ፊልም ይወጣዋል ብዬ አስባለሁ፡፡ ፊልም ሠሪዎች እንዳያመልጣችሁ ነው በዚህ አጋጣሚ ለማስታወስ የምፈልገው፡፡

መጽሐፉ የአንድ ሃምሳ አለቃ ተረክ ወይም ያለፈበትን መንገድ፣ የዘገበበትን መንገድ ሳይሆን የሚመስለው፣ ታስቦበት፣ ተወጥኖ፣ ገጸ ባህርይ ተሥሎ፣ ሤራ ተሸክኖ፣ ግጭት ተፈጥሮ፣ የተጻፈ ልቦለድ ነው የሚመስለው፡፡ በዚያ ልክ መነበብ የሚችል ሰነድ ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡ እንግዲህ በዚህ ደረጃ መጽሐፍን መጻፍ የሚችሉ ሰዎች ሲገኙ ከጸሐፊያኑ ይልቅ አንባቢያን ዕድለኞች ናቸው፡፡ ብዙ ጊዜ ታሪክን በዚህ መንገድ አጣፍጦ ማስቀመጥ ያስቸግራልና ከጥቂት ታሪክን አጣፍጠው መጻፍ ከሚችሉት መካከል የሚያሰቀምጠው ጅምር ሥራ ስላየሁ፣ ቻቻው እንኳን ደስ አለህ ለማለት እወዳለሁ፡፡

ሌላው ቻቻው እንድታስብበት የምፈልገው፣ የዓለማችን ዘመን ተሻጋሪ ጸሐፊዎች ስትራቴጂስትስ፣ እጅግ ድንቅ የሆኑ፣ መቶ፣ ሁለት መቶ፣ ሦስት መቶ፣ ከዚያም በላይ የቆዩ ጽሑፎች፣ የወጡት ከወታደር ነው፡፡ የሚገርሙ ጽሑፎችና አሁንም የሠለጠነው ዓለም እየተመለሰ ሪፈር የሚያደርጋቸው፣ ለምሳሌ የአቴንስና የስፓርታ ጦርነት የጻፈው ጄኔራል እስካሁን እንደ ትንግርት የሚታይ ነው፡፡ የሰንዙ ወታደራዊ ስትራቴጂ ብዙዎች የሚጠቀሙበት ነው፡፡ ላው ስሚዝ የተባለው ጀርመናዊ ስለሁለተኛው የዓለም ጦርነት የጻፈው፣ እንዲሁም ‹‹ዘ ባይብል ኦፍ ዎር›› የተባለው በአሁኑ ጊዜም በምዕራቡ ዓለም ሪፈር የሚደረግ ነው፡፡ መርዊን አለ፡፡ ፖሊን ኮል አለ፡፡ የራሱን ባዮግራፊ የጻፈ፣ ሊድል ሀርት አለ፡፡ በጣም በርካታ ጸሐፊያን የወጡት፣ ከወታደር ቤት ነው፡፡ እና ቻቻው ጀምረሃል፡፡ ከዚህ ቀደም ሁለት መጻሕፍት እንዳሉ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ አይቻለሁ፡፡ አላነበብኳቸውም፤ ግን ይህን ጅምር እንደምታሰቀጥል በጣም ትልቅ እምነትና ተስፋ አለኝ፡፡ ትልቅ ብዕር ስላየሁበት፡፡

በዚህ ጽሑፍ ላይ ቻቻው ቅድመ ጦርነቱን፣ ወታደር የተገነባበት፣ የነበረውን ሻጥር፣ የነበረውን ዘረኝነት፣ የነበረውን አድሎ በተወሰነ ደረጃ ለማሳየት ሞክሯል፡፡ ከዚያም ባሻገር የዕገታውን ሒደት፣ እርሱ ያለበትንም፣ ጓደኞቹ ያሉበትንም በጣም መሳጭ በሆነ መንገድ አስቀምጦታል፡፡ ጦርነቱን በሚመለከት በአብዛኛው እርሱ በዕገታ ውስጥ ስለነበር፣ ስለጦርነት ሲያወሳ እኛን በመውቀስ፣ መንግሥትን በመውቀስ ነው ጊዜ የሚያባክነው፡፡ ጦርነቱን እምብዛም አልዘገበውም፡፡ ምክንያቱም ስላልነበረበት፡፡ እኔ ወደፊት ቢታዩ፣ ቻቻውም ሌሎች ጸሓፍትም ቢያዩት ብዬ የማስበው ይህ ጦርነት በጣም  መልከ ብዙ ገጽ አለው፡፡

አንደኛው ‹ሳይኮሎጂያዊ ዋርፌሩ› ነው፡፡ ሳይኮሎጂካል ዋርፌሩ በብዙ ቦታ እንዳስቀመጥከው ቀድሞ ከመሳደብ፣ የኢትዮጵያን ወታደር ዳግም ለማፍረስ ከመፎከር፣ እኛ የማንቻል ነን፣ ጀግንነት ከእኛ ወዲያ የለም ከሚሉ በእብሪት የተሞሉ አሮጋንስ፣ ኅብረተሰቡ ኢንሰኪዩር እንዲሆን የሚያደርጉ ሙከራዎች፣ ቄስም ተኩኖ፣ የካፌቴሪያ አስተናጋጅም ተኩኖ በሁሉም ልክ ያየናቸው በተለይም ደግሞ በቅርብ መሪዎች ሆነው የሠሩት ሥራ፣ ከዚያ ባሻገር በዓለም ላይ የነበሩ ሚዲያዎች፣ በሚችሉት መንገድ ሁሉ ሳይኮሎጂካል የማንችል መሆናችንን ለማሳየት ተግተዋል፡፡ ይህ በጣም መጻፍ ይኖርበታል፡፡ ነገም የሚገጥመን ፈተና ስለሆነ፡፡

ሁለተኛው የጦርነት ግንባሮች፣ ቻቻው የራሱን የመከራ፣ የዕገታ የችግር ጊዜና የጓደኞቹን የውጊያ ሒደት ነው ያነሳው፡፡ ግን በኢኮኖሚው የተደረጉብን አሻጥሮች፣ በኢኮኖሚ የተደረጉብን ጫናዎች፣ የሚያነሳበት ዓውድና የመረጃ እጥረት ሊኖረው ይችላል፡፡ መጻፍ ግን አለበት፡፡ በጣም ከፍተኛ የሆነ ኢኮኖሚያዊ ጫና ለማሳደር ተሞክሯል፡፡ በዲፕሎማሲም ቢሆን ደፋር ዲፕሎማቶች ካሉ እጅግ አስደናቂ የሆኑ ጫናዎችና ያለፍንባቸው ጫናዎች ለትውልድ አስተማሪ በሆነ መንገድ ሊቀመጡ፣ ሊጠቀሱ፣ ሊጻፉ የሚያስችሉ ነጥቦች አሉት፡፡

ሌላው ‹አውት ካሙ› ነው መተንተን ያለበት፡፡ ይኼ ጥሬ ሐቅ ዳታ ተቀምጧል ግን ትንተና ይፈልጋል፡፡ ለምንድነው አርሚው እንደዚያ ማደራጀት ያስፈለገው ለምንድነው በውጊያ ሒደት ውስጥ ጠዋት መብረቃዊ ጥቃት ከሰዓት ተደበደብን የተባለው? ልክ ቻቻው አሁን እንደገረመህ ማለት ነው፡፡ ለምን የሐሳብ ልዩነት ተፈጠረ? በዝግጅት ውስጥ ምን ስህተት ነበር፣ ጠላት አጥብቆ በማወቅ ወታደር ራሱን በሚያውቀው ልክ ጠላቱን ካላወቀ አያሸንፍም፡፡ የብዙ የኢትዮጵያ ችግርም እሱ ነው፡፡ አድቨርሰሪን አስተካክሎ አለማወቅ፣ አድቨርሰሪ በሚዘጋጅበትና በሚጥልበት ልክ አለማወቅና መናቅ ማናናቅ ያን ያህል ጣጣ እንዳለው ተቀምጧል ግን መተንተን አለበት፡፡ ትንተናው በእጅጉ እንደሚጠቅመን ስለሆነ፡፡

እና ዛሬ እንደመጣ ያስገደደኝ ሃምሳ አለቃ እያለሁ የመጻፍ ዕድል ሳይገጥመኝ የቀደመኝን ሃምሳ አለቃን ለማክበር ነው፡፡ ሁለተኛው የመጣሁት ሃምሳ አለቃው ጽሑፍ ጽፎ፣ የጸፈውን ጽሑፍ ለማሳተም ያየውን መከራ ያስቀመጠበት መንገድ መለስ ብዬ ራሴን እንዳይ ስላደረገኝ ነው፡፡ ምክትል የመቶ አለቃ እያለሁ እንዲሁ እኔም ጽፌ ነበርና፣ መከራዬን ዓይቼ ደክሞኝ ተውኩት፡፡ እርሱ ግን ተሳካለት፡፡ እንዴት እንደተሳካለት አላውቅም ሃምሳ አለቃ ሆኖ፡፡ እኔ እንደሱ ለመሆን ደጅ ጠናሁ ግን አልተሳካልኝምና አሁንም አልታገዘም ይሆናል፣ ቢያንስ ማገዝ እንኳን ባንችል ማመስገን ብንችል ብዙዎችን ይቀሰቅስ ይሆናል በሚል ዕሳቤ ነው ዛሬ ለመምጣት ያሰብኩት፡፡

ሌላው ለማንሳት የምወደው ነገር በኢትዮጵያ እስካሁን የተካሄደው ጦርነት በሙሉ ቅድም ኤፍሬም በግጥሙ ያነሳቸውንና ያላነሳቸውም ጭምር ሁሉም ጦርነቶች የሰበብ እንጂ የምክንያት ልዩነት የላቸውም፡፡ የምናሳብበት መንገድ እንጂ ምክንያቶቹ አንድ ናቸው፡፡ የሁሉም፡፡ እኛ አገር ትልቁ ችግር ኢትዮጵያ የውኃ ማማ ናት? ነገር ግን ስለውኃዋ መናገር ስትራቴጂ መቀየስ አይገባትም ብለው የሚያስቡ በርካታ ስትራቴጂስቶች አሉ፡፡ ኢትዮጵያ ለቀይ ባህር መቅረብ ብቻ ሳይሆን ለቀይ ባህር የቀረቡና ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ካላቸው አገሮች ግንባር ቀደም ናት፡፡ ነገር ግን ስለቀይ ባህር አያገባሽም፣ አታስቢ፣ አትናገሪ የሚሉ ኃይሎች ብዙ ናቸው፡፡ እኛን አታስቢ ብለው ከርቀት ደግሞ ስለ ቀይባህር የሚጨነቁ አገሮች አሉ፡፡ በምድርም በሰማይም፡፡ የዘመን አቆጣጠርን የወሰድን እንደሆነ መነሾው ኢትዮጵያ ናት፡፡ ስለዘመን ማሰብ መተንተን ግን አይፈቀድልንም፡፡ ስለከዋክብትም እንደዚሁ ነው፡፡ ከእኛ በፊት ከዋክብትን በስም ለይቶ፣ በግብር ለይቶ፣ የተከተለ አገር የለም፡፡ አባቶቻችን በዚህ ይታወቃሉ፡፡ ስለዚህ፣ ይህን ጉዳይ እንድናነሳ አይፈቀድም፡፡ ባህላዊ መድኃኒትን ብንወስድ ኢትዮጵያ በባህል መድኃኒት በእጅጉ ትታወቃለች፡፡ በፓተንት ስምና ጎጂ ‹‹ሳይዱ›› [ጎኑ] የጎላ ነው በሚል ስም ስለመድኃኒት እንድንናገር አይፈቀድም፡፡ ኢትዮጵያዊ መድኃኒትነቱን አውቆ ቢጠቀምም በውጭ አገር እምብዛም ነው፡፡ የሰው ልጅ መገኛ ነን በዓለም ላይ ግን ከፍ ያለና ዝቅ ያለ ቦታ የያዘች አገር ናት፡፡ የባህር ወለል ከፍ ያለውና ዝቅ ያለው ቦታ ያላት አገር ናት ኢትዮጵያ፡፡ የሃይማኖት መናገሻም ናት ኢትዮጵያ፡፡ ለሺሕ ዓመታት ታላላቅ ሃይማኖቶችን የያዘች፣ ብዙ ድርሳናት ያላት፡፡ የራሷን ቋንቋ ጻፈች፣ በዓለም ላይ ካሉት 20 አገሮች ‹ቱቢ ስፕሲፊክ› 18 አገሮች በራሳቸው ቋንቋ ሲጽፉ ከእነርሱ መካከል አንዷ ናት፡፡ በዚህ ሁሉ ጉዳይ አይመለከታቸሁም፡፡ እናንተ አድማጭ፣ እናንተ ተማሪ፣ እናንተ የእኛን ገድል ተራኪ እንጂ የሚተረክ ገድል የላችሁም ሲሉ ፖርቱጋሎች ሞክረውናል፡፡ ስፔይኖች ሞክረውናል፡፡ እንግሊዞች ሞክረውናል፡፡ ግሪኮች ሞክረውናል፡፡ ጣሊያን ሞክሯል፣ ግብፆች በተደጋጋሚ ሞክረውናል፡፡ ፋርስ ሞክሯል፡፡ ኦቶማን ቱርክ ሞክሯል፡፡ ታላቁ እስክንድርም፣ ታላቁ የሮማው ቄሳርም ሞክሯል፡፡ የሁሉም ሞካሪዎች   ታክቲክ አንድና ያው ነው፡፡ ያው ከውጭ መምታት ከውስጥ መከፋፈል? ከውስጥ ካልከፋፈሉን በስተቀር አንድ ሆነን ስንቆም እኛን መምታት አይቻልም ብለው ስለሚያስቡ የዛሬ ሦስት ወር ገደማ እንኳን ኢትዮጵያውያን አንድ ስለሆኑ አሁን የሚሻለው በሚዲያ በትዊተር በፌስቡክ፣ ከፍተኛ በውጭ ከምንናገር ‹ፐብሊክሊ› በውስጥ እየከፋፈልናቸው የተደበቁ ፍላጎቶቻችንና እናከናውናለን ብለው አገሮች ዕቅድ ይዘዋል፡፡ ግን እነዚህ አገሮች ያልገባቸው አንድ ነገር አለ፡፡ ኢትዮጵያውያን በሰላም ጊዜ ሁሌም ተጨቃጫቂ ነዝናዛዎች ናቸው፡፡ ነገር ግን ከውጭ የተለየ ኃይል የመጣ ቀን ምንም ያህል ያቀደ፣ ያለመም ቢሆን፣ አንድ ሆነው መመከት ታሪካቸው ነውና አድርገውታል፣ ወደፊትም ያደርጉታል፡፡ ይህ ሙከራ አሁንም አለ፡፡

በቻቻው መጽሐፍ ላይ በተለይም በዕገታው ሰሞን፣ የነበረው የመሣሪያ ሽሚያ፣ መሣሪያ ለማግበስበስ፣ የራስን ወታደር ትጥቅ ፍታ፣ ስቶር አስቀምጥ፣ ተኛ? እየተተኮሰ አትዋጋ፣ የሚለው ዕሳቤ መሣሪያን በብዛት ለመቆጣጠር የነበረው ፍላጎት፣ የሞራልና የ‹ማይቲ› ሚና ካለመረዳት ነው፡፡ ‹ዘ ሚስትሪ ኦፍ ሞራል› በማይቲ ውስጥ በሁሉም ውጊያዎች ያለውን ሚና የማያውቁ ሰዎች ትጥቅ ካለ፣ ሚሊሻ ካለን እናሸንፋለን ብለው ያስባሉ፡፡ መከላከያ ሁለት ሞራሎች አሉት፡፡ አንደኛው ሞራል ማርኮም ቢሆን የሚያበላ ነው፡፡ ማርኮም ቢሆን ጡት የማይቆርጥ፣ የሰውን ልጅ እንደሰው የሚያከብርና የማያዋርድ መሆን አለበት፡፡ የዚያ ሞራል ጉድለት ነው ቻቻው በዝርዝር ሊያሳየን የፈለገው፡፡

ሁለተኛው ሞራል ግን የማድረግ መሻት፣ የ‹ኢሞሽን› መነሳሳት ነው፡፡ ሁለቱም እዚያ ቦታ የሉም፡፡ ሁለቱም እዚያ ቦታ እንደሌሉ የሚታወቀው ቻቻው ጥበቃ ዋርዲያ በነበረበት ሰዓት የመጣው አለቃው ትጥቅህን ፍታ፣ ተነስ ማለት ሲገባው አትተኩስና ተቀመጥ ይለዋል፡፡ ወታደር ነው? ጥበቃ እየጠበቀ ነው? ጠላት ቢመጣበት ቢችል ተኩስ እንደሚችል ማሰብ ያልቻለው ኮሎኔል የማድረግ ሞራል አልነበረውም፡፡ ራሱ ግራ በተጋባ መንገድ ነው ሁኔታውን ሲመራ የነበረው፡፡ ያ ባይሆን ኖሮ ቻቻውን ጨምሮ ሁሉንም ጓደኞቹን ሳይቀሩ ማስቀረት የሚያስችል ዕድል ነበረው፡፡ ስለዚህም ሞራል ሁልጊዜ ‹ማይትን ዲፊት› ያደርገዋል የሚባለው ለዚያ ነው፣ እኛ ያሸነፍነው፡፡ ባስቀመጥከው ቁጥር ላይ በርከት ያለ ኃይል፣ በርከት ያው ትጥቅ እዚያ እንዳለ አንተም በደንብ ተርከሃል፣ ግን ትጥቅና ሰው ሳይሆን እውነት፣ ሞራል ያላቸው ኃይሎች ሁሌም አሸናፊዎች ይሆናሉ፡፡ በሞራል ደግሞ ልቆ ለመገኘት የነበረው ሒደት ብዙ የሚያሳየን ይሆናል፡፡ 

በመጨረሻም መልዕክቴ ሁላችንም ለኢትዮጵያ ልዕልና ለኢትዮጵያ ታላቅነት፣ ኢትዮጵያ በአካባቢዋ ብቻ ሳይሆን በዓለም ደረጃ ባላት ታሪክ ልክ የሚያቆም ራዕይና ተግባር ይዘን መቆም ያስፈልጋል፡፡ ብዙ የሚያጨቃጭቁን ነገሮች የሰፈር ናቸው፡፡ ከእነሱ ወጥተን ከፍ ባለ ቦታ ላይ ስለአገር ማሰብ፣ ለአገር መቆጨትና መሥራት ስንችል በዚህ መጽሐፍ ላይ የተቀመጡት በጣም በርካታ ፋክቶች ለትምህርት የሚውሉ ናቸው፡፡

በመጽሐፉ ላይ ቻቻው ችግሮቹን ቁልጭ አድርጎ ነው ያሳያቸው፣ በዘር መከፋፈል፣ ሌላውን ዘር ማንቋሸሽ፣ ሁሌ ራስን አስበልጦ ለማሳየት ሌላውን አሳንሶ ማየት፣ ስለሰው በጥላቻ መናገር፣ ስለእኔ በበርካታ ቦታዎች እኔን ይሳደቡ እንደነበር ቻቻው ጽፏል፡፡ ቻቻው ያልገባው አንድ ምስጢር አለ፡፡ ሰዎች ከሰደቡህ እያከበሩህ ነው፡፡ ከሰደቡህ የሆነ የፈሩት ነገር አለ ማለት ነው፡፡ ‹ኢን ዩር አብሰንስ› ሰው ስላንተ የሚያወራ ከሆነ ‹ሪኮግኒሽን› ነው፡፡ እንደ መናቅ ወይም እንደ አንደርእስቲሜሽን ሳይሆን የፈሩት ያከበሩት ነገር እንዳለ ነው መልዕክቱ የሚናገረው፡፡

ዋናው ነገር ግን ምን እንማር? ትላንት በዘር ላይ የተመሠረተ አርሚ ነበር፡፡ ስለዘር አውርተን፣ ባየኸው ልክ ተባላን፡፡ አሁን ግን እሱ የለም፡፡ የምንገነባው አርሚ እንዴት ተሸጋሪ ይሁን? ኢትዮጵያ ውስጥ አርሚ ሥርዓት ሲያፈርስ፣ መንግሥት ሲያፈርስና ፖለቲካውን በጉልበት ሲያሸንፍ አይተናል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሚሊሻ በወጉ በውትድርና ያልሠለጠነና ቀን የሰጠው ሰው አሸንፎ ወታደሩን ሲበትነው አይተናል፡፡ (አሜሪካ፣ ቻይና ቬትናም) እንደ መንገደኛ ሲበትነው፣ ለማኝ ሲያደርገው አይተናል፡፡ አሁን የገነባነው ወታደር፣ ፖለቲካውን በጉልበት የማይቀማ፣ ፖለቲካውን የማይበትነው አርሚ እንዲኖር ነው፡፡ ግን እንዴት እንሥራው? የሚለው ጉዳይ ለትምህርት የሚተው፣ ለምክክር የሚተው፣ ለንግግር የሚተው ይሆናል፡፡ ብዙ ማሰብ፣ ብዙ መነጋገር ያለብን ይመስለኛል፡፡

ቻቻውን በጣም ለማድነቅ የምፈልገው፣ ሚዛናዊ ለመሆን የሄደበት ርቀት እጅግ አስደማሚ ነው፡፡ ከዚያ አስቀያሚ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ እንኳን፣ መደነቅ የሚገባቸውን እናቶችና አባቶች በየቦታው ለማንሳት ጥረት አድርጓል፡፡ በድፍኑ የትግራይ ሕዝብ በሚል በጥላቻ ሳይሆን፣ የነበረውን ጥሩም ሆነ መጥፎ ጎን፣ በጣም ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ለማስቀመጥ ጥረት አድርጓል፡፡ ይህም ማለት በጽሑፉ ውስጥ ይህን ነገር ባያነሳው፣ ይህን ሲል እንኳን አበላሽቶታል፣ እዚህ ጋ እንኳን ጠይቆ ነው ያለፈው፣ እንደዚያ አልነበረም፣ ታሪኩ ያልኩባቸው ቦታዎች የሉም ማለት አይደለም፡፡ አሉ፡፡ ነገር ግን ሚዛናዊ ለመሆን፣ በዚያ ሁሉ መከራ ውስጥ ሆኖ ያስቀመጠበት መንገድ ትልቅ ብስለትና የኢትዮጵያዊ የሞራል ልቀት የታየበት መጽሐፍ ነው፡፡ ብዙዎቻችን፣ እንደዚያ እንድንሆን ነው ምኞቴ፡፡ ምናልባት በኋላ ባልኖርም፣ ቻቻውን የምጠይቀው ፈጣሪን በዚያ ሁሉ ሒደት ውስጥ መንግሥትን ስታማርር፣ አንዳንድ ጊዜ እኔን እያነሳህ ስታማርር ፈጣሪን ሳታማርር ማለፍህ ገርሞኛል፡፡ ምክንያቱም ብዙ ጊዜ ሲጨንቀን፣ ‹‹አለህ ወይ?›› ብለን የምናንጋጥጠው ወደ ሰማይ ነው፡፡ ለጸሎት ላስቲክ የሰጠህበት መንገድ እንደተጠበቀ ሆኖ እንዴት በዚያ ሁሉ ምሬት ውስጥ አልፎ አልፎም ቢሆን ‹‹ወዴት ነው ያለኸው ብለህ አልጠየቅከውም?›› የሚለውን ጥያቄ ለአንተ እተወዋለሁ፡፡ በመከራ ጊዜ ብዙ ሰዎች እንደዚያ ያደርጋሉ ብዬ ስለማስብ ነው፡፡ የምርቃቱ ታሪክ ደስ ብሎኛል፣ ለቴዲ ያለህ ቦታና ያሰቀመጥከው ነገር ደስ ብሎኛል፡፡ ግን በቴዲና ቻቻው ብቻ ሳይሆን፣ ብዙ ወታደሮች እንደዚያ ናቸው፡፡ የሚተሳሰቡ፣ የሚዋደዱ፣ ከራሳቸው አስበልጠው ወንድማቸውን የሚያስቡ ናቸው፡፡ የመሐመድ ኑርና የማርያም ጉዳይም በጣም ደስ ይላል፡፡ ኢትዮጵያዊ እንደዚያ ስለሆነ፡፡ አንተም ብለኸዋል፡፡ እና በዚህ ሁሉ ውስጥ በርካታ ትምህርት የተቀሰመበት፣ አንተም ለታሪክ ኖረህ ታሪክን ለመዘከር የበቃህበት፣ ቲፒኤልኤፍ ብዙ መከራ ያደረሰብህ ቢሆንም ለእኛ ደግሞ እንደዚህ ያለ የሚጣፍጥ ነገር እንድታተርፍ ያደረገህም ጭምር ስለሆነ እጅህን ቁርጥማት አይንካው፣ ደጋግመህ ጻፍ፣ አትተኛ ልልህ እፈልጋለሁ፡፡ ብዙ ፈተናዎች ከፊታችን አሉ፣ ማስታወሻ እንያዝ ስለምንረሳ፣ በተቻለ መጠን እንጻፍ፣ በተቻለ መጠን እናንብብ፣ በተቻለ መጠን ያነበቡ ሰዎችንም እናመስግን፣ በተቻለ መጠን እንደ ቻቻው ሚዛናዊ ለመሆን እንሞክር፡፡ እኛ የማንችለውንና የማንሠራን ሰዎች ላይ ከመደፍደፍና ከመፍረድ እንቆጠብ፡፡ ቀሪው ጊዜ የሰላም፣ የፍቅርና የደስታ፣ የአንድነት ይሁንላችሁ፡፡ ቻቻው ይህ መጽሐፍ ስላበረከትክልኝ እጅግ አድርጌ አመሰግናለሁ፡፡ ወደ ፊት በግል አገኝሃለሁ፡፡ ሳላገኝህ የመጣሁት እንዳትጠብቀኝ ብዬ ነው፡፡ መልካም ነው፡፡›› የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተያየት መጨረሻ፡፡  

ስለመጽሐፉ ያየኋቸው ውስን የሚዲያ ሽፋኖች

እርግጥ ነው፣ መጽሐፉ በሬዲዮ እንዲነበብ መደረጉም ለመጽሐፉ ከፍተኛ ግምት የተሰጠው መሆኑን ያመለክታል፡፡ አንባቢም ተመርጦለታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ‹‹አሸባሪው ሕወሓት በሰሜን ዕዝ ላይ ያደረሰውን የጭካኔ ድርጊት የሚያትተው ‹የተካደው ሰሜን ዕዝ› መጽሐፍ በትረካ ሊተላለፍ ነው›› በሚል ርዕስ ሰኔ 16 ቀን  2014  ዓ.ም. ባስተላለፈው ዜና ‹‹አሸባሪው ሕወሓት በሰሜን ዕዝ የአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ያደረሰውን የጭካኔ ድርጊትና በሠራዊቱ የተመዘገበውን ድል የሚያትተው ‹የተካደው ሰሜን ዕዝ› መጽሐፍ በትረካ መልክ ማቅረብ እንደሚጀመር አስታውቋል፡፡

‹‹ጥቅምት 24 በዕለተ ማክሰኞ ለዚያውም በውድቅት ሌሊት ሠራዊቱ አገር አማን ብሎ በተኛበት አሸባሪው የሕወሓት ቡድን የአገር ዘብ በሆነው የሰሜን ዕዝ ላይ የጭካኔ በትሩን አሳርፏል።

‹‹ትረፊ ያላት ነፍስ›› እንዲሉ ከጥቃቱ ተርፎ ሁነቱን ለመመስከር የበቃው ሃምሳ አለቃ ጋሻዬ ጤናው (ቻቻው) ‹‹የተካደው ሰሜን ዕዝ›› በሚል ርዕስ የደረሰውን መጽሐፍ ለተደራስያን እንካችሁ ማለቱ ይታወሳል። የተካደው የሰሜን ዕዝ የታፋኙ ወጥቶ አደር ማስታወሻ መጽሐፍም ‹‹የማይካደው›› በሚል መሪ ቃል በአንጋፋው የኪነጥበብ ሰው ደበበ እሸቱ ተተርኮ ለአድማጭ ተመልካቾች እንዲተላለፍ ተሰናድቷል። የመጽሐፉን ትረካ በቀረፃና ቅንብር የሰነደው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) መጽሐፉን ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ተደራሽ ለማድረግ በማሰብ እንዲዘጋጅ አድርጓል። የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሸን (ኢብኮ) የመጽሐፉን ትረካ በቴሌቪዥንና በሬዲዮ ተደራሽ ለማድረግ ኃላፊነት ወስዶ ተረክቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በተጨማሪም የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ጉዳይ አማካሪ ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፣ ኢዜአ መጽሐፉን በትረካ መልክ ማዘጋጀቱ፣ ኢብኮ ደግሞ እንዲተላለፍ ኃላፊነት መውሰዱን አመስግነዋል። የመጽሐፉ መተረክ መጽሐፉን ማግኘት ላልቻሉ ወገኖች እንዲደርስ ዕድል ይፈጥራል ብለዋል። የተካደው ሰሜን ዕዝ ማስታወሻ ደራሲ ሃምሳ አለቃ ጋሻዬ ጤናው፣ መጽሐፉ በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፎ ‹‹የማይካደው-ተካደ›› በሚል መሪ ሐሳብ  ለኅትመት ከዚያም ተሻግሮ ለትረካ መብቃቱ እንዳስደሰተው ገልጿል።

የኢዜአ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ፣ ጠቅላይ ሚነስትር ዓብይ አህመድ፣ የኢዜአ 80ኛ ዓመት ላይ ተገኝተው ለአገርና ሕዝብ የሚጠቅም እውነተኛ መረጃ ማድረስ አለባችሁ በማለት ያስተላለፉትን መልዕክት በመሰነቅ እውነተኛና ጠቃሚ መረጃ ለሕዝብ ለማድረስ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል። ሃምሳ አለቃ ጋሻው ጤናው የደረሰው መጽሐፍም ለሕዝቡ በሚጠቅም፣ የሠራዊቱን ክብር በሚመጥንና በሚያከብር መልኩ ተተርኮ መቅረቡን ተናግረዋል። መጽሐፉ ለኢትዮጵያውያን ትምህርት በሚሆን መልኩ ተቃኝቶ እንዲተላለፍ በማሰብ በትረካ መልክ መዘጋጀቱን ተናግረዋል። የኢብኮ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሥሐ ይታገሱ፣ በሰሜን ዕዝ ላይ የደረሰው የግፍ ጥግ ለኢትዮጵያውያን በሚገባው ልክ ተላልፎ ይሆን የሚለው የዘወትር ጥያቄያቸው እንደነበር ገልጸዋል። መጽሐፉ በተከሰተው ታሪክ ውስጥ ተሳትፎ በነበረውና የግፍ ጽዋውንም በቀመሰው ወታደር የተጻፈ በመሆኑ ሕዝብ እውነታውን በሚገባ እንዲረዳ ያስችላል ብለዋል፡፡

በመሆኑም ትረካው በተቋሙ የሬዲዮና ቴሌቪዥን ማሠራጫዎች ለሕዝቡ እንደሚተላለፍም አረጋግጠዋል፡፡ ‹‹የማይካደው›› የተካደው ሰሜን ዕዝ መጽሐፍ ትረካም በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የሬዲዮና ቴሌቪዥን ማሠራጫ ጣቢያዎች የሚተላለፍ ሲሆን አድማጭ ተመልካቾች ትረካውን እንዲከታተሉ ከወዲሁ ተጋብዘዋል። መጽሐፉ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ተመርቆ ለተደራስያን መቅረቡ ይታወሳል።

የዚህ ጽሑፍ መውጫ

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት አስተያየት ‹‹ይህም ማለት በጽሑፉ ውስጥ ይህን ነገር ባያነሳው፣ ይህን ሲል እንኳን አበላሽቶታል፣ እዚህ ጋ እንኳን ጠይቆ ነው ያለፈው፣ እንደዚያ አልበረም ታሪኩ፣ ያልኩባቸው ቦታዎች የሉም ማለት አይደለም አሉ፡፡›› እንዳሉት፣ ለወደፊቱ ትውልድ ሲባል እልክን፣ ሐዘንን፣ መከራን ዋጥ አድርጎ መታለፍ የነበረባቸው ሐሳቦች ነበሩ፡፡ ከእነዚህም መካከል ለአብነት ያህል ብቻ ከገጽ 376-377 ያለውን እንመልከት፡፡ በገጽ 376 ‹‹ከከተማዋ መሀል ያለውን የማርያም አደባባይ ስንደርስ ሦስት ወጣቶች መንገድ ሲያቋርጡ አንደኛው ሲያቅለበልበው ‹‹እንኳን ደህና መጣችሁ›› አለ፡፡ ሁሉም ጭንቅላቱን በመስኮት እያወጣ ‹‹ምን አልክ አንተ ጁንታ? መርቀህ የሸኘኸን መሰለህ? መጥተንልሃል… ያደረግህብንን እጥፍ አድርገን እንመልስልሃለን… እንደ ሄዱ ይቀራሉ ብለህ ነበር? መጥተናል…›› ሁሉም ወረደበት፡፡ ልጁ ደንግጦ ከአስፓልቱ በዚህ ገባ ሳንለው ተሰወረ፤›› ይላል፡፡ በገጽ 377 ደግሞ ‹‹ከመቀሌ ማውጫ የተወሰኑ ሴቶች ነጠላቸውን ለብሰው ተሰባስበዋል፡፡ አስፓልቱ ላይ ብዙም ሰው ስላላየን የእነሱ መሰባሰብ አስደነገጠን፡፡ መኪኖቹን ሲያዩ እየወጡ ጥግ ያዙ፡፡ አቤት እንዴት እንዳዩን! ፍርሃትና ጥላቻ የተቀላቀለበት አስተያየት፡፡ ፍርሃትና ጥላቻ ያለበት ሰው ፊት ምንድነው የሚመስለው?

‹‹ምን ሆናችሁ ነው?›› ስንላቸው ‹‹ዕርዳታ ልንቀበል›› አሉ፡፡ አንዱ ጓድ ‹‹ጎሽ እናንተ የሚያምርባችሁ እኮ ተሰልፋችሁ ዕርዳታ ስትወስዱ ነው፡፡ ስትለምኑ ነው የሚያምርባችሁ፡፡ እንኳን ደስ ያላችሁ፡፡ የሚያምርባችሁን ነገር አገኛችሁ፡፡›› አለና መኪናው ውስጥ ያለውን ሁሉ አሳቀን በማለት ይገልጻል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹‹ባያነሳው›› ያሉት ይህን ይሆን? ሊሆንም ላይሆንም ይችላል፡፡ 

መጽሐፉ ቅጽ አንድ ስለሆነ ቅጽ ሁለት እንጠብቃለን፡፡ ስለነበረው ሁኔታ በራሱ መንገድ ስላሳወቀን ግን እናመሰግናለን፡፡

እንዲህ ያለው የእርስ በርስ መጠፋፋት ይቀር ዘንድ አገራችንን ሰላም ያድርግልን፡፡ የእልከኝነት መጥፎ መንፈስ ያርቅልን፡፡ ተራርቀናልና፣ ወደ መቀራረብና መገናኛት የሚወስድ ድልድይ ፈጣሪ ይሥራልን፡፡ መልካም አዲስ ዓመት፡፡

     ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው አንጋፋ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ የእስልምና ጉዳዮች ተመራማሪ፣ እንዲሁም የታሪክ አጥኚ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው bktesheat@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles