ምዕራባውያን አገሮች በኢትዮጵያ ላይ ጠንካራ ጫና ማሳደራቸውን ቀጥለዋል፡፡ በዲፕሎማሲም ሆነ በፖለቲካ ረገድ ከኃይል መለስ (ማለትም ከወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ውጪ) ያሉ አቅሞቻቸውን ተጠቅመው፣ ኢትዮጵያን በተፅዕኗቸው ሥር ለማድረግ ጫናቸውን መቀጠላቸው ይታያል፡፡ በትግራይ ክልል ጦርነት በተቀሰቀሰ ማግሥት የጀመረው የምዕራባውያኑ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳዮች ጣልቃ ለመግባት መሞከርና ጫና የማሳደር እንቅስቃሴ፣ እስከ የት ድረስ እንደሚቀጥል ከመገመት ውጪ ማንም በእርግጠኝነት አያውቅም፡፡
የምዕራባውያኑን ጫናና ጣልቃ ገብነት በዋናነት እየጋበዘ ያለው የእነሱ ፍላጎት ብቻ አለመሆኑም ተደጋግሞ ይነገራል፡፡ የሕወሓት ኃይሎች አሳሳች የመረጃ ሥርጭት እንዲሁም የማሳመንና የማግባባት (Lobby) ብቃት በኢትዮጵያ ላይ የሚደረገውን ጫናና ጣልቃ ገብነት አበርትቶታል የሚሉ መላምቶች ይሰማሉ፡፡
ባለፉት አምስት ወራት ከጦርነቱ መብረድ ጋር ጋብ ብሎ የቆየው የምዕራባውያኑ ጫናና ጣልቃ ገብነት፣ ነሐሴ 18 ቀን 2014 ዓ.ም. ዳግም ካገረሸው ሦስተኛ ዙር ጦርነት ጋር አብሮ አገርሽቷል፡፡
ባለፈው ሳምንት ለአፍሪካ ቀንድ ጋዜጠኞች በኢንተርኔት መግለጫ የሰጡት የአሜሪካ የምሥራቅ አፍሪካ ልዩ ልዑክ ማይክ ሐመር ጦርነቱ በአስቸኳይ ቆሞ፣ እንደገና ድርድርና የሰላም ንግግር እንዲጀመር ግፊት ሲያደርጉ ተሰምተዋል፡፡ አገራቸው አሜሪካ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ ዕልቂትና ቀውስ እንዳይቀጥል ከማዕቀብ ጀምሮ፣ ሁሉንም ዓይነት የዲፕሎማሲና የፖለቲካ ማስገደጃ አማራጮች በኢትዮጵያ ላይ ልትጠቀም እንደምትችልም ተናግረዋል፡፡
ሐምሌ 26 ቀን 2014 ዓ.ም. ከአውሮፓ ኅብረት ልዑካን ጋር መቀሌ አምርተው ከሕወሓት መሪዎች ጋር መገናኘታቸውን ማይክ ሐመር በዚሁ መግለጫቸው ጠቅሰዋል፡፡ በወቅቱ ሕወሓቶች ጦርነት ልንጀምር እንችላለን ብለው እንደ ነገሯቸውም ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ ላይ ሁሉንም የማስገደጃ አማራጮች እንጠቀማለን ሲሉ የተደመጡት ማይክ ሐመር፣ ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ለማስቆምና በሕወሓቶች ላይ ጫና ለማሳደር ለምን እንዳልሞከሩ ግን ሳያብራሩ ነው ያለፉት፡፡ ጦርነቱ ሳይቀሰቀስ ማስቆም እየተቻለ አሁን ተባብሶ መቀጠሉን አይተው የኢትዮጵያ ኃይሎች በአስቸኳይ ወደ ሰላም ካልመጡ የሚል ጫና ማሳደርን አሜሪካኖቹ የተካኑበት ይመስላል፡፡
‹‹የትግራይ ጦርነት ሲጀምር ምዕራባውያኑ ከኢትዮጵያ ጎን የቆሙ ይመስል ነበር፡፡ ወዲያው ግን ኢትዮጵያን ወደ መጫኑ ገብተዋል፤›› ሲል የሚናገረው ጋዜጠኛ ፍትሕ አወቅ የወንድወሰን፣ ጫናውን የሚወስነው ደግሞ የኢትዮጵያ ተፈጥሯዊ ባህሪ መሆኑን ያስረዳል፡፡
‹‹ኢትዮጵያ ቅኝ ያልተገዛችና ነፃ አገር መሆኗ፣ እንዲሁም ከሰብዓዊ ድጋፍና ከዲፕሎማሲ ውጪ በንግድ፣ በኢንቨስትመንትም ሆነ በኢኮኖሚ ከምዕራባውያኑ ጋር ጥብቅ ቁርኝት የሌላት መሆኑም ጫናውን ይወስነዋል፤›› ሲልም ያክላል፡፡
‹‹ከቅኝ ተገዥነት ተላቆና ያለ ውጭ ተፅዕኖ ሕዝቡ የኖረ በመሆኑ፣ ከውጭ የሚመጣ ጣልቃ ገብነትን በቀላሉ እንዳይቀበል አድርጎታል፡፡ ይህ በመላው ዓለም አገሮች ላይ ተፅዕኗቸውን ማስፈን የሚፈልጉትን ምዕራባውያን አያስደስትም፤›› ይላል፡፡
ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ ለሌሎች መጥፎ ምሳሌ ልትሆን ትችላለች የሚል የምዕራባውያንን ጫና የሚጋብዝ መሆኑን ፍትሕ አወቅ ይጠቅሳል፡፡ ሌላው በኢትዮጵያ ላይ የምዕራባውያንን ጫና ጋባዥ ጉዳይ የሰብዓዊ መብቶች አያያዝና ከሌሎች ኃያላን አገሮች ጋር ያላት አጋርነት መሆኑን ያክላል፡፡
ይህንኑ የሚያጠናክር አስተያየት የሰጡት ከሰሞኑ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዳጉ የውይይት ፕሮግራም ላይ ቀርበው የነበሩት የሕግ ባለሙያው አቶ የሺዋስ አድማሱ፣ የሰብዓዊ መብት ጉዳይ የምዕራባውያኑ ዋነኛ ‹የኒዮኮሎኒያሊዝም› (የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት) ማራመጃ ቀዳዳ ነው ብለዋል፡፡ ምዕራባውያኑ እንደ ቀደመው ጊዜ ጠብመንጃና መድፍ ታጥቀው ሳይሆን በዓለም አቀፍ ሕጎች በሰፈሩ የሰብዓዊ መብቶች አዋጆችን አጣቅሰው፣ በእጅ አዙር ተፅዕኖአቸውን ለማስፈጸም እንደሚመጡ ገልጸዋል፡፡
‹‹የፀረ ባርነት፣ የፀረ ዘረኝነት፣ የሰብዓዊ ወንጀሎች፣ የጦርነት ወንጀሎችና የዘር ማጥፋት ሕጎችን ተገን በማድረግ ነው የሚመጡብን፡፡ ከሰሞኑ አቻኩለውና ያልተረጋገጡ መረጃዎችን አጭቀው ይፋ ያደረጉትና በጦርነቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተፈጽሟል የሚለው ሪፖርትም የዚሁ ጫና ተቀፅላ ነው፤›› ሲሉም የሕግ ባለሙያው አቶ የሺዋስ ገልጸውታል፡፡
በዚሁ ፕሮግራም ሌላኛው ተወያይ የነበሩት የታሪክ ተመራማሪው አየለ በክሪ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ አዲሱ የተመድ ሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ሪፖርት ምዕራባውያኑ በኢትዮጵያ በቀጥታ እንዲገቡ የሚጋብዝ ነው ይላሉ፡፡ ‹‹ሪፖርቱ በምክረ ሐሳቡ እንደ የአፍሪካ ኅበረት፣ ኢጋድ፣ የተመድ ፀጥታው ምክር ቤት፣ የአውሮፓ ኅብረትና ሌሎች የሚመለከታቸው ሁሉ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ በቀጥታ እንዲገቡ አሳሳች በሆነ መንገድ ምክረ ሐሳብ ይሰጣል፤›› ሲሉ ነው የተናገሩት፡፡
ልክ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ሪፖርት በወጣ ማግሥት በተጠራው ስብሰባ ላይም፣ የኢትዮጵያ ጉዳይ ዋና የውይይት አጀንዳ ሆኖ የቀረበ ሲሆን፣ የምዕራባውያን አገሮች ተወካዮች በኢትዮጵያ ላይ ግፊት እንዲደረግ ወትውተዋል፡፡
የአውሮፓ ኅበረት ተወካይዋ በኢትዮጵያ ግጭቱ ቆሞ በአስቸኳይ የሰላም ውይይት እንዲደረግ አሳስበዋል፡፡ የእንግሊዝ ተወካይዋ ይህንኑ በሌላ ቋንቋ የደገሙት ሲሆን፣ የኤርትራ ኃይል ከኢትዮጵያ እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡ የአሜሪካዋ ልዑክም በተመሳሳይ በኢትዮጵያ የቀጠለው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ያሳስበናል ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ከዚህ ተነስተውም ለሰብዓዊ መብት ጥሰቱ ምክንያት የሆኑ ኃይሎችን እናወግዛለን ያሉት ዲፕሎማቷ፣ የኤርትራ ጣልቃ ገብነትም በአስቸኳይ ይብቃ ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
በዋናነት ኢትዮጵያንና መሰል አገሮችን ለማውገዝ የተጠራ በሚመስለው በዚህ ጉባዔ ላይ እንደተጠበቀው እንደ ቻይናና ሩሲያ ያሉ አገሮች ነበሩ የኢትዮጵያን አቋም ሲደግፉ የታዩት፡፡ የአፍሪካን አቋም ያንፀባረቁት ኮትዲቯርና ደቡብ ሱዳንን ጨምሮ ጥቂት አገሮች ነበሩ ኢትዮጵያን መደገፍ ችግሩን ለመፍታት አዋጪ መንገድ መሆኑን ያስረዱት፡፡
‹ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ወገኖችም ሆኑ ዓለም አቀፍ ሕጎች፣ አገሮች በየራሳቸው መንገድና ተጨባጭ ሁኔታ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር የሚያደርጉትን ጥረት መተካት አይደለም ሚናቸው› ሲሉ እነዚህ ወገኖች ለምዕራባውያኑ በተለያዩ መንገዶች ነግረዋቸዋል፡፡
በሌላ በኩልም ለራሱ ዜጎች በማሰብም ሆነ በመቅረብ ከኢትዮጵያ መንግሥት የተሻለ የለም በሚል መንፈስ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በአገሪቱ የሰብዓዊ መብቶች እንዲከበር የሚያደርገውን ጥረት መደገፍ እንደሚገባ እነዚህ አገሮች የምዕራባውያን አቻዎቻቸውን አሳስበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ተወካይም የተመድ ሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ኮሚቴ ሪፖርትን አጠንክረው ነበር የተቃወሙት፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ አድሎአዊና ኢፍትሐዊ በሆነ መንገድ በዚህ ኮሚቴ ጫና ሲደረግባት አንድ ዓመት አለፈ፡፡ ይህ ምክር ቤት የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎችም ቢሆን በተሳሳተ መረጃና ፖለቲካዊ ዓላማን ባነገበ መንገድ የሚካሄድ ይመስላል፤›› በማለት አጠቃላይ ሒደቱን የተቹት የኢትዮጵያ ተወካይ፣ አገሪቱ ለዓለም አቀፍና ለራሷ የሰብዓዊ መብት ሕጎች እንደምትገዛ አስምረውበታል፡፡
ኢትዮጵያ በተለይ ከትግራይ ክልል ጦርነት መፈንዳት ወዲህ ተጠናክሮ በቀጠለው በኢትዮጵያ ላይ ምዕራባውያኑ የሚያሳድሩት ጫና መነሻ መንስዔው ብቻ ሳይሆን፣ ጋብ የሚልበት መንገድም በእጅጉ ግራ እንደሚያጋባ ብዙዎች ይገምታሉ፡፡
ምዕራባውያኑ ከቀድሞው የኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የነበራቸው ግንኙነት አሁን ለቀጠለው ጫና ምክንያት ሊሆን እንደሚችል የሚገምቱ ስሜ አይጠቀስ ያሉ አንድ የውጭ ግንኙነት ባለሙያ፣ ተላላኪ መንግሥት በኢትዮጵያ እንዲፈጠር ከመፈለግ ጫናው እንደሚመጣ ይጠቅሳሉ፡፡
‹‹የቀደመው መንግሥት ጥሩ አገልጋይና አሽከር ከሆናቸው፣ የአሁኑ መንግሥት ባህሪ ደግሞ ከዚያ አንፃር የማይተነበይ ከሆነባቸው፣ ለእነሱ የተመቸ መንግሥት እስኪፈጠር በኢትዮጵያ ላይ የሚያሳድሩትን ግፊትና ጣልቃ ገብነት ይገፉበት ይሆናል፤›› ሲሉ ነው ባለሙያው የተናገሩት፡፡
ጋዜጠኛ ፍትሕ አወቅ በበኩሉ ከዚህ በተጨማሪ የዓለም ኃያላን አገሮች ፉክክርና ቀጣናዊ የምሥራቅ አፍሪካ ፖለቲካ የምዕራቡን ጫና የሚጋብዙ ሌሎች ምክንያቶች መሆናቸውን ይናገራል፡፡ ‹‹የምሥራቅ አፍሪካ ቀንድ፣ ሩቅ ቢመስልም እስከ የመን ያለው የመካከለኛው ምሥራቅ ቀጣና ከቅኝ ግዛት ማክተም ጀምሮ ላለፉት 50/60 ዓመታት በቀውስ ውስጥ የኖረ ነው፡፡ ምዕራባውያን በዚህ ቀጣና ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ያለች ብዙ ሕዝብ ያላት ሰፊ አገርን በተፅዕኖ ሥር ለማዋል ይፈልጋሉ በማለት ይገልጻል፡፡
በዚህ ረገድ ደግሞ ፖለቲካው ብቻም ሳይሆን የኢኮኖሚ ጉዳይም በተፅዕኖ ምንጭነት ታሳቢ መሆን እንዳለበት ፍትሕ አወቅ ይጠቁማል፡፡
‹‹ዛሬ ላይ በፖለቲካው አለመረጋጋት ውስጥ ኢትዮጵያ ብትወድቅም፣ ነገር ግን ደግሞ ተስፋ ያላት አገር ናት፡፡ መሥራት የሚችል ሰፊ የሆነ ወጣት ሕዝብ አላት፡፡ ኢትዮጵያ ሰፊ የገበያ መዳረሻ መሆን የምትችል አገር ብቻ ሳትሆን የውጭ ኢንቨስትመንቶችን ሊስቡ የሚችሉ ገና ያልተነኩ ብዙ የኢኮኖሚ ዕድሎችም ያላት ናት፡፡ አገሪቱ ተረጋግታ ጠንካራ ኢኮኖሚ መገንባት ከቻለች ለራሷ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ዕድል ትፈጥራለች፡፡ ይህ ካልሆነና ቀውሱ ተባብሶ የአገሪቱ ህልውና አደጋ ላይ ከወደቀ ደግሞ የስደት፣ የአደንዛዥ ዕፅ፣ የወንጀል፣ የሽብርና የጦር መሣሪያ ዝውውር መናኸሪያ በመሆን ለምዕራባውያኑም ሆነ ለመላው ዓለም ሥጋት ትፈጥራለች፤›› በማለትም የኢትዮጵያን ጂኦ ፖለቲካ ገጽታ ያብራራል፡፡
‹‹የኢትዮ ቴሌኮም 40 በመቶ ድርሻ ለሽያጭ ሲቀርብ በዓለም ገበያ ትልቅ የፕራይቬታይዜሽን ዜና ሆኖ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ግብርና ዘርፍ ቢሠራበት ከአገሪቱ አልፎ ለመላው የመካከለኛው ምሥራቅ የዳቦ ምንጭ መሆን የሚችል ነው፤›› በማለት ማሳያዎችን ይጠቅሳል፡፡ ከዚህ በመነሳትም ምዕራባውያንን ወደ ኢትዮጵያ እንዲያተኩሩ የሚያደርግ ብዙ ምክንያት መኖሩን የሚጠቅሰው ፍትሕ አወቅ፣ መንግሥት የእነሱን ጫና ለመቋቋም ከባድ ሁኔታ ውስጥ እንዳለ ነው የሚናገረው፡፡
እስካሁን ባለው ሁኔታ መንግሥት በተለያዩ መንገዶች ጫናውን ለመከላከል ጥረት ቢያደርግም፣ ከምዕራባውያን በኩል የሚቃጣውን ግፊት ግን ሙሉ ለሙሉ ማስቆም አለመቻሉ ይታያል፡፡ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ መንገዶች ግፊቱን ለመቋቋም ጥረት ባያደርጉ ኖሮ፣ እንደ ጫናው ክብደት አገሪቱ ተንገዳግዳ በወደቀች ነበር ሲሉ ብዙዎች ይገምታሉ፡፡ በዜጎች የበጎ ፈቃድ ተሳትፎ እየተካሄደ ያለው በማኅበራዊ ሚዲያ ዘመቻዎችና በተቃውሞ ሠልፎች የታገዘው የፐብሊክ ዲፕሎማሲ፣ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ የሚቃጣውን ጣልቃ ገብነት ጋብ እንዳደረገው ብዙዎች ይናገራሉ፡፡
ይሁን እንጂ ከሁሉ በላይ ጫናውን እንዲቀጥል ያደረገውና ያበረታው የውስጥ አቅም መዳከም እንደሆነ ነው የሕግ ባለሙያው አቶ መንግሥቱ አሰፋ የሚናገሩት፡፡ ‹‹ደካማ ከሆንክና ውስጣዊ ጥንካሬህን ካጣህ እንደ አገር ሁሉም ይንቅሃል፡፡ የራሱን ፍላጎት ሊያስፈጽምብህ ይሞክራል፡፡ ለጥቅሜ ካላደርክ ብሎ የበለጠ ሊያስጎነብስህ ይሞክራል፤›› በማለት ነው የሕግ ባለሙያው የሚያስረዱት፡፡
‹‹ዓለም የጎበዞች ናት፡፡ ምዕራባውያን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጀምሮ ዓለምን በራሳቸው ዛቢያ እንድትሽከረከር የሚያደርግ ሥርዓት ፈጥረዋል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ኔቶ፣ አይኤምኤፍ፣ የዓለም ባንክ፣ ወዘተ እያሉ በ70 ዓመታት ውስጥ ዓለም በአሜሪካ ፍፁም የበላይነት እንድትመራ የሚያደርግ ሥርዓት ፈጥረዋል፤›› ሲሉ የሚናገሩት አቶ መንግሥቱ፣ ኢትዮጵያም ከዚህ በተለየ ዓለም እንደማትዳኝ ገልጸዋል፡፡
እንደ ቻይና ያሉ ኃያላን አገሮች የነገ የዓለም ኃያላን ቢሆኑ እንጂ፣ አሁን እንኳን ሌሎችን ራሳቸውንም ለማዳንም እንደሚፈተኑ የሕግ ባለሙያው ይናገራል፡፡ ‹‹የውሻን ጥርስ በአጥንት እንደሚባለው ምዕራባውያኑ ቻይናን በታይዋን ጉዳይ ሲፈትኗት ነበር፡፡ ከዚያ ይልቅ የሩሲያው ፑቲን ብቻውን ቆሞ ያን ሁሉ የዓለም ግሪሳን ለመፋለም ሲታገል ዓይተናል፡፡ እንደ ቻይና ያሉ ወደ ኃያልነት እየገሰገሱ የሚገኙ አገሮች ከሩሲያ ጎን ካልቆሙ፣ ለራሳቸውም ሆነ አንፃራዊ ሚዛን ለነበረው ዓለም ፍፁም ውድቀት ነው፤›› በማለትም የዓለምን ጂኦ ፖለቲካዊ ግብግብ ያብራራሉ፡፡
ኢትዮጵያ ፍልሚያና ተፋላሚ በበዛበት በዚህ ‹‹ጨካኝ የጉልበተኞች ዓለም›› ራሷን ጠንካራ ተገዳዳሪ አድርጋ መቅረብ ካልቻለች፣ ‹‹የምዕራባውያን መጫወቻ›› ሆና ትቀጥላለች የሚል ግምታቸውንም ያብራራሉ፡፡
‹‹አሁን ያለው ማዕከላዊ መንግሥታችን ሐሳብ፣ ፍላጎትም ሆነ ግብ ምንድነው? ኢትዮጵያን ማፅናትና ሉዓላዊ አንድነቷን ጠብቆ የማቆየት ፍላጎት አለው ወይ?›› የሚል ጥያቄም ያነሳሉ፡፡ የሕግ ባለሙያው አቶ መንግሥቱ የአገሪቱን አንድነትና ጥንካሬ መጠበቅ ብቻ የምዕራባውያኑን ጫና ለመቋቋምና ጣልቃ ገብነቱን ለማስቆም ዋነኛ መፍትሔ መሆኑን ነው የሚናገሩት፡፡
ከሰሞኑ በብሔራዊ ቴሌቪዥናቸው መግለጫ የሰጡት የኤርትራ መሪ ኢሳያስ አፈወርቂ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያን በተመለከቱ ካነሷቸው ጉዳዮች ለምዕራባውያን ዓላማ ማጎብደድ የሚል ሐሳብ መኖሩ በሰፊው ተዘግቧል፡፡
‹‹ምዕራባውያኑ ሁልጊዜም ቢሆን ዋና አጀንዳቸው ብሔራዊ ጥቅማቸው ነው፡፡ የእነሱን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስጠብቅ አጎብዳጅ ቡድን እስከሆነ እንኳንስ ሕወሓት በራሳቸው ምክር ቤቶች አሸባሪ ተብለው ከተፈረጁ እንደ አልሸባብና አልቃይዳ ከመሳሰሉ ኃይሎች ጋርም ይተባበራሉ፤›› በማለት መናገራቸው በሰፊው ተዘግቧል፡፡
ለምዕራባውያን ብዙም ፊት ባለመስጠት የሚጠቀሱት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ በዚህ መግለጫቸው፣ ምዕራባውያኑ በኢትዮጵያ ጉዳይ እየተከተሉት ያለውን ለሕወሓት ያደላ ፖሊሲ አጠንክረው ኮንነውታል፡፡
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ታዬ አፅቀ ሥላሴ (አምባሳደር) በበበኩላቸው፣ ከውጭ ጫናና ጣልቃ ገብነት ለመላቀቅ ራስን መቻል ያለውን ትልቅ ድርሻ አጉልተው ያነሳሉ፡፡ ከሰሞኑ በተካሄዱ የተመድ ጉባዔዎች ብቻ ሳይሆን ጦርነቱ ከተጀመረ ጀምሮ የኢትዮጵያ ጉዳይ በሚታይባቸው ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ በመከራከር የሚታወቁት ታዬ (አምባሳደር)፣ ምግብ እንደመለመን አንገት የሚያስደፋ ነገር እንደሌለ ነው የተናገሩት፡፡ ከኃያላኑ ተፅዕኖ ለመላቀቅ በምግብ ራስን መቻልና ከተረጂነት መላቀቅ እየተባለ የሚመከረውን ሐሳብ ነው የበለጠ ያጠናከሩት፡፡