Thursday, November 30, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

መንግሥት የሥራ ግብር ምጣኔን እንዲቀንስ ተጠየቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) መንግሥት የሠራተኛውን የኑሮ ጫና ታሳቢ በማድረግ፣ በቅጥር ገቢ ላይ የሚጣለውን የግብር ምጣኔ እንዲቀንስ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትን ጨምሮ ለገንዘብ ሚኒስቴር ጥያቄ አቀረበ፡፡

የኮንፌዴሪሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ ለሪፖርተር እንዳስረዱት፣ በ19ኛው የኢሠማኮ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ማጠቃለያ በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት፣ ሠራተኛው ዝቅተኛ የደመወዝ ወለልን ጨምሮ ካለው የኑሮ ውድነት አንፃር የሥራ ግብር እንዲቀነስ መንግሥት ይጠየቅ የሚል ጥያቄ ቀርቧል፡፡

‹‹ሠራተኛው በቀን ሦስት ጊዜ ቀርቶ አንድ ጊዜ በልቶ ማደር ያልቻለበት ደረጃ ላይ ደርሷል›› ያሉት አቶ ካሳሁን፣ መንግሥትን ‹‹በጀት አውጥተህ ደጉም›› ማለት ስለማይቻል በሌሎችም አገሮች የኑሮ ውድነት ሲከሰት እንደሚደረገው ሁሉ የሥራ ግብር ምጣኔ መቀነስ እንደሚጠበቅበት አስረድተዋል፡፡

በፌዴራል ገቢ ግብር አዋጅ 983/2008 እንደተደነገገው፣ ማንኛውም ተቀጣሪ የሚያገኘው ጠቅላላ የወር ገቢ ከ601 ብር በላይ ሲሆን፣ ከአሥር በመቶ አንስቶ፣ እስከ 35 በመቶ የሚደርስ የግብር ምጣኔ ይጣልበታል፡፡

ወርኃዊ ገቢው ከ600 ብር በላይ ከሆነ ሠራተኛ የሥራ ግብር እንደሚቆረጥበት ያስታወሱት አቶ ካሳሁን፣ ካለው ወቅታዊ የኑሮ ውድነት አኳያ ምጣኔው የተቀመጠበት የወር ገቢ ከፍ ሊል ይገባል ብለዋል፡፡ መንግሥት ሠራተኛውን መደገፍ ከፈለገ፣ አንዱ ማድረግ የሚችለው በዚህ ዓይነት መንገድ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ከ10,900 ብር በላይ ወርኃዊ ገቢ በሚያገኙ ሠራተኞች ላይ የሚጣለው የ35 በመቶ የግብር ምጣኔ፣ ዝቅ ሊል እንደሚገባው የኮንፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አስረድተዋል፡፡

ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው የሚሠሩ የድርጅት ሠራተኞች በወር የሚያገኙት የትራንስፖርት አበል ከስድስት መቶ ብር በላይ ከሆነ ግብር እንደሚጣልባቸው የተናገሩት አቶ ካሳሁን፣ በቀን ቢሰላ ከ20 ብር የማይበልጥ ገንዘብ እንደ ተጨማሪ ገቢ ተቆጥሮ ከላዩ ላይ ተቀናሽ መደረጉ ፍትሐዊ አይደለም ብለዋል፡፡

ሌሎችም ከሥራ ግብር የተያያዙ ጥያቄዎችን የኮንፌዴሬሽኑ ጠቅላላ ጉባዔ በሰጠው አቅጣጫ መሠረት ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በጽሑፍ መቅረቡ የተገለጸ ሲሆን፣ አዋጁ በገንዘብ ሚኒስቴር የወጣ ስለሆነ ለገንዘብ ሚኒስቴር እንዲሁ ምጣኔው እንዲሻሻል በቀጥታ ደብዳቤ መጻፉ ታውቋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ለሥራና ክህሎት ሚኒስቴር እንዲሁ ጥያቄው መቅረቡን አቶ ካሳሁን ተናግረዋል፡፡

የኑሮ ቀውስ በሚኖርበት ወቅት የሥራ ግብር ምጣኔ እንዲቀነስ መጠየቅ  በደሃ አገሮች ብቻ ሳይሆን በአደጉ አገሮችም የሚጠየቅ መሆኑን ያስታወቁት የኢሠማኮ ፕሬዚዳንት፣ የኮንፌዴሬሽኑ ጥያቄም ከዚያ አኳያ የሚታይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለልን የተመለከተ ጥያቄን ኮንፌዴሬሽኑ ቀደም ብሎ ለሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶች ማቅረቡ ይታወቃል፡፡ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለልን በሚመለከት በረቂቅ ደንቡ ላይ ውይይት እንደተደረገ፣ ረቂቁም በቀድሞው የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቢቀርብም ታይቶ ወደ ሥራ አለመግባቱን ያመላከተው ኮንፌዴሬሽኑ፣ ነገር ግን ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል አንዱ የኑሮ ውድነትና መነሻ በመሆኑ ደንቡ በሚኒስትሮች ምክር ቤት አማካይነት እንዲወጣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ኢሠማኮ ደብዳቤ መጻፉ ተገልጿል፡፡

ለአብነት ኬንያ  በግንቦት ወር የዓለም አቀፍ የላብ አደሮች ቀን ሲከበር ከዚህ ቀደም በሥራ ላይ የነበረውን ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል የኑሮ ውድነትን ከግምት ውስጥ በመክተት፣ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ አደባባይ ተገኝተው ዝቅተኛ የደመወዝ ወለሉን በአዋጅ በስድስት በመቶ እንዲጨምር ማስደረጋቸውን ያስታወሱት አቶ ካሳሁን፣ ኢትዮጵያ ከመነሻውም ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል የሌላት አገር መሆኗንና መንግሥት በጉዳዩ ላይ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥበት መጠየቁን አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች