Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትአለ ብዙ ነገር እስኪ እንነጋገር

አለ ብዙ ነገር እስኪ እንነጋገር

ቀን:

በገነት ዓለሙ

ዴሞክራሲ የመገንባት ጉዳይ ከሌሎች መካከል የተለያየ ሐሳብ የሚወከሉና የሚያከራክሩ ለፀብ የለሽ ውድድር የተፈጠሙ፣ ከትጥቅ ትግል ውጪ የሆኑ ፓርቲዎችን ይፈልጋል፡፡ ፓርቲዎች ግን ከጠመንጃ ብቻ የተፋቱ መሆን የለባቸውም፡፡ ከጠመንጃ የተላቀቀ ከብረት ትግል የተፋታ ቡድን ሁሉ ፓርቲ ሊሆን አይችልም፡፡ ከዚህ አኳያ ሕወሓት መፈተሽ ያለበት በኢትዮጵያ የፖለቲካ መልክዓ ምድርና ሰማይ ውስጥ በምርጫ የሕዝብ ፈቃድና የድምፅ ብልጫ አግኝቶ ፍላጎቱን ውሳኔ ማድረግ የሚያስችል፣ ለሁሉም እኩል የሆነ የጨዋታ ሜዳና ሕግ ውስጥ ገብቶና በእሱም ተስማምቶ መንቀሳቀስ ይሆንለታል ወይ? ይስማማል ወይ? ከሚል መሠረታዊ ጥያቄ አንፃር ነው፡፡

በዚህ ምክንያት ሕወሓት ፓርቲ ነው ወይ? ፓርቲ ሆኖ ያውቃል ወይ? ፓርቲ ሊሆንስ ይችላል ወይ? ተብሎ መጠየቅ አለበት፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሁሉም በላይ ደግሞ የትግራይ ሕዝብ፣ ትግራይን ብቻ ሳይሆን መላውን ኢትዮጵያን አገሬ ብሎ መኖር የሚያውቅበት የትግራይ ሕዝብ መመርመር፣ መጠየቅና መመለስ ያለበት ይህንኑ  ጉዳይ ነው፡፡ ይህም ጽሑፌ የሚያተኩረው ይህንን ጉዳይ ለመመለስ የማገዝ ጥቂት፣ እጅግ በጣም ጥቂት አስተዋጽኦ ለማድረግ ነው፡፡

ሕወሓት ለ1983 ዓ.ም. ግንቦት ድል የበቃው የትግራይን ሕዝብ የሕይወት መስዋዕትነት ከዚህም ጋር ብሶቱን፣ ተስፋውንና አመኔታውን እየተመገበ ነው፡፡ ሕወሓት ሥልጣን ላይ እያለም፣ ከዚያ በኋላ ደግሞ ከሥልጣን መንሸራተትን ባመጣ ጊዜም ጭምር ድንገት አንዳንዴ፣ መተንፈሻ አግኝቶ በሚነገር አስተያየት ደርግን ያሸነፈው ሕወሓት አይደለም እየተባለ የሚነገረውና በነፃነት ተገልጦና ተናፍሶ የማያውቀው ዕይታም በፍፁም ውድቅ የሚደረግ ነገር አይደለም፡፡ ለወታደራዊው አምባገነናዊው የደርግ መንግሥት ውድቀት የበለጠ ድርሻ ያዋጣው የራሱ የደርግ ችግር ነው፡፡ አገራዊና ኅብረ ብሔራዊውን ዴሞክራሲያዊ ሰላማዊና ሕጋዊ የከተማ ትግል ክፉኛ በመምታት፣ በማቆርቆዝና በመጨፍጨፍ ለ‹‹ብሔርተኛ›› እና ለአመፅ ትግል መቀፍቀፍ ምክንያት የሆነው የራሱ የደርግ ባህርይና አስተዋጽኦ ነው፡፡ ደርግ ገና 70ዎቹ መጀመርያ ላይ ካቀለት በኋላ ጀምሮ በእንቅልፍ ልቡና በሙቱ እንዲገዛ ያስቻለውና የሕዝብ መስዋዕትነትን ያበዛው፣ የሕወሓት የራሱ ስህተተኛና ፖለቲከኛ የትግል ሥልት ነው፡፡

እንዲያም ሆኖ ግን በ1983 ዓ.ም ደርግ ወደቀ፡፡ ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም. ወታደራዊ አምባገነንነት የፈረሰበት፣ ፈላጭ ቆራጮች እምባጮ የሆኑበት፣ ወታደራዊ ኃይላቸው፣ የፀጥታ መረባቸውና ፓርቲያቸው የተበጣጠሰበት ቀን ጊዜ ይሁን እንጂ፣ በዚህና ይህ ስለተደረገ ብቻ ዴሞክራሲ በምትኩ ይመጣል ማለት አይደለም፡፡ ሕወሓት በሚያሳፍር ሁኔታ የወደቀው ይህንን ባለመገንዘብ ድንቁርናው ብቻ ሳይሆን፣ እኔ ብቻ ልክ ዳፍንቱና ትምክህቱ ጭምር ነው፡፡ ሕወሓት እንኳንስ ስለአዲስ ገለልተኛ ወታደራዊ አውታረ መንግሥት ማሰብ ይቅርና ራሱን ተቋሙን ከገነቡት ግለሰብ ወታደሮችና መኮንኖች ጭምር መለየት አቅቶት፣ ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን ዓለምም የመዘገበው አሰቃቂ የሰብዓዊ መብት ረገጣ ዕርምጃ በመላው ወታደራዊ የሰው ኃይል ላይ ፈጸመ፡፡ ፀረ ሕዝብ ወታደራዊ ተቋምን ማፍረስ በመሠረቱ የዕዝ መዋቅሩንና የአቀራረፅ ሥርዓቱን መናድና ለአዲስ ግንባታ ማዘጋጀት እንጂ፣ በግለሰብ አባላት ላይ በነቂስና በጅምላ የበቀል ዕርምጃ መውሰድ ማለት አለመሆኑ ለሕወሓት እንኳን ያኔ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅትም ሙሉ በሙሉ ይቅርታ ያልተጠየቀበት ጉዳይ ነው፡፡

እና ሕወሓት በ1983 ዓ.ም. ያን ሁሉ ቅድመ 83 ተጋድሎ ረግጦ፣ የመላውን የትግራይንና የኢትዮጵያን ሕዝብ ጉጉት አፈር ድሜ አብልቶ፣ ለዚያውም በአዲስ ሥርዓት ስም ተጋዳላዮችን የሌላ የአፈናና የጥርነፋ ሥርዓት መሣሪያ አድርጎ በኢትዮጵያ ላይ በአዲስ ጉልበት አዲስ አምባገነንነትን ዘረጋ፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ በዚህ አድራጎቱ የትግራይ ልጅነት ከእሱ ቅሬታና ተቃውሞ አፍላቂ ገዥነት ጋር ተዛምዶ እንዲታይ፣ ማለትም የትግራይ ሕዝብ ከቡድኑ ጋር አብሮ የተጠቀመ ያስመሰለ ሥዕል እንዲፈጠር አደረገ፡፡ ክፍልፋይ አስተሳሰብና ወገናዊነትን ባባዛ አመለካከቱም፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን መተሳሰብ የጎዳና መርዙንም ለመንቀል ብዙ መከራ ያሳየ ሥራ ሠራ፡፡

እስኪ በዘመን ቅኝት ወደፊት እንለፍና 90ዎቹ ውስጥ እንግባ፡፡ ሕወሓት  በ1990ዎቹ መጀመርያ ላይ፣ እንዲሁም የኢትዮ ኤርትራ ግንኙነት ወታደራዊ ግጭት ውስጥ በገባበት ጊዜና ከዚያ ቀውስ ጋር ተያይዞም (ሕወሓት) ድርጅታዊ መሰንጠቅ በደረሰበት ጊዜም፣ በ1997 ዓ.ም. ብሩህ የምርጫ ዓመትም እንዲሁ ከአፈና አዙሪት በወጣ የዕርቅና የለውጥ መንገድ ከኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር መግባት የሚችልበትን ዕድሎች ታሪክ ይኼውልህ ብሎት ነበር፡፡ እነሱንም ተጫወተባቸው፣ አልተጠቀመባቸውም፡፡ 2010 ዓ.ም. መጋቢት መጣ፡፡ ይህ የመጋቢት 2010 ዓ.ም. ለውጥ ላይ እንዴት እንደደረስን መለስ ብለን እንይ፡፡ ምርጫ 2007 ተካሄደ፡፡ ሕወሓት ቁንጮና አቅጣጫ ነዳፊ፣ አድራጊ ፈጣሪ የሆነበት ኢሕአዴግ በኦባማ/ሱዛን ራይስ ‹‹ጊነስ ቡክ›› ሳይቀር የተመዘገበ መቶ በመቶ የምርጫ አሸናፊ የሆነበት ምርጫ ተካሂዶ የ2008 ዓ.ም. አምስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቋቋመው መንግሥት መስከረም መጨረሻ ላይ ተቋቁሞ ኅዳር ወር የተጀመረው ተቃውሞ፣ የ2010 ዓ.ም. መጋቢት ወር ለውጥ አመጣ፡፡ ይህ ለውጥ በኢትዮጵያ ወጣቶች ተጋድሎ ከራሱ ከኢሕአዴግ ውስጥ ብቅ ባለ ጊዜም፣ ሕወሓት የኢትዮጵያ ሕዝቦችን ይቅርታ አላከብርም አለ፡፡ በዚህ ለውጥ አማካይነት በአዲስ የለውጥ ስሜት የትግራይንና የኢትዮጵያ ሕዝቦችን የመካስ ዕድል ተደቅኖለት የነበረ ቢሆንም፣ እሱንም ለፀፀት አልበገር ብሎና ይህንንም ዕድል ረግጦ፣ ለአገር መናጋት ለትግራይ ሕዝብ ዳፋ ቀጥተኛ ምክንያት የሆነ ቡድን ነው፡፡

በዚህም አላበቃም፡፡ ከዚያም በኋላ በሥርዓቱ ላይ የበረታው ትግል የሕወሓትን የበላይነት፣ አድራጊ ፈጣሪነት፣ አቅጣጫ ነዳፊነትና ባህርይ ቃኝነት ሲያናጋ፣ እንዲሁም ወደ ሰሜን ያፈገፈገበት ሁኔታ ሲመጣ፣ የፀፀት፣ የይቅርታና ሕዝብን የመካስ አንጀት ያልፈጠረባቸው የቡድን መሪዎች ትግራይን መሰባሰቢያ ማዕከል አደረጉ፡፡ ከፌዴራሉ መንግሥት ጋርም የተማመኑበትን ተማምነው፣ ለመላው 27 ዓመት የሠሩትንና የደገሱትን ይዘው፣ በኢሕአዴግ ስም በቁጥጥራቸው ሥር የነበረውን መንግሥታዊ አውታር ውስጥ ያለውን ተፅዕኗቸውንና ትስስራቸውን ምሽግ አድርገው ምን ታመጣለህ!? ምን አባክስ ትሆናለህ!? ማለት ድረስ ዘራፍ ያለና የባለገ በተግባርም የተተረጎመ ሕገወጥነት ፈጸሙ፡፡ በዚህ ሳያበቁ ትግራይን የሌላ ጦርነት ማደራጃ ምሽግ፣ የትግራይ ሕዝብን ጉርስና ሀብት የሌላ ጦርነት መዘጋጃ ስንቅ፣ የትግራይን ወጣት የሌላ ጦርነት ጥይታቸው የማድረግ ሥራ ውስጥ ገቡ፡፡ የወታደራዊና የደኅንነት አቅም ያልነበረውን የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ መንግሥትም በሕወሓትና በትግራይ ሕዝብ ላይ ጥላቻና ጥቃት የከፈተ አስመስለው እያጭበረበሩ፣ ከሁሉም በላይ የሚገርመውና የሚደንቀው ደግሞ የራያና የወልቃይት ሕዝብ ልብ መሸፈትም ከራሱ ከሕወሓታዊ የደፍጠጣ አገዛዝ የመነጨ መሆኑን ደብቀውና አምታትተው፣ የራሳቸውን ጥፋት በአማራ (ሕዝብ መንግሥት) ላይ እያላከኩ፣ ‹‹በትግራይ ሕዝብ ላይ ማግለልና ከበባ እየተካሄደ ነው›› ብለው፣ የትግራይ ሕዝብ ከኢትዮጵያ ሕዝቦች ተነጥሎ የበቀል ጓዳቸው እንዲሆን ሠሩ፡፡ በዚህም አማካይነት የትግራይ ሕዝብ ጭምር የተዋደቀላትን ኢትዮጵያ ለመቦጫጨቅ ተነሱ፡፡ 

ወደፊት ከመቀጠላችን በፊት ለምን የዓብይ ወይም የለውጡ መንግሥት የወታደራዊና የደኅንነት አቅም አጣ የሚለውን ጥያቄ ትንሽ አፍታትተን እንየው፡፡ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ መንግሥታዊ አውታር ባለቤትነት፣ አዛዥና ናዛዥነት፣ አድራጊ ፈጣሪነት የሕወሓት ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ፓርቲው ኢሕአዴግና የመንግሥቱ ፓርላማ ሊቀመንበርና ጠቅላይ ሚኒስትር አድርገው የመረጡት ተሿሚ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ውስጥ ሲገባ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ሥልጣንንም አብሮ ማግኘት ያልቻለበት ‹‹ተደብቆ›› የኖረ በውሸት ሲሽሞነሞን የኖረ ሀቅ ብቅ አለ፡፡ ይህንን ሀቅ ራሱን በግልጽና በአደባባይ በይፋ የሰማነው እንኳ ከጥቅምት ጦርነት በኋላ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓርላማ የኅዳር 2013 ዓ.ም. መልስ/ማብራሪያ ላይ ነው፡፡

ጥቅምት 24 ቀን በተነሳ ቁጥር ዜናው ውስጥ፣ ዜና ቢጤ ነገሩ ውስጥ የምሰማው የሚገርመኝ ብቻ ሳይሆን የሚያመኝ አንድ ነገር አለ፡፡ በአጠቃላይ ይህ ዜና ሲነገር ይህን ይመስላል፣ ወይም እንዲህ ይላል፡፡ ጦርነቱ የተነሳው/የጀመረው ጥቅምት 24 መሆኑን ይገልጽና፣ ጦርነቱ ጥቅምት 24 የተነሳው ዓብይ አህመድ ወታደሮቹ በትግራይ አማፅያን/ቡድን ላይ ዕርምጃ እንዲወስዱ ሲያዝ ነው ይላል፡፡ እርግጥ ነው ዓብይ ለወታደሮቹ ትዕዛዝ የሰጠው ዝም ብለው፣ ከመሬት ተነስተው ነው አይልም ዜናው፡፡ ዓብይ አህመድ ለሠራዊታቸው ትዕዛዝ የሰጡት ግን በዚህ ‹‹የተቋቋመ›› ዜና መሠረት የሰሜን ዕዝ በሕወሓት ስለተጠቃ ሳይሆን፣ ተጠቃብኝ ብለው ነው እንዲህ ያለ የተድበሰበሰ፣ ከዚያም አልፎ ሰሜን ዕዝን መጠቃት (ሌላው ቢቀር መጠቃት) የሚክድ ዜና ስፖንሰር የሚያደርጉና የሚያራምዱ ‹‹የዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ›› አባላት ለሰላም እንቆማለን ሲሉ፣ አስታራቂ ሲሆኑ የየጆኦግራፊያቸውና የ‹‹የጥቅማቸው›› የሰላም መልዕክተኛ ሲሾሙ ያማል፡፡

የሕወሓት የጥቅምት 24 የክህደትና የውስጥ ወረራ ዕርምጃው ግን ትግራይ ውስጥ ቤት ንብረት እስከ መመሥረት የዘለቀ ትስስር የነበረው፣ ቤተሰቡን ለመጦር እንደደረሰና እንደበቃ ልጅ የትግራይን ሕዝብ በታማኝነት ሲያገለግል የቆየውን የሰሜን ዕዝ ሠራዊት ከውስጥ ባስካዷቸው ደበኞቻቸው/ትክል ወኪሎቸው አማይነት፣ እንዲሁም የእነሱ የብቻ አድርገው በሞሸሯቸው ልዩ ኃይሎች አማካይነት በሰሜን ዕዝ ላይ ከመሣሪያ ነጥሎ የመፍጀትና ከሥራ ውጪ አድርጎ የመበተን ግፍ ፈጸሙ፡፡ ይህ ራሱ ብቻውን ብዙ የሚያቆይ የክህደት፣ የውስጥ ወረራ፣ የአገርን የመከላከያ አቅም ያሽመደመደና አገርን ራቁት ያስቀረ አደጋ ያደረሰ ከፍተኛና ብርቱ የወንጀል ተግባር ነው፡፡

ከዚህ ፍጅትና ክህደት ወጥመድና አደጋ እየተተኮሰ ያመለጠው የሰሜን ዕዝ ተራፊ ከሌላው ቀሪ የኢትዮጵያ ክፍል ከደረሰው ኃይሎች ጋር ሆኖና በኤርትራም ታግዞ የደረሰበትንና የተፈጸመበትን ክህደት፣ ጅምላ ጥቃትና ወረራ ጭምር ጅምላ በቀል መውሰጃ ነውር አድርጎ ሳያብድ በ15 ቀናት ውስጥ በድል መቀሌ በገባ ጊዜም፣ የሕወሓት ጦርኞች ኧረ አሁንስ የትግራይ ሕዝብ ከመከራ ይተንፍስ አላሉም፡፡ ‹‹ትግላቸው››ን ቀጠሉ፡፡ ትግላቸውንም/ጦርነታቸውንም ሕግ፣ የትኛውም ዓይነት ሕግ፣ የጦርነት ሕግ ጭምር የሚገዛው አልነበረም፡፡ ብዙ ሺሕ ደረቅ ወንጀለኞችን ለቀቁና በትግራይ ሕዝብ ላይ በተኑ፡፡ ከሞላ ጎደል የራሳቸው ካድሬዎች የተቆጣጠሩትን የጊዜያዊ አስተዳደር መዋቅር መሻጠሪያና የወንጀል ድርጊት መፈጸሚያቸው አደረጉ፡፡ የኢትዮጵያና የኤርትራ ወታደራዊ የደንብ ልብስ በለበሱ ሰዎቻቸው አማካይነት ሸሮች ብቻ ሳይሆን ወንጀል በመሥራት ጭምር በሰላም ሠርቶ መግባት እንዲያቅት፣ በዚህም አማካይነት የትግራይን ሕዝብ ጉስቁልናና ብሶት እያበራከቱና በኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት ላይ የሕዝብ ቁጣ እንዲፈላ እያደረጉ፣ የትግራይን ሕዝብ መከራ እየቸረቸሩ ቀጣፊ የፖለቲካ ትርፍ ነገዱ፡፡ ይህ ንግዳቸው የወደፊት የዓለም አቀፋዊ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ምርመራ ማስረጃ ‹‹ማምረቻ›› የመሆንም፣ እንዲሁም ትግራይን ሕዝብ በእልህ አሳብዶ ለሌላ ጦርነት በማገዶነት የማሠለፍ ሌላ ግፍ መደገሻ አገልግሎት ነበረው፡፡

እንደ ተመኙትም፣ እንደፈለጉትም ከሁሉም በላይ ደግሞ የአገር፣ የኢትዮጵያ መንግሥትን ሥልጣን የግል፣ የጎጠኛ፣ የፓርቲያዊ ፍላጎታቸው ማስፈጸሚያ መሣሪያ አድርገው፣ የዓለም አቀፋዊ ግንኙነታችንን ወንበር፣ ቦታና ሀብት ጭምር ተጠቅመው በኢትዮጵያ ጥቅም ላይ ተጫወቱ፣ ‹‹ተጫውቱብን››፡፡ ‹‹ዕድሜ›› የዝርፊያ ማዕድ፣ የምርኮ ሲሳይ፣ የግልና የፓርቲ ጥቅም ምሽግ ሆኖ ላረፈው የኢትዮጵያ መንግሥት ሥልጣን እንጂ፣ የመንግሥታቱ ድርጅት ሥርዓት (UN System) የሚባለው ሁሉ፣ ሚዲያው እንደ ተቋም ሳይቀር፣ ግለሰብ ጋዜጠኛን ጭምር ገንዘብ የሚገዛው፣ የተሻለም ካገኘ በ‹‹ጨረታው›› የማይገደድ፣ ኃፍረት የማያውቅና አገልግሎቱን የሚሸጥ፣ አክቲቪስትነትና ፖለቲከኛነት ነገር ሆነ፡፡ በአገራችን ጋዜጠኝነት ውስጥ በራሱ፣ በአቅሚቲ የደረሰው ድብቅም ግልጽም የሚያስነቃም የማያስነቃ፣ የማያሠጋም እንደ ሙያ የሚቆጠር መገለባበጥ ራሱ ዋናውና አጣዳፊ ጉዳያችን ሲያልፍ እናወራዋለን ብለን የያዝነው ጉዳይ ነው፡፡

እንደፈለጉትና እንደተመኙትም የበቀል ቁጣን በሸር አፍልተው የመከላከያ ሠራዊቱን በራሱ ጥፋት ባልሆነ ምክንያት የሚያሽመደምድ ውጤት ያለው ሥራ ሠሩ፡፡ ሠራዊቱም ፊት ለፊቱ የተጋረጠበትን ሕዝብ የመፍጀት ‹‹ግብዣ›› ዕንቢ ብሎና እየሸሸ ከትግራይ ወጣ፡፡ ሕወሓቶች ግን ከወጣም በኋላ የትግራይ ሕዝብ ክረምቱን አርሶ ይጉረስ እንኳን አላሉም፡፡ ታዳጊዎችን ሳይቀር፣ እነሱን ጭምር ካልተሟላ ሥልጠናና መሣሪያ ጋር እያንጋፈፉና የትግራይን የሙያ ሰዎች/ባለሙያዎች የማሽን ነቀላና የዘረፋ ኃይል አዝማቾች አድርገው ወደ አማራና ወደ አፋር ክልሎች አዘመቱ፡፡ በዚህ ‹‹ሁለተኛው ዙር›› ጦርነትና ዘመቻ ተደራራቢና ብርቱ ወንጀሎችን ፈጸሙ፡፡ ዝርዝሩ ብዙ ነው፡፡  አሁን ደግሞ ሦስተኛውና የተባበሩት መንግሥታት ሥርዓት ማለትም ‹‹የUN System›› የሚባለውም የሚሳተፉለት፣ ተካፋይ የሆነበት ‹‹ሦስተኛው ዙር›› ጦርነት ውስጥ ነን፡፡

‹‹ሁለተኛው ዙር›› ውስጥ ምን ሆነ? አንዳንዶችንና አጠቃላይ ገጽታቸውን መለስ ብለን የምንቃኘው ዝርዝሩም ሆነ ይዘቱ ሁለተኛውን ዙር ከመተረክ ይልቅ፣ ‹‹ሦስተኛውን›› ዙር ፈተናችን ‹‹መስታወት›› ሆኖ ስለሚያገለግለን ጭምር ነው፡፡

ሕወሓቶች ለጦርነታቸው ማገዶ ያደረጉትን የትግራይ አዋቂና ታዳጊ በንፁኃን የአፋርና የአማራ ሲቪሎችና ሲቪል ተቋማት ላይ ጭምር በነውረኛ ስድብ የቀለመ ኢሰብዓዊ፣ ጨካኝና ነውረኛ ጥቃት እንዲፈጸም፣ ቤተ እምነቶችን እንዲደፍርና እንዲመዘብር አደረጉ፡፡

ሕወሓቶች አዲስ አበባ ድረስም እንመጣለን ብለው ተዘባነኑ፣ ፎከሩ፣ ‹‹ተዘመረላቸውም››፡፡ አዲስ አበባ ድረስ ገብተው በቀል ለመወጣት ከተመቸና ከቀና ኢትዮጵያን ወደ ትንንሽ አገሮች ቆራርሰው፣ እነሱ በኮንፌዴሬሽን ሥልት ከኢትዮጵያ ሊያገኙ የሚችሉትን ለመጋጥ፣ ይህ ካልሆነም ኢትዮጵያ የምትባለዋን አገር ከዚህ ወዲያ እንዳትገጣጠም አድርጎ ለማባላትና ሕዝቧንም ለማጨራረስ ሲሉ፣ ከትግራይ ሕዝብ በገፍ ያፈሷቸውን የተዋጊ ማገዶዎች (ወደ ምዕራብም፣ ወደ ምሥራቅም ወደ ደቡብም ሰሜን ሸዋ ዘልቆ አዲስ አበባን እስከ ማማተር ድረስ) በሰፊ በረዥም ርቀት ረጭተው በአፀፋ መልሶ ማጥቃት ደግሞ ከባድ ዕልቂት እንዲደርስባቸው አደረጉ፡፡

ታሪኩና እውነቱ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ያን ያህል መከጀላቸው፣ ያን ያህል ከትግራይ ውጪ ኢትዮጵያን ‹‹ማጥለቅለቃቸው››፣ ተው ሲባሉ ሞቼ እገኛለሁ ብለው የጠሩት የአፀፋ ዕርምጃ የግድ ሲመጣ ደግሞ ከባድ ዕልቂት የደረሰባቸው መሆኑ ብቻ አይደለም ታሪኩና እውነቱ፡፡ የአፀፋ መልሶ ማጥቃቱ ዘመቻ በውጤትነት ያስከተለው መሸሻቸውን ብቻ አልነበረም፡፡ የሸሹትና የወጡት እየዘረፉ፣ እያወደሙ፣ እየረገፉም ነው፡፡ በዚህ እየዘረፉና እያወደሙ በመሸሽ ሒደትም ውስጥ ከበፊቱ በተጨማሪ ሌላ የርሸና ወንጀል እንዲፈጸም በማድረግ የአፋርና የአማራ ሕዝብ ከኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎች ጋር ቁጭት በቁጭት ነደው ወደ ትግራይ በመግባት የትየለሌ የግፍ ብቀላ እንዲፈጸም፣ ሕዝብ ከሕዝብ እስከ መጨረሻውና እስከ ወዲያኛው እንዲቆራረጥላቸው በከፋ ድርጊታቸው አባበሉ፣ ጋበዙ፡፡ የትግራይ ጦረኞች (ሕወሓቶች) ሌላው ቀርቶ የተረፈው ተርፎ ወደ ትግራይ አስተዳደር ወሰን የገባውን ትራፊ ኃይል እንኳን ዕረፍት ሊሰጡት አልፈቀዱም፡፡ ይህ ኃይል እንደገና እየተወረወረ አፋርና አማራ ላይ አስከፊ ጥፋት በመፈጸም በአፀፋው በትግራይ ሕዝብ ላይ ጅምላ ጥቃትና ጭፍጨፋ እንዲመጣ ቋምጠው መለማመኛ አደረጉት፡፡ ይህ ምኞታቸው፣ ሥለትና ፀሎታቸው ግን አልሠራም፡፡ በዚህ ምክንያት ግድያና ጭፍጨፋ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሕዝብ ከሕዝብ ጋር ደም እንዲቃባ፣ እስከ መጨረሻ እንዲቆራረጥ ማድረግ  የሚችል አደጋንም ተከላክሏል፡፡

ኢትዮጵያ ላይ ‹‹የተሾሙ›› የሰብዓዊ መብት አስከባሪ ተከላካይና መርማሪዎች ተብዬዎች ግን እንዲህ ያለ ነገር አያውቁም፣ አይገባቸውም፡፡ መደበኛውን፣ ተራውን፣ እንጀራ የሚበሉበትን፣ ዝናና ክብር የሚያገኙበትን፣ በሥርዓቱ ውስጥ (በራሱ በመንግሥታቱ ድርጅት ሥርዓት ውስጥ ጭምር) ከአሠሪያቸው ተቋም የሱሪ ኪስ ወደ ደረት ኪስ ለመግባት የሚታጩበትን ታሪክ ለማስመዝገብ ሽር ብትን የሚሉ እንጂ ለሙያና ለኃላፊነት የሚታመን ባህርይ የሌላቸው ናቸው፡፡ በየቦታው ሰውና ስም እየጠቀስን እዩዋቸው፣ ስሟቸው የምንላቸው በርካታ አሉ፡፡

ሕወሓት ለምን እንዲህ ያደርጋል? እነዚያስ እነ ኢንተቤ ኡጋንዳ መቀመጫቸውን ያደረጉት ኢንተርናሽናል ኤክስፐርት ተብዬዎች፣ ሌሎች በዩኤን ሲስተም ውስጥ ያሉት ያገባናል ባዮች፣ እነ አሌክስ ዱቫልን የመሳሰሉ በዩኒቨርሲቲና በሰላም ማዕከል ዙሪያ የተሰባሰቡ ሰዎችስ በምን ምክንያት እንዲህ ያደርጉናል? ለምን? ለምን?

ሕወሓት ከሰላማዊና ከሕጋዊ ትግል ጋር የማይተዋወቅ ጦረኛ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከደርግ ወታደራዊ አገዛዝ የተሰናበተችበት ለውጥ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ባይወስድም፣ የተገኘው ሥልጣን የመስዋዕትነቴ፣ የትግሌ፣ የጦርነቴ፣ የድል አድራጊነቴ ውጤት ነው ብሎ የሚመፃደቅ በጦርነት ማሸነፍን የትክክኛነቱ፣ የሕዝብ ጥቅም ውክልና ባለቤትነቱ ማስረጃ አድርጎ ሲበዛ የሚኮራ፣ በዚህም ምክንያት ኩራቱን ወደ ትምክህት የቀየረ ድርጅት ነው፡፡ ከጥቅምት 24 በፊት በታዩት የመፋጠጥና የጦርነት ዋዜማ ወቅት ሕወሓትን እናውቀዋለን የሚሉና በዚህም ‹‹ዕውቀታቸው›› ታውቀው በኮርፖሬት ሚዲያው ገንዘብ የሚከፈልበት የምስክርነት አገልግሎት የሚሰጡ ግለሰቦችና ተቋማት የሕወሓትን የጦርነት ብቃት፣ ብልኃትና ጥበብ ሲተነብዩ ኖረዋል፡፡ እሱም ራሱን ቢሆን ስለማሸነፍ የማይጠረጠር፣ በተፈጥሮውና በልምዱ አሸናፊ እንደሆነ ከመናገር የማያፍር፣ በዚህም ላይ ደግሞ ፍትሐዊ ምክንያቱ ሁሌምና ምንጊዜም ለአሸናፊነቱ ማረጋገጫ እንደሆነ የገዛ ራሱን ምስክርነት የሚሰጥና ‹‹ፓርቲ››ም ነኝ የሚል፣ በተለይም ኢትዮጵያን ለማፈራረስና ሕዝቧን ለማጨፋጨፍ ገሃነመ እሳት ድረስም መሄድ ይችላል/እችላለሁ የሚል ቡድን ነው፡፡

ሲሸነፍና ሲመታ፣ እንዲሁም ይጠቅምሃል/ይጠቅመኛል ሲልና ሲባል ግን ተቃራኒውን ተፋላሚ ኃይል መክሰስ ብቻ ሳይሆን፣ እንዲከሰሱም ጭምር ጥቃትና ጭፍጨፋ በሕዝብ ላይ እንዲመጣ ያባብላል፣ ይጠራል፣ ያሳስታልም፡፡ ከሰመረለትም፣ እንደ ፈቃዱ ከሆነለትም የገዛ ራሱን ሕዝብ አስፈጅቶም ይሁን ዕልቂቱን የሚደግስ ቴአትር ሠርቶ ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብን ‹‹ድረሱ››ልኝ ይላል፡፡

ዛሬ የአንድ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት በሚላወስበት በተመድ፣ በተመድ ሲስተም ውስጥና ተያያዥነት ባላቸው ተቋማት አካባቢ ግጭቶችና የተለያዩ ጉዳዮች ፍትሐዊ መስተንግዶና መፍትሔ እንዲያገኙ ማድረግ ኃላፊነታችን ነው በሚሉ አገሮች ውስጥ ለምሳሌ ቅኝ ተገዛሁ ያለና አዎ ተገዝተሃል ያሉት ሕዝብ ከቅኝ ገዥው የመለየት መብት የታወቀ ነገር ነው ይባላል፡፡ እንዲሁም የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ የተካሄደበት ሕዝብ ከጭፍጨፋ አደጋ መገላገልን ከመነጠል/መገንጠል ጋር አያይዞ ሲንቀሳቀስ፣ ጥያቄውን ተገቢ አድርጎ የመደግፍና በሕግ አግባብ የሚያስተናገድ ዝንባሌ አለ፡፡ ሕወሓት ይህንን አሳምሮ የሚያውቁ ብቻ ሳይሆን እንዲህ ያለ መሰሪነት፣ ‹‹ሙሽሪነት››ና ሴራ የሚደግሱ በ‹‹ኪራይ›› የሚሠሩ ‹‹ባለሙያዎች›› አሉት፡፡

ለምሳሌ ኢትዮጵያ ፈቃዷን ሳትሰጥና ውዴታዋን ሳትገልጽ የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት እ.ኤ.አ. በዲሴምበር 17 ቀን 2021 ያቋቋመው በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኤክስፖርቶች ዓለም አቀፋዊ ኮሚሽን ተብዬው መርማሪ ቡድን መስከረም 9 ቀን 2015 ዓ.ም. ያወጣው የመጀመርው ሪፖርት (ፍርድ)፣ ገና ከሩቁ የሚሸትና አላስቀርብም የሚል ጉድና ክፋት አለው፡፡ የዋናው ሪፖርት አካል ወይም አኔክስ አንድ ሆኖ የተያዘው የኢትዮጵያ ‹‹አጭር ታሪክ›› መግለጫ፣ ዘመናዊት ኢትዮጵያ የተቋቋመችው በ19ኛው ምዕተ ዓመት ሁለተኛው አጋማሽ ውስጥ በተካሄደ መስፋፋት መሆኑን፣ በ1855 እና በ1898 ዓ.ም. መካከል ተከታታይ የትግራይና የአማራ ነገሥታት ሥልጣናቸውን ለማማከል መንቀሳቀሳቸውንና ወደ ደቡብ ያሉ ሰፊ ግዛቶች፣ በርካታ ነፃ መንግሥታትንና ኤምሬቶችን ጨምሮ በሰሜናዊው አገዛዝ ቁጥጥር ሥር መግባታቸውን፣ ይህም ሒደት ከአውሮፓውያን የቅኝ አገዛዝ ኃይሎች አጎራባች አካባቢዎችን ከመስበር/ከማጠቃለል ተግባራቸው ጋር ተገዳዳሪ መሆኑን የኢትዮጵያ የግዛት መስፋፋት ማብቂያ ላይ ኢትዮጵያ ከ80 በላይ የታወቁ ቋንቋዎችን የሚናገሩ፣ አብዛኞቹም እስልምናና ትራዲሽናል ሃይማኖቶች ተከታይ የሆኑ ሕዝቦች ማካተቷን ይናገራል፡፡

ታዲያ የዚህ ‹‹መግቢያ›› ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ›› ችግር ምንድነው? የሚል ጥያቄም ይነሳል፡፡ የኢትዮጵያን ችግር ለሚያውቅ (እንኳንስ የኢትዮጵያ ችግር በ‹‹ዳኝነት›› እፈታለሁ የሚል የተሾመና ሥልጣን የተሰጠው አካል) በአሁኑ ሰዓት፣ በተለይም በዚህ ወቅት ከኢትዮጵያ የታሪክ ጉዳዮች መካከል እንደ ጦር የሚፈራውና ከሁሉም በበለጠ የመግባባት ችግር ያለበት ነገር አንዱ የኢትዮጵያ አገነባብ ጉዳይ ነው፡፡ የብሔር/ብሔረሰብ ነገር ነው፡፡ ማነው ብሔር፣ ማነው ብሔረሰብ እንኳን በጋራ የሚያግባባ አይደለም፡፡ በዚህ ውስጥ በአንዳንድ ብሔረሰቦች ዘንድ ቅኝ ውስጥ ነኝ የሚለው አመለካከት በታሪክ ጥናት ውስጥ እንደ ቆንጥር ያስቸገረ ጉዳይ ነው፡፡ በየትም ዓለም ቅኝ ገዥነት በተፈጸመባቸው ቦታዎች ውስጥ ቅኝ ገዥዎች፣ ቅኝ ገዥነታቸውን ተጠራጥረው አያውቁም፡፡ ተገዥዎቹም ቅኝ ውስጥ ነን ወይስ አይደለንም የሚል ግራ መጋባትና ክርክር ተፈጥሮባቸው አያውቅም፡፡ በእኛ ሁኔታ ግን ‹‹ቅኝነቱ››ን የወለደው የመነጠል ፖለቲካ በመሆኑ አወዛግቧል፡፡ መነጠልን በማሳካት ዓላማ ታሪክ ተቆልምሟል፡፡

እነ ማርቲን ፕላውትና ሌሎችም የኪራይ ኤክስፐርቶች/ተንታኞች 80 ማኅበረሰብ ስላላት የኢትዮጵያ ኢምፓየርና ይህንንም ኢምፓየር ወደ ዴሞክራሲ ስለማሸጋገር ግዙፍ ችግር በሚያወሩበት ዓውድ ውስጥ ከሁሉም በላይ ደግሞ እንደ ጦር የሚፈራውን፣ የጋራ መግባቢያ እንዲያገኝ የሚፈለገውን፣ ይህንን ጉዳይና ክርክር የእናንተን ዳኝነት ጠይቆ የቀረበ ጭብጥ ነው ያላቸው ሳይኖር በዚህ ጉዳይ ላይ በኤኔክስ I ተራ ቁጥር አንድና ሁለት ላይ ‹‹ብይን››፣ ‹‹ፍርድ›› መስጠታቸው ድንቁርናቸውን ከማጋለጥ በላይ አለን የሚሉትን የ‹‹ዳኝነት ሥልጣን›› መሠረት የሚንድ ነው፡፡ የሚነድ፣ የሚቃጠል የእሳት አደጋን ለመከላከል የተሰማራ ተከላካይ ብርጌድ እሳቱ ላይ የሚደፋው/የሚተፋው ኬሚካል ምንድነው? የሥራው፣ የሙያው/የጥበብ መጀመርያ ነው፡፡

ሕወሓት ምን እንደሚፈልግ አሳምረን እናውቃለን፡፡ እሱ የማይገዛት ኢትዮጵያ ትፈርሳለች እንጂ የሰው መኖሪያ አትሆንም፡፡ ይህን ሥራዬ ብለው የሚሠሩ መኖራቸውን አውቀናለን፡፡ ይህንን በጥበብ ማጋለጥ፣ አገርን ከማዳን የህልውና ፈተናችንና ዴሞክራሲን ከማደላደል የሥረ የመሠረት አደራችን ጋር ተገጣጥሞ ድርብርብ ጥረት፣ ድርብርብ ጥጋትና በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ርብርብ ጠይቆናል፡፡ 

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አወዛጋቢው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ

በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ የሚቀሰቀስበት...

 መፍትሔ  ያላዘለው  የጎዳና  መደብሮችን  ማፍረስ

በአበበ ፍቅር ያለፉት ስድስት ዓመታት በርካቶች በግጭቶችና በመፈናቀሎች በከፍተኛ ሁኔታ...

የተናደው ከቀደምቱ አንዱ የነበረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ መናገሻ ከተማቸውን...

የአከርካሪ አጥንት ሕክምናን ከፍ ያደረገው ‘ካይሮፕራክቲክ’

በአፍሪካ ከጀርባ ሕመም ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ የአካል...