Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

ቀን:

በዚህ የ‹‹ኮሜዲ›› በሚመስል አስገራሚ ዘመን ብዙ ሰዎች ቀልደኛ ለመሆን ሲውተረተሩ ይታያሉ፡፡ ለዛሬው ገጠመኜ መነሻ የሆኑኝን አንዳንድ ትውስታዎችን አቅርቤ ወደ ጉዳዬ አመራለሁ፡፡ አንድ ጊዜ ጫማዬን የሚያሳምርልኝ ታዳጊ ከሊስትሮ ሳጥኑ አጠገብ ሁለት ደብተሮች አስቀምጧል፡፡ የልጁ ብልህነት አስደስቶኝ፣ ‹‹ጎበዝ ልጅ በርታ፡፡ ማታ ማታ ትማራለህ እንዴ?›› ስለው በመገረም እያየኝ፣ ‹‹ኧረ እኔ አልማርም፤›› አለኝ፡፡ እኔም ደንገጥ ብዬ፣ ‹‹እነዚህ ደብተሮች የማናቸው ታዲያ?›› በማለት ጠየቅኩት፡፡ እሱም ሳቅ እያለ፣ ‹‹እነዚህ? እነዚህማ የቀን ውሎዬን የምጽፍባቸው ናቸው፤›› አለ፡፡ ማስታወሻ የመያዝ ልምድ በሌለበት አገር ውስጥ ይህ ትንሽ ልጅ ከየት እንዳመጣው ገርሞኛል፡፡

ልጁ እንደነገረኝ ከሆነ ከኃላፊ አግዳሚው የሚሰማውን ቀልድና ተረብ ደብተሮቹ ውስጥ ይከትባል፡፡ ‹‹ምን ያደርግልሃል?›› ለሚለው ጥያቄ የሰጠኝ መልስ ፈገግ ያደርጋል፡፡ ‹‹ቀልዶች ተጠራቅመው አይደል የኮሜዲ ፊልሞች የሚሠሩት? እኔም የምሰማቸውን ቀልዶችና ተረቦች አጠራቅሜ ካቀነባበርኩኝ በኋላ ፊልም ለሚሠሩ ሰዎች በደህና ገንዘብ እሸጣቸዋለሁ፡፡ ከዚያም ድህነትን ደህና ሰንብት እላለሁ፤›› አለኝ፡፡ በጣም ገርሞኝ፣ ‹‹ለመሆኑ ይህንን ዘዴ የነገረህ ማነው?›› ስለው፣ ‹‹ከኑሮ በላይ ማን አስተማሪ አለ?›› ሲለኝ ሌላ ጥያቄ አልነበረኝም፡፡ ተሰናብቼው መንቀሳቀስ ከጀመርኩ በኋላ ገርሞኝ ዞር ብዬ ሳየው ምላሱን እያወጣ እያሾፈብኝ ነበር፡፡ ለካ በእኔ ላይ ቀልድ እየተለማመደ ነበር፡፡

አንድ ጊዜ ደግሞ ሥጋ ለመግዛት መኖሪያ አካባቢዬ የሚገኝ ሉኳንዳ ቤት እሄዳለሁ፡፡ ሥጋ ቆራጩ ቢላውን እያፏጨ፣ ‹‹ስንት ኪሎ?›› አለኝ፡፡ ከመቁረጡ በፊት ዋጋው ስንት እንደሆነ ስጠይቀው፣ ‹‹የቁርጥ 650 ብር፣ የክትፎ 700 ብር፣ የወጥ 500 ብር፣ እዚህ ከሆነ ደግሞ 750 ብር…›› ብሎ ዘረዘረልኝ፡፡ በዋጋው ሥሌት መሠረት የኪሴን አቅም ካገናዘብኩ በኋላ አንድ ኪሎ የቁርጥና አንድ ኪሎ የወጥ ሥጋ አዝዤ ሰውየው መቁረጥ ጀመረ፡፡ በዚህ መሀል፣ ‹‹ለመሆኑ በዚህ ውድ ዋጋ እየሸጣችሁ ገበያ አለ እንዴ?›› የሚል ጥያቄ አቀረብኩለት፡፡ ሥጋ ቆራጩ ዛሬ ገና ሥጋ የምገዛ መስዬው ይሆን ወይም በሌላ ምክንያት አላውቅም፣ ምኑንም ምኑንም ቆራርጦ ሚዛን ላይ ካስቀመጠ በኋላ፣ ‹‹ወይ ጊዜ ድንችና ሥጋ የማይለዩ ይመጡብን ጀመር?›› ብሎ ሲያሽሟጥጥ ቴአትር የሚሠራ ይመስል ነበር፡፡

በጣም ተናድጄ ስለነበር፣ ‹‹ሰማህ እኔ እኮ ለሥጋ እንግዳ ወይም ባዕድ አይደለሁም፡፡ ከፈለግህ ከበሬው ጭንቅላት እስከ ጭራው ድረስ ያለውን የብልት ክፍል እጠራልሀለሁ፡፡ ስለዚህ ከሽንጥ፣ ከዳቢት፣ ከሳልገኝ አመጣጥነህ ስጠኝ…›› ብዬ ስንጣጣ ሳቀብኝ፡፡ ሳቁን ከጨረሰ በኋላ፣ ‹‹እንዴት አሪፍ ነህ እባክህ? እኔ እኮ ገበያ አላችሁ ወይ ስትለኝ በሆዴ የማነው ፋራ ብዬሃለሁ፡፡ ሥጋ የምታውቅ ከሆነ ለምን ሉኳንዳ ቤት አትከፍትም ነበር?›› ብሎ አላገጠብኝ፡፡ የማንም መቀለጃ መሆኔ እያናደደኝ፣ ‹‹በል በቃህ…›› ስል፣ ‹‹ኧረ ጌታዬ አትቆጣ፡፡ ውስጥ ገባ ብትል እኮ የአንበሳ ልደት የሚያከብሩ ስንት ጀግኖች አሉ መሰለህ፡፡ ያውም ሦስት ሆነው አምስት ኪሎ ጥሬ ሥጋ ጨርሰው ሁለት ኪሎ የጨመሩ…›› ሲለኝ በአላዋቂነቴ ይሆን በምን እንደሚቀልድ ሳላውቅ፣ ሒሳቤን ከከፈልኩ በኋላ የሰጠኝን ጉላንጆ ተሸክሜ ተለያየን፡፡ ይኼም አንድ ቀን የኮሜዲ ፊልም ስክሪፕት ይጻፍበት ይሆናል፡፡

ከላይ እንደገለጽኩት በትውስታዎቼ የጀመርኩት ለዛሬው ገጠመኜ እንዲመች ብዬ ነው፡፡ በቅርቡ ከጓደኞቼ ጋር ምሳ በልተን ቡና እየጠጣን አንድ ሞቅ ያለው ሰው መጣ፡፡ በእጁ የቆየ ጋዜጣ ይዟል፡፡ ሰውየው አጠገባችን ካለ ጠረጴዛ ወንበር ስቦ ተቀመጠ፡፡ ጋዜጣውንም ጠረጴዛው ላይ አስቀመጠ፡፡ ተንጠራርቼ ጋዜጣውን ሳይ የመጀመሪያ ገጽ ላይ ከላይ የሰፈረው ዜና ቀልቤን ሳበው፡፡ የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የ2010 ዓ.ም. ሪፖርት ለፓርላማ መቅረቡን የሚተነትነው ዜና በፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ያለውን የገንዘብ ብክነት፣ ሒሳብ አለማወራረድ፣ የተዝረከረኩ አሠራሮችና በርካታ ግድፈቶችን ይዟል፡፡ ይህንን የቆየ ጋዜጣ ከዚህ በፊት እኔም ሆንኩ ወዳጆቼ አላነበብነውም፡፡ ይህ የተለመደና አሳሳቢ የተባለ ችግር በፓርላማ ዕርምጃ እንዲወሰድበት በሪፖርቱ ላይ መካተቱን ዜናው ያስረዳል፡፡ ግሩም ነው፡፡ ይህ ለዓመታት ሲንከባለል የመጣ ችግር አሁንም መፍትሔ ሳያገኝ መቀጠሉ ይታወቃል፡፡ ለሌብነትና ለዘረፋ የተመቻቹ አሠራሮች አሁንም አሉ፡፡ ደንብና መመርያ እየተጣሰ የሚፈጸሙ ግዥዎችና የግንባታ ሥራዎች መብዛታቸው ዛሬም ራስን ያሳምማል፡፡ እኔና ጓደኞቼ አምስት ዓመታት ሊሞሉት ትንሽ የቀረውን ዜና አንብበን ከጨረስን በኋላ የጦፈ ውይይት ይዘናል፡፡ እልህ በተሞላበት ሁኔታ ነበር የምንነጋገረው፡፡ እኛም እኮ እንገርማለን፡፡

ውይይታችንን በፅሞና ሲሰማ የነበረው አንድ ጓደኛችን እኛ በኃይለ ቃል የምንነጋገርበትን ጉዳይ ወዲያው ቀየረው፡፡ ይህ ጓደኛችን ለዓመታት እንዲህ ዓይነት ሪፖርት ይቀርብ እንደነበር አስታውሶ፣ ከዓመታት በፊት ይሠራበት የነበረው አንድ የዕርዳታ ድርጅት ውስጥ የሥራ ማስኬጃ ሒሳብ የሚያንቀሳቅስ ሰው በአንድ ወር ውስጥ የ600 ሺሕ ብር ጉድለት ተገኘበት አለን፡፡ ሰውየው መሸት ሲል ውስኪ ቤት ጎራ እያለ መጎንጨት በመልመዱ ምክንያት በአንድ ወር 600 ሺሕ ብሩን አጨብጭቦበታል፡፡ ያገኘውን ሁሉ ጠርሙስ እያወረደ እየጋበዘ፡፡ የድርጅቱ ኃላፊ፣ ‹‹እስካሁን ያልታየብህ የሒሳብ ጉድለት ከየት መጣ?›› ሲሉት እንደ ቀልድ፣ ‹‹ውኃ ወስዶት ነው…›› ይላቸዋል፡፡ በእሱ ቤት መቀለዱ ነው፡፡ በአነጋገሩ የተናደዱት ኃላፊ፣ ‹‹እምነት በማጉደል ወንጀል ከስሼ አስቀጣሃለሁ…›› በማለት ሲያስፈራሩት፣ ‹‹እንኳን እኔ አንድ ደሃ ብዙዎቹ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በቢሊዮን የሚቆጠሩ ብሮችን አጥፍተው ማን ጠየቃቸው?›› ብሎ መለሰላቸው፡፡ ‹‹ሰውየው የዋዛ አልነበሩምና ተከሶ እስራት ተፈርዶበት እስር ቤት ተላከ፡፡ አሁንም ከሳሽና ቀጪ ከሌለ ቢሊዮኖች ጠፉ፣ ሒሳብ አይወራረድም፣ ብክነት አለ፣ ዕርምጃ ይወሰድ የሚል ጩኸት ብቻውን ዋጋ የለውም…›› አለን፡፡ አሁንማ ሌብነቱና ዝርፊያው ከማስደንገጡ የተነሳ ራሱን የቻለ የታሪክ ክፍል ሳይፈጠርለት አይቀርም፡፡ ይመዘገባል ለማለት ነው፡፡

ጠያቂና ተጠያቂ በጠፉበት ጊዜ አንጀትን ከማሳረር መቀለድ የሚሻል መሰለኝ፡፡ የዘመኑ የኮሜዲ ፊልም ደራሲያን ምነው እንዲህ ዓይነቱን ነገር ቢደፍሩ? ነው ወይስ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ለኮሜዲ አይመጥኑም? ‹‹ቢሊዮኖች የት ኮበለሉ?›› በሚል ርዕስ ኮሜዲ ፊልም ቢሠራ እኮ የሚሊዮኖችን ቀልብ መሳብ ይቻላል፡፡ ከዚያም ሚሊዮን ብሮችን ማፈስ ነው፡፡ ይህ አልበቃ ካለ ደግሞ ሕዝብን ከቀዬው አፈናቅለው የተላከለትን ዕርዳታ ቅርጥፍ አድርገው የሚበሉትንም መርሳት አይገባም፡፡ ይህም አልበቃ ብሎ በሕዝብ ስም ደም እያፈሰሱ በጀግንነት የሚያናፉትን ማካተት ቢታከልበት መልካም ነው፡፡ አደራ አስቡበት፡፡ ከቀለዱ አይቀር እንዲህ ነው፡፡

(አመሐ ሳህሌ፣ ከፒያሳ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አወዛጋቢው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ

በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ የሚቀሰቀስበት...

 መፍትሔ  ያላዘለው  የጎዳና  መደብሮችን  ማፍረስ

በአበበ ፍቅር ያለፉት ስድስት ዓመታት በርካቶች በግጭቶችና በመፈናቀሎች በከፍተኛ ሁኔታ...

የተናደው ከቀደምቱ አንዱ የነበረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ መናገሻ ከተማቸውን...

የአከርካሪ አጥንት ሕክምናን ከፍ ያደረገው ‘ካይሮፕራክቲክ’

በአፍሪካ ከጀርባ ሕመም ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ የአካል...