ከማክሮ ፋይናንስ ተቋምነት ወደ ባንክ አገልግሎት ከተሸጋገሩ አምስት የማክሮ ፋይናንስ ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው ሲንቄ ባንክ 250 ቅርንጫፎቹን ለባንክ አገልግሎት ለማዋል የሚያስችለውን ፈቃድ በማግኘት ሥራ ማስጀመሩን አስታወቀ፡፡
ባንኩ ባለፈው ሐሙስ መስከረም 12 ቀን 2015 ዓ.ም. የተሟላ የባንክ አገልግሎት መጀመሩንና አዲሱን የባንኩን መለያ በይፋ ባስተዋወቀበት ፕሮግራም ላይ እንዳስታወቀው ፣ የማክሮ ፋይናንስ አገልግሎቱን ይሰጥባቸው ከነበሩ 405 ቅርንጫፎች ውስጥ 250ዎቹን ለባንክ አገልግሎት አደራጅቶ ከብሔራዊ ባንክ ፈቃድ አግኝቶ ወደ ሥራ እንዲገቡ አድርጓል።
ቀሪዎቹን 155 ቅርንጫፎች ደግሞ ወደ ባንክ ቅርንጫፍነት ለማሸጋገር የሚያስችሉ ሥራዎች እያከናወነ እንደሆነና በአጭር ጊዜ ውስጥም ወደ ሥራ እንደሚገቡ የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ንዋይ መገርሳ ገልጸዋል፡፡
ባንኩ ከነዚህ ቅርንጫፎች ሌላ በአራቱም የአገሪቱ ክፍሎችና የኢትዮጵያ ጎረቤት በሆኑ አገሮች ቅርንጫፎቹን ለማስፋት መጠነ ሰፊ ሥራ በመሥራት ላይ መሆኑን ያመለከቱት ፕሬዚዳንቱ፣ ዘመናዊ የባንክ አገልግሎቶችን ለደንበኞቹ ለማድረስ የሚያስችሉ ዝግጅቶችንም ማጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡
ባንኩ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎቶችን ለመስጠት የሚያስችለውን ፈቃድ ከብሔራዊ ባንክ እንዳገኘም የተገለጸ ሲሆን፣ ይህንንም አገልግሎቱን በሰፊው የሚተገብረውና የባንክ ተደራሾችን ቁጥር ለማሳደግ አቅዶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አመልክቷል፡፡
ሲንቄ ባንክ በአገሪቱ የባንክ ታሪክ ከማክሮ ፋይናንስ ተቋም ወደ ባንክ የተሸጋገረ የመጀመርያው ባንክ ስለመሆኑ የገለጹት የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ቶሎሳ ደገፋ በበኩላቸው ባንኩ ተቋቁሞ ወደ ሥራ ሲገባ ያስመዘገበው የተከፈለ ካፒታል መጠን የአገሪቱ ባንኮች ሲቋቋሙ ካስመዘገቡት የተከፈለ ካፒታል የላቀ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ባንኩ ወደ ሥራ ሲገባ 15 ቢሊዮን ብር የተመዘገበና 7.04 ቢሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ይዞ እንደነበር የገለጹት የቦርድ ሰብሳቢው ይህም ባንኩ በከፍተኛ ካፒታል ሥራ በመጀመር አገልግሎቱን በስፋት እንዲሠራ ማስቻሉንም ጠቅሰዋል፡፡
እንደ ቦርድ ሊቀመንበሩ ገለጻ ሲንቄ ባንክ እስካሁን ከ16 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር የሰጠ ሲሆን የዚህ ብድር ተጠቃሚዎች ቁጥርም ከአንድ ሚሊዮን በላይ መድረሳቸውን ጠቅሰዋል፡፡
የባንኩ አስቀማጭ ደንበኞች ቁጥር ከሦስት ሚሊዮን በላይ መድረሱንም የቦርድ ሊቀመንበሩ አመልክተዋል፡፡
የባንኩን ልዩ መገለጫ ‹‹ብራንድ›› ተቀርጾም በዕለቱ ይፋ ተደርጓል፡፡ የባንኩ ኃላፊዎች አዲሱን የባንኩ መገለጫ ‹‹ብራንድ›› አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ፣ ‹‹የማኅበረሰባችንን ባህልና እሴት አክብሮ እንዲሁም ምርጥ ዓለም አቀፋዊ ተሞክሮዎች ላይ ተመርኩዞ የተሠራ ነው፤›› ብለዋል፡፡
ይህ ብራንድ የባንኩን ተልዕኮ ከግብ ለማድረስና ተወዳዳሪነቱን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ድርሻ እንደሚኖረውም ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡ የባንኩን በይፋ ሥራ መጀመርና አዲስ ብራንድ የማስተዋወቅ ፕሮግራሙ ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር)፣ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሽመልስ አብዲሳና ሌሎች የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡