በ938 እስከ 995 ይኖር የነበረው አብዱልቃሲም ኢስማኤል አስገራሚ ቤተ መጻሕፍት ነበረው። ነገሩ ቤተ መጻሕፍት ይባል እንጂ፣ መጻሕፍቱ ግን በቤት ውስጥ የነበሩ አይደሉም። ጀርባ ላይ ተጭነው በሥርዓት በግመል የተደረደሩ ስለሆኑ ምናልባት በነጮች ‹‹ሞባይል ላይብረሪ›› ወይም ተዘዋዋሪ ቤተ መጻሕፍት የሚሉትን ዓይነት መጠሪያ ቢሰጠው አይከፋም።
ታዲያ የፐርሺያ ዕውቅ ባለሥልጣን የነበረው ይኸው አብዱልቃሲም 117 ሺሕ መጻሕፍት በፊደላት የቅደም ተከተል ሥርዓት በ400 ግመሎች ላይ አስጭኖ አስደርድሮ በተለያዩ ሥፍራዎች ይዘዋወር ነበር። በጥንት ጊዜ በቤተ መጻሕፍት ሠራተኞች ላይ መጥፎ ግምት ነበር። ይኸውም በዚህ ሙያ ላይ የተሰማሩት ሠራተኞች ፈጽሞ ያልተማሩና ያልሠለጠኑ ተደርገው የሚቆጠሩበት የተሳሳተ ግምት ነው።
ይህንኑ ሁኔታ ኤድዋርድ ያንግ በጽሑፉ ሲገልፅ ‹‹ስልቦች ሴቶችን ሳይነኩ እንደሚጠብቁ ሁሉ ማንበብ የማይችሉ ሰዎችም መጻሕፍትን በጥንቃቄ ይይዛሉ›› ብሎ ነበር። ይህን አባባል እውነት ነው ለማለት እንደማያስደፍር ማስረጃ አያሻም። ይሁንና በምድራችን ላይ አያሌ ዕውቅ ደራሲያን፣ የብዕርና የፖለቲካ ሰዎች መሀል የቤተ መጻሕፍት ሠራተኛ የነበሩ መጥቀስ ይቻላል። ጂኤድጋር ሁቨር፣ ማኦ ሴ ቱንግ፣ ፖፕ ፒየስ 11ኛ እንዲሁም ከደራስያን መሀል ጎትፍሬድ ቮን ሌብኒዝ፣ ዳቪድ ሂዩም፣ ኦገስት ስትሪንበርግና አርቺባልድ ማክሊሽ በቤተ መጻሕፍት ይሠሩ የነበሩ ሰዎች ናቸው።
– ንጉሤ አየለና ደጀኔ ጥላሁን ‹‹ጣዝማ አስደናቂው የደራስያን ሕይወት›› (2014)- ክብሩቡክስ