- ሽግሽጉ ከሚደረግባቸው መካከል የአዲስ አበባና የባህር ዳር ደርቢዎች ይገኙበታል
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ2015 ዓ.ም. ውድድር መርሐ ግብርን የተመልካቾች ቁጥርን ታሳቢ በማድረግ የጨዋታ ሳምንት ማሸጋሸጉ ተሰማ፡፡
የዘንድሮን የውድድር ሰሌዳ ሐምሌ 26 ቀን 2014 ዓ.ም. ዕጣ በማውጣት ይፋ ያደረገው የሊጉ አክሲዮን ማኅበር፣ የጨዋታ ሳምንቶች ላይ ሽግሽግ ያደረገው በርካታ ተመልካቾች ሊታደሙበት ይችላሉ ያላቸውን ነው፡፡
በዚህም መሠረት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኢትዮጵያ ቡና፣ ፋሲል ከነማ ከባህር ዳር ከተማ እንዲሁም ሲዳማ ቡና ከወላይታ ዲቻ የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች የቀን መሸጋሸግ ተደርጎባቸዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ይፋ ሆኖ በነበረው መርሐ ግብር መሠረት፣ ፋሲል ከነማ ከባህር ዳር ከነማ በ3ኛ ሳምንት በባህር ዳር ስታዲየም፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኢትዮጵያ ቡና በ12ኛ ሳምንት በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የሚያደርጉት ጨዋታዎች እንዲሁም የወላይታ ዲቻና የሲዳማ ቡና የ11ኛ ሳምንት ጨዋታ ላይ ሽግሽግ እንደሚደረግ ይጠበቃል፡፡
የጨዋታዎቹ ሳምንታት የመሸጋሸግ ዋነኛ ምክንያት የተመልካቾችን ቁጥር ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆኑን የሚጠቅሱት የሪፖርተር ምንጮች፣ በዚህም መሠረት በርካታ ተመልካች ያላቸውን የጨዋታ ሳምንቶች ለክለቦቹ ቅርብ በሆኑ ስታዲየሞች ላይ ጨዋታቸውን ለማከናወን መታቀዱን ያነሳሉ፡፡
ከዚህም ባሻገር በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ እየተሳተፈ የሚገኘው ፋሲል ከነማ በቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ የቡሩንዲውን ቡማሙሩ 3 ለ 1 በሆነ ድምር ውጤት ረትቶ ወደ ቀጣይ የምድብ ጨዋታ መሻገሩን ይታወሳል፡፡
ፋሲል ቀጣይ የማጣሪያ ጨዋታውን መስከረም 24 ቀን 2015 ዓ.ም. በባህር ዳር ስታዲየም የሚያከናውን በመሆኑና የፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያ ዙር መርሐ ግብር በባህር ዳር ስታዲየም መሆኑን ተከትሎ የጨዋታ መርሐ ግብር ሽግሽግ እንደሚደረግ ተጠቅሷል፡፡
እንደ ምንጮች አስተያየት ከሆነ፣ የዘንድሮን የቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊግ መርሐ ግብር የሚያስተናግዱትን የስታዲየሞች ቅደም ተከተል በመከተል በርካታ ተመልካቾች የሚታደሙባቸውን ጨዋታዎች ለተመልካቹ ቅርብ በሆኑ ስታዲየሞች እንዲደረጉ ታሳቢ ያደረገ ሽግሽግ እንደሚደረግ ተጠቅሷል፡፡
አክሲዮን ማኅበሩ የ2015 ዓ.ም. ውድድር መክፈቻ መስከረም 20 ቀን 2015 ዓ.ም. በባህር ዳር ስታዲየም የሚያከናውን ሲሆን በተከታታይም በድሬዳዋ፣ አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም እንዲሁም ማጠናቀቂያውን በአዲስ አበባ ከተማ እንደሚያደርግ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡
ሆኖም ዘንድሮ ተመልካቾች በስታዲየም እንዲታደሙ መታቀዱን ተከትሎ፣ በርካታ ተመልካቾች ይታደሙባቸዋል ተብለው የሚታሰቡ ስታዲየሞችና ጨዋታዎች ከግምት ውስጥ ገብተው እንደ አስፈላጊነቱ ለውጥ ሊደረግባቸው እንደሚችል አክሲዮን ማኅበሩ ጠቅሷል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘም ከተጠቀሱት የክልል ከተሞች ባሻገር ለውድድር ብቁ ሆኖ የተገኘ ስታዲየም የተሻለውን መርጦ ውድድሩን የማከናወን ጭምር አማራጭ እንዳለ አክሲዮን ማኅበሩ አስታውቋል፡፡
የኮቪድ-19 ወርርሽኝ መከሰትን ተከትሎ ከሁለት ዓመታት በላይ ተገድቦ የቆየው የተመልካቾች ቁጥር፣ በዘንድሮ ውድድር ላይ ዕገዳው እንደሚነሳ የሚጠበቅ ሲሆን፣ በተመልካቾች ዕጦት ተመተው የከረሙት ስታዲየሞች ተመልካች ይታደምባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የተመልካቾችን የሚገድበው የኮቪድ-19 ፕሮቶኮል በግልጽ መነሳቱ ይፋ ባይሆንም፣ በአንፃሩ አክሲዮን ማኅበሩ ዘንድሮ ባወጣው መርሐ ግብር ላይ በቀዳሚነት ተመልካቾችን ተሳቢ ያደረገ እንደሆነ ተገልጿል፡፡