Sunday, March 3, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የድጎማ በጀት ለፖለቲካ ሥራ ማስፈጸሚያ እንደሚውል የሚያሳይ ሪፖርት ቀረበ

የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የድጎማ በጀት ለፖለቲካ ሥራ ማስፈጸሚያ እንደሚውል የሚያሳይ ሪፖርት ቀረበ

ቀን:

ለመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የሚደረግ የበጀት ድጎማ ከመደበኛው ሥራ ይልቅ ከዋናው ተልዕኮ ውጪ ለሆነ የፖለቲካ ሥራ እንደሚውል፣ የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ሪፖርት አስታወቀ፡፡

ሪፖርተር ከምንጮቹ ያገኘውና ኮሚሽኑ በተመረጡ 61 ተቋማት ላይ ያደረገው የጥናት ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ ከመምህራን ልማትና ከአሠልጣኞች ምልመላ ጋር በተገናኘ፣ የዘመድና የፓርቲ አሠራር፣ እንዲሁም አድልኦና ጉቦ የመቀበል አዝማሚያ በስፋት ይስተዋላል፡፡

ኮሚሽኑ ጥናቱን ያከናወነው በፌዴራል ደረጃ በሚገኙ የመንግሥትና የግል ዩኒቨርሲቲዎች ሲሆን፣ የጥናቱ ትኩረት ሙስናና ብልሹ አሠራር በትምህርት ዘርፍ ላይ የሚያደርሰውን የሙስና ሥጋት ለመለየት መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በመምህራንና ሠራተኞች አስተዳደር ክፍል ሕገወጥ ቅጥርና ዝውውር መኖር፣ መምህራን ተማሪዎችን ለይቶ ለመጥቀም የሚደረግ ዝንባሌ መኖር፣ ለመምህራን ቅጥር ውድድር ተፈልጎ እኩል ውጤት ሲመጣ፣ አንዱን በትውውቅ ብቻ የመምረጥ አሠራር እንደሚስተዋል በጥናቱ ተገልጿል፡፡

ከሐሰተኛ የትምህርት ሰነድ ጋር በተያያዘ የብቃት ማረጋገጥና ፈቃድ አሰጣጥ ላይ መሥፈርት ሳያሟሉ፣ ለተቋማት ፈቃድ መስጠትና የፈቃድ ዕድሳት እንደሚከናወን በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

በሌላ ቡከል በመምህራንና የትምህርት አስተዳደር አመራር ላይ ያሉ ሠራተኞች፣ ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ እንደተገኘባቸው፣ ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃን ለማጣራት ሲሞከር ደግሞ ሠራተኞች ከሥራ ቀድመው የመልቀቅ እንቅስቃሴ፣ በግል ኮሌጆች የሲኦሲ ምዘና ሳያልፉና ትምህርት አጠናቀው ሳይጨርሱ፣ እንዲሁም ፈጽሞ ያልተማሩ ሰዎች የትምህርት ማስረጃ አትሞ መስጠትና በኮሌጆች ሽያጭ የመፈጸም ድርጊት መኖሩን ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡

በተመሳሳይ በኮሌጆችና በዩኒቨርሲቲዎች ሬጅስትራሮች ውስጥ የተማሪዎችን ውጤት የማሳሳትና የማጭበርበር ድርጊት እንዳለ የተጠቀሰ ሲሆን፣ ሪፖርቱ እንደሚያሳየው በግል ትምህርት ተቋማት ውሳኔዎች የሚተላለፉት ለተቋማቸው መልካም ስም ቅድሚያ በመስጠት እንደሆነ፣ በመንግሥት ተቋማት ደግሞ ሰነድ ማዘጋጀት እንጂ ትግበራ ላይ እምብዛም የሉበትም ተብሏል፡፡

በተደረገው ጥናት በተቋማቸው ውስጥ የመልካም አስተዳደር ችግሮች አሉ ወይ ተብለው ከተጠየቁት ውስጥ 65 በመቶ የሚሆኑት ‹‹አዎ›› የሚል መልስ መስጠታቸውን፣ 35 በመቶ የሚሆኑት ‹‹የለም›› የሚል መልስ ሲሰጡ፣ በተመሳሳይ የሙስና ችግሮች መኖራቸውን 66 በመቶ መናገራቸውና፣ 47 በመቶ ደግሞ ለሚቀርቡ ጥቆማዎች ከተቋማቱ መልስ እንደማይሰጥ ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡

ሪፖርቱ እንደሚያሳየው በትምህርት ተቋማቱ የመምህራን በተደጋጋሚ ወደ ክፍል አለመግባት፣ ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ መስጠት፣ በአመራር የሚከናወን ስርቆት፣ ሕገወጥ ዝውውርና የደረጃ ዕድገት፣ ሕግና ደንብን ተከትሎ የማይከናወን ግዥ፣ የመረጃና ማስረጃ ማጭበርበር፣ ግልጽነት የሌለው አሠራር መብዛት፣ በሬጅስትራር የሚፈጸም ብልሹ አሠራር ተቋማቱን ለከባድ ሙስና አደጋ ጥሏቸዋል፡፡

በተመሳሳይ በግዥ ወቅት ለተቋም የማያስፈልግ ንብረት እንዲገዛ ተጨማሪ በጀት ማስያዝ፣ በጨረታ ወቅት የተወሰኑ ሰዎችን ብቻ እንዲጋብዝ አድርጎ ሰነድ ማዘጋጀት፣ ወቅቱንና ጥራቱን ያልጠበቀ ግንባታ እንዲከናወን ማድረግ፣ በሕንፃ ርክክብ ጥራቱን ያልጠበቀ ሕንፃ እንዲገነባ ማድረግና ያልተጠናቀቀ ሕንፃ መረከብ ተቋማቱን ለከባድ ሙስና እንዳጋለጣቸው ተመላክቷል፡፡

እንደ ምክንያት ከተጠቀሱት ችግሮች መካከል የሠራተኞች ዝቅተኛ የደመወዝ ክፍያ፣ የተጠናከረ የቁጥጥር ሥርዓት አለመኖር፣ የሞራል መላሸቅ፣ የተጠያቂነት ማነስ፣ የላላ የአመራር ቁጥጥርና ከፍተኛ የሆነ የበጀት ምደባ የሚሉት ይገኙበታል፡፡

የኮሚሽኑን ሪፖርት በተመለከተ በተቋማቱ የተነሳው የአሠራር ችግር ላይ አስተያየታቸውን እንዲሰጡ የተጠየቁ የትምህርት ሚኒስትር የበላይ ኃላፊዎችን ለማግኘት አልተቻለም፡፡

የትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊው አቶ ታረቀኝ ገረሱ በግል ትምህርት ቤቶች ውስጥ ይታያል የተባለውን የአሠራር ብልሹነት አስመልክተው ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ምንም እንኳ ችግሮቹ ቢኖሩም ባለሥልጣኑ በተለያዩ ጊዜያት መመርያና ደንብ በማውረድ ክትትል ያደርጋል፡፡

ባለፉት ሦስት ዓመታት በተደረገ ጥረት ወደ 200 የሚደርሱ የትምህርት ተቋማትና ቅርንጫፎቸቻቸው ላይ፣ ተቋማቱን ከማስጠንቀቅ ጀምሮ እስከ ፈቃድ መሰረዝና መዝጋት የሚደርስ ዕርምጃ መውሰዳቸውን ኃላፊው አክለው ተናግረዋል፡፡

ከግል ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች የሚመረቁ ተማሪዎች የሚያገኙት ዲግሪ በባለሥልጣኑ ሳይረጋገጥ ወደ ቅጥር መሄድ እንደማይቻል የገለጹት ኃላፊው፣ ከየትኛውም የግል ዩኒቨርሲቲ የሚመጣ ዲግሪ ከምረቃ በኋላ በባለሥልጣኑ መረጋገጥ አለበት ብለዋል፡፡

ባለሥልጣኑ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የሚገኙ ከ300 በላይ የሚደርሱ የግል ተቋማትን ለመቆጣጠር አደረጃጀቱን እያስፋፋ መሆኑን የገለጹት አቶ ታረቀኝ፣ በእያንዳንዱ ትምህርት ቤት ክትትል በማድረግ በመጀመርያ ዓመት ከተመዘገቡ ተማሪዎች ውጪ በመጨረሻ ዓመት ሲመረቁ፣ አዲስ የሚገባ የተማሪ ስም እንዳይኖር በባለሥልጣኑ ዲጂታል ዳታ ማዕከል ቁጥጥር እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡

ኮሚሽኑ ጥናቱን ባካሄደበት ወቅት የተቋማት አመራሮች በቦታው አለመገኘት፣ ተቋማት መረጃ ለመሥራት ፈቃደኛ አለመሆን፣ የተቋማት አመራርና ሠራተኞች መረጃዎችን በተጨባጭ መረጃ ላይ ተመሥርቶ አለመስጠት መሰል ዓይነት ችግሮች እንደነበሩ ተጠቅሷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...