Sunday, July 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአገር ውስጥ ምርቶችን በመጠቀም የውጪ ምንዛሪ ለማዳን ተግቶ እየሠራ ነው!

ሪፖርተር ጋዜጣ በነሐሴ 8 ቀን 2014 ዕትሙ ‹ሸማች› በተሰኘው ዓምዱ ሥር ‹የአገር ኩራት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአገር ውስጥ ምርት ይጠቀም› በሚል ርዕስ አጠር ያለ ምልከታ ማስነበቡ ይታወሳል፡፡ ምልከታው የአገር ውስጥ ምርቶችን በመጠቀም የውጭ ምንዛሪን ለማዳንና አገር በቀል አምራቾችን ከማበረታታት አንጻር አቅጣጫ ማሳየቱ የሚበረታታ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአገር ውስጥ ምርቶችን ከመጠቀምና የውጭ ምንዛሪን ከማዳን አንጻር ያለውን አበርክቶና ቁርጠኝነት አዛብቶ አቅርቧል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለተጓዦቹ ለሚያቀርባቸው ምግቦችና መጠጦች ግብዓት የሚሆኑ ምርቶችን ከአገር በቀል አምራቾች ለመግዛትና የአምራቾችን አቅም በማሳደግ አገራዊ ኃላፊነቱን በመወጣት የውጭ ምንዛሪን ለማዳን የተለያዩ ጥረቶች ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ የአየር ትራንስፖርት ኢንዱስትሪው የሚጠይቀውን የጥራት ደረጃ አሟልተው የምግብ ግብዓቶችን በሚፈለገው መጠንና ጊዜ ከሚያቀርቡ የአገር ውስጥ አምራቾችና የአርሶ አደር ማኅበራት የተለያዩ ግብዓቶችን ሲገዛ ቆይቷል፣ ወደፊትም መግዛቱን ይቀጥላል፡፡

በአሁኑ ወቅት አየር መንገዳችን አትክልትና ፍራፍሬ፣ የወተት ተዋጽኦ፣ የበሬ፣ የበግና የዶሮ ሥጋ፣ የባልትና ውጤቶች፣ ብስኩት፣ የአልኮልና ከአልኮል ነጻ መጠጦች (ቢራ፣ ወይን፣ ለስላሳ መጠጥና ውኃ የመሳሰሉትን)፣ ዱቄት፣ ስኳር፣ በረዶና ሌሎች ምርቶችን ከተለያዩ አምራቾችና የአገር በቀል ምርት አቅራቢዎች በመግዛት ላይ ይገኛል፡፡ ይሁን እንጂ የሚፈለገውን የጥራት ደረጃ አሟልተው የምግብ ግብዓቶችን በሚፈለገው መጠንና ጊዜ የሚያቀርቡ የአገር ውስጥ አምራቾችና የአርሶ አደሮች ማኅበራት እንዳሉ ሁሉ፣ የሚፈለገውን የብዛትና የጥራት ደረጃ ማሟላት ያልቻሉ አቅራቢዎችም አሉ፡፡

አየር መንገዳችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ጥራት ያለው ምግብ ለመንገደኞቻቸው ከሚያቀርቡ ግዙፍ አየር መንገዶች ጋር የሚወዳደር በመሆኑ፣ የሚያቀርበው የምግብ ግብዓት የጥራት ደረጃ የኢንዱስትሪውን መለኪያ ያሟላና በሚፈለገው ጊዜና መጠን የሚቀርብ መሆኑን ማረጋገጥ አለበት፡፡ በዚህም መሠረት መሥፈርቱን ከሚያሟሉ አገር በቀል አምራቾችና አቅራቢዎች የተለያዩ ግብዓቶችን በመግዛት ላይ ሲሆን፣ ከእነዚህ አቅራቢዎች በሚፈለገው መጠንና የጥራት ደረጃ ሊያገኛቸው ያልቻላቸውን ግብዓቶች ከውጭ አገር አቅራቢዎች በመግዛት ላይ ይገኛል፡፡

አየር መንገዳችን የምግብ ግብዓቶችና ሌሎች አቅርቦቶች ፍላጎት በሚኖረው ጊዜ አገር በቀል አምራቾች መሳትፍ ይችሉ ዘንድ በአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን የጨረታ ግብዣ ያደርጋል፡፡ ይሁን እንጂ የሚጠየቀውን መሥፈርት አሟልተው በጨረታው ላይ የሚሳተፉት አገር በቀል አምራቾች በጣም ጥቂቶች ናቸው፡፡ በጨረታው ተሳትፈው ከሚያሸንፉት መሀል ደግሞ ወጥነት ያለው ግብዓት ለማቅረብ የሚቸገሩ አምራቾች እንዳሉ ለመታዘብም ችለናል፡፡ ይባስ ብሎም ከአየር መንገዱ ጋር የረዥም ጊዜ አቅርቦት ውል ስምምነት ከገቡ በኋላ የሚከሰቱ የዋጋ ጭማሪዎችን ለመጠቀም ሲሉ ምርቶቻቸውን ለሌላ ገዢዎች በማቅረብ ለአየር መንገዳችን ማቅረብ የሚገባቸውን ምርት የሚሰርዙ አቅራቢዎችም አሉ፡፡ 

የአገር ውስጥ ግብዓቶችን መጠቀም የውጭ ምንዛሪን ከመቆጠቡም በላይ የውጭ ምርቶችን አጓጉዞ ለማስቀመጥና ለመጠቀም የሚወጣውን የትራንስፖርትና የመጋዘን ወጪ ያስቀራል፡፡ ስለሆነም አየር መንገዳችን የሚፈለገውን የጥራት ደረጃና የአቅርቦት መጠን የሚያሟሉ አገር በቀል አምራቾች በበቂ ሁኔታ ቢኖሩና የምግብም ሆነ ሌሎች ግብዓቶችን ሙሉ በሙሉ ከአገር ውስጥ አምራቾች መግዛት ቢችል ይመርጣል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአገር ውስጥ ምርቶችን ለመጠቀም ካለው ቁርጠኝነት አንጻር፣ ከውጭ አገር የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ምርቶች ለመተካት በቋሚነት ጥናት የሚያደርግና ምክረ ሐሳብ የሚያቀርብ ክፍል አቋቁሞ በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡ በዚህም መሠረት የሶፍት ወረቀት ምርቶችና አንዳንድ ተጨማሪ ምርቶችን ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ከአገር በቀል አምራቾች ማግኘት እንደምንችል ባደረግናቸው ጥናቶች ለማወቅ ችለናል፡፡ እንደ ምሳሌ ለመጥቀስ ያህል፣ የሶፍት ወረቀት ምርቶችን ከአገር ውስጥ አምራቾች በሚፈለገው ጥራትና የአቅርቦት መጠን ማግኘት በመቻላችን ከውጭ እናስገባ የነበረውን የሶፍት ምርት ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ ምርት ተክተናል፡፡ በዚህም የውጭ ምንዛሪን ከማዳናችንም በላይ ወደ 100 ሺሕ ዶላር የሚጠጋ ተጨማሪ ዓመታዊ ወጪ ለማዳን ችለናል፡፡

አየር መንገዳችን አገር በቀል አምራቾች አቅማቸውን አጎልብተው ጥራቱን የጠበቀ፣ ተወዳዳሪ ምርት በሚፈለገው መጠንና ጊዜ ማቅረብ የሚያስችላቸውን ድጋፍ እንዲያገኙም የበኩሉን አስተዋጽኦ በመወጣት ላይ ይገኛል፡፡ ለምሳሌ ያህል አርሶ አደሮች ጥራቱን የጠበቀ የምግብ ግብዓት ለአየር መንገዳችን ማቅረብ ይችሉ ዘንድ የአቅም ግንባታ ድጋፍ እንዲያገኙ ከዩኤስኤይድ (USAID) ጋር ስምምነት ተፈራርመን የሚያስፈልጋቸውን የድጋፍ ዓይነት ለመለየት ጥናት በማድረግ ላይ እንገኛለን፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአገራችን አግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ እንዲያድግና እንደ ጭማቂ ያሉ የአግሮ ፕሮሰሲንግ ውጤቶችን ከአገር ውስጥ አምራቾች መግዛት የሚችልበት ሁኔታ እንዲፈጠር ጽኑ ፍላጎት አለው፡፡ አየር መንገዳችን በአሁኑ ወቅት የአገራችን ምርት የሆነውን አዲስ ሻይ ለተጓዦች እያቀረበ የሚገኝ ሲሆን የደንበኞችን የተለያየ ምርጫ ለማሟላት እንደ አረንጓዴ ሻይ ያሉ በአገር ውስጥ የማይመረቱ የሻይ ዓይነቶችን ከውጭ አምራቾች ይገዛል፡፡ በረራ ላይ የሚቀርቡ የታሸጉ የምግብና የመጠጥ ምርቶችን በተመለከተ፣ ማሸጊያውና አስተሻሸጉ አውሮፕላን በብዙ ጫማዎች ከፍታ ላይ ሲበር በረራው ውስጥ የሚኖረውን የአየር ግፊት ታሳቢ ባደረገ መልኩና የታሸገው ምግብ (መጠጥ) ሲከፈት ችግር በማይፈጥር መልኩ የአስተሻሸግ ደረጃውን ጠብቆ በከፍተኛ ጥንቃቄ የሚዘጋጅ ነው፡፡ ይህንን ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ በሚፈለገው የአስተሻሸግ ደረጃ ቡና የሚያቀርቡ አገር በቀል አምራቾች እስካሁን ማግኘት አልቻልንም፡፡

ከላይ በተጠቀሰው የምልከታ ጽሑፍ የአየር መንገዳችን የበረራ ሠራተኞች የደንብ ልብስና ደንበኞች በበረራ ወቅት የሚለብሷቸው ሙቀት ሰጪ አልባሳት በአገር ውስጥ ምርቶች ቢተኩ የሚል ምክረ ሐሳብ አቅርቧል፡፡ በዓለም አቀፍ የአቪዬሽን መመርያዎች መሠረት የበረራ ሠራተኞች የደንብ ልብስ የሚዘጋጅበት የጥራት ደረጃ የተቀመጠ ቢሆንም እነዚህን ደረጃዎች ባሟላ መልኩ የደንብ ልብሶቹን የሚያቀርብ አገር በቀል አምራች ማግኘት አልቻልንም፡፡

ሙቀት ሰጪ አልባሳቱም እንዲሁ የተጓዦችን ደኅንነት ለመጠበቅ ሲባል የጥራት ደረጃ ተቀምጦላቸው እሳትን መከላከል እንዲችሉ ተደርጎ የሚዘጋጁ መሆኑ ግምት ውስጥ መግባት አለበት፡፡ እነዚህን አልባሳት የሚፈለገውን የጥራት ደረጃ ባሟላ መልኩ የሚያቀርብ አገር በቀል አምራች እስካሁን ማግኘት ባለመቻላችን ከውጭ አምራቾች ለመግዛት ተገደናል፡፡  

ከቀረጥ ነጻ (ዲውቲፍሪ) ለሽያጭ የሚቀርቡ ምርቶችን በተመለከተ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንደ ሌሎች ዓለም አቀፍ አየር መንገዶች ሁሉ ደንበኞች የሚፈልጓቸውን ምርቶችን በረራ ላይ ያቀርባል፡፡ ይሁን እንጂ አንድ አውሮፕላን መሸከም የሚችለው ጭነት ውስን በመሆኑ አሁን በረራ ላይ ለሽያጭ በመቅረብ ላይ ካሉት ምርቶች በተጨማሪ አገር በቀል ምርቶችን መጨመር አዳጋች ነው፡፡

የአገር በቀል ምርቶች ለኢኮኖሚያችን የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ ማሳደግ ይቻል ዘንድ አየር መንገዳችን በቅርቡ 200 ካሬ ሜትር ስፋት ባለው መሬት ላይ ያረፈ አዲስ የዲውቲፍሪ የሽያጭ ማዕከል በአዲስ አበባ ቦሌ አየር ማረፊያ ተርሚናል ውስጥ ማስመረቁ ይታወሳል፡፡ እስካሁን ስምንት የቆዳ ውጤት አምራች ድርጅቶች የኢትዮጵያን የቆዳ ውጤቶች ለሽያጭ በማቅረብ ላይ የሚገኙ ሲሆን ባለፉት ሁለት ወራት 200 ሺሕ ዶላር ገቢ ማግኘት ችለዋል፡፡ ለሽያጭ ከሚቀርቡት የቆዳ ውጤቶች እስከ 400 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ ዓመታዊ ገቢ እንደሚገኝ ይጠበቃል፡፡

በአጠቃላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የውጭ ምርቶችን በአገር ውስጥ ምርቶች በመተካት የውጭ ምንዛሪን ለማስቀረት ብሎም አገር በቀል አምራቾችን ለማበረታታትና ተጠቃሚ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱና እስካሁን ያስመዘገባቸውን አመርቂ ውጤቶች በጥቂቱ ለማሳየት ሞክረናል፡፡ አየር መንገዳችን ወደፊትም በጥናት ላይ በመመሥረት ጥረቱን አጠናክሮ ለመቀጠልና በተሻለ ደረጃ የአገር ውስጥ ምርቶችን በመጠቀም የውጭ ምንዛሪን ለማዳን ተግቶ የሚሠራ መሆኑን ለመግለጽ ይወዳል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት