Wednesday, June 7, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ብልሹ አሠራሮች እንዲወገዱ ሕግና ሥርዓት ይከበር!

በኢትዮጵያ ምድር ጦርነትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አጠናቆ ሙሉ ለሙሉ ፊትን ወደ ልማት ለማዞር ያለው ፍላጎት አሁንም ፈተና እየገጠመው ነው፡፡ ኢትዮጵያ አዲሱ ዓመት ሲብት በሙሉ ኃይል በሁሉም መስኮች ልማቷን ለማቀላጠፍ እንድትችል መልካም ምኞቶች ቢሰሙም፣ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት መቼ እንደሚጠናቀቅ ለማወቅ አዳጋች የሆነ ይመስላል፡፡ እየተካሄደ ያለውን ጦርነት በተመለከተ ይፋዊ መረጃ ባለመኖሩ ማቆሚያው መቼ ይሆን የሚለው ብዙዎችን ያሳስባል፡፡ ጦርነት የሰዎችን ሕይወት ብቻ ሳይሆን የአገርንም ሀብት እንደ እሳት የሚበላ በመሆኑ፣ ከደሃ አገር የተጣበበ በጀት ላይ ብዙውን እንደሚያወድም የታወቀ ነው፡፡ ጦርነት ማለት በእጅ ያለ ገንዘብን እየጠቀለሉ እሳት ውስጥ መክተት ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ የምግብም ሆነ ምግብ ነክ ያልሆኑ ምርቶች ዋጋ አልቀመስ እያለ ነው፡፡ በዜጎች ገቢ ላይ ምንም ዓይነት ለውጥ ሳይታይ ኑሮን በአስከፊ የዋጋ ግሽበት መምራት ከአቅም በላይ እየሆነ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የገጠማትን አስከፊ ፈተና በፍጥነት ወደ ልማት እንድትሸጋገር መደረግ አለበት፡፡ በሁሉም መስኮች የተትረፈረፉ ምርቶች ለማግኘት የሚያስችል መደላድል ይፈጠር፡፡

ዘንድሮ ይጀመራል የተባለው አገራዊ የምክክር መድረክ ስኬታማ ሆኖ ሁሉም ልዩነቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ፣ በኢትዮጵያ ምድር የጦረኝነት አባዜ ቆሞ ለውይይት ዕድሎች እንዲመቻቹና የጠላትነት ስሜት እንዲወገድ ኢትዮጵያውያን በአንድነት መተባበር አለባቸው፡፡ ለዘመናት ምንም ሳታጣ በድህነት ውስጥ ተዘፍቃ የኖረች አገር ውስጥ ልዩነትን በሠለጠነ መንገድ መፍታት ባህል እንዲሆን፣ ለአገራዊ ምክክር መድረኩ ልዩ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ በእኩልነትና በነፃነት የሚኖርበት ሥርዓት ማቆም የሚቻለው፣ በሁሉም ብሔራዊ ጉዳዮች ላይ በመነጋገር ስምምነት ሲፈጠር ነው፡፡ ችግሮች ሲያጋጥሙ ጦር ከመነቅነቅ ይልቅ ተቀምጦ ለመነጋገር የሚያስችል ባህል ማዳበር ተገቢ ነው፡፡ ልዩነቶች ተከብረው በሥርዓት መነጋገር መቻል ያስፈልጋል፡፡ ሲመች ጉልበት ለማሳየት መንጠራራት ሳይመች የድርድር ጥሪ ማድረግ በሕዝብ ሕይወት ላይ መቀለድ ነው፡፡ በተደጋጋሚ ለማስታወስ እንደተፈለገው የጥቂቶች ዕብሪትና ጥጋብ የሚፈጥረው ቀውስ አገርን እንዴት እንደበደለ ይታወቃል፡፡ በኢትዮጵያ ሕዝብ መሀል ይህ ነው የሚባል ለግጭት የሚዳርግ ቅራኔ ሳይኖር፣ በጥቂቶች የሥልጣን ጥማት ምክንያት የደረሰው መከራ አላባራ ማለቱ ሊያስቆጭ ይገባል፡፡

ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ ፍፁም ሰላም የሚያስፈልጋት ጊዜ ላይ ትገኛለች፡፡ ሰላም የሚሰፍነው ደግሞ በአንድ ወገን ፍላጎት ባለመሆኑ፣ ሁሉም ወገኖች ለሰላም መስፈን ቁርጠኝነታቸውን ማሳየት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በሕዝባችን ላይ የደረሰው ሥቃይና ሰቆቃ መቼም የሚረሳ አይደለም፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶችና በተፈጸሙ ጥቃቶች የደረሰው መከራ አይዘነጋም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በሁሉም ሥፍራዎች በሰላም ተንቀሳቅሶ ለመሥራት የማይቻልበት ጊዜ ውስጥ ነው ያለነው፡፡ ግጭቶች ባሉበት እንኳን ከድህነት ለመውጣት በሰላም ወጥቶ መግባት ብርቅ ነው የሚሆነው፡፡ በ21ኛው ክፍለ ዘመን በሰላማዊ መንገድ ተነጋግሮ ችግርን መፍታት ሲያቅት ያሳዝናል፡፡ በጦረኝነት አባዜ ውስጥ ያሉ ኃይሎች በዚህ ዘመንም ጉልበትን የፍላጎት ማስፈጸሚያ ሲያደርጉ ማየት ያሳቅቃል፡፡ በዚህ በሠለጠነ ዘመን በአጉል ጀብደኝነት ጦርነት እየቀሰቀሱ ሕዝብንና አገርን ችግር ውስጥ መክተት፣ ከአደገኛ ቁማርተኝነት ተለይቶ አይታይም፡፡ በስሙ የሚነገድበት ሕዝብም ይህንን ቁማርተኝነት ተገንዝቦ በቃ ሊል ይገባል፡፡ ጥቂቶች ለሥልጣንና ለሚያስገኘው ሀብትና ክብር ሲሉ በሚቆሰቁሱት እሳት የሚቃጠሉት ንፁኃን እንደሆኑ ማንም አይስተውም፡፡

ኢትዮጵያ ለሥራ ከደረሰ ወጣት ኃይሏ በተጨማሪ በተፈጥሮ ፀጋዎች የታደለች አገር ናት፡፡ በርካታ ሚሊዮን ሔክታሮች ያልታረሱ ለም መሬቶቿ ከተሠራባቸው ክረምት ከበጋ ማምረት ይችላሉ፡፡ በበጋም ሆነ በክረምት በሚከናወኑ የእርሻ ሥራዎች ከኢትዮጵያ አልፈው የአፍሪካንና የዓለምን ገበያዎች የሚያጣብቡ ምርቶች ማግኘት አያቅትም፡፡ ሁሉንም የምግብ ምርቶች፣ አትክልትና ፍራፍሬዎች፣ እንዲሁም ለማጣፈጫ የሚውሉ ቅመማ ቅመሞች በማምረት ከፍተኛ የኤክስፖርት ገቢ ማግኘት ይቻላል፡፡ ለምግብ ዘይት ኢንዱስትሪዎች የሚውሉ የቅባት እህሎችን በብዛት በማምረት ዳጎስ ያለ ገቢ ይገኛል፡፡ የማዕድን ሀብቶቿ በጣም ብዙ ከመሆናቸው የተነሳ በዚህ ዘርፍ ጠንክሮ መሥራት ከተቻለ ተዓምር ማሳየት አያቅትም፡፡ በአራቱም ማዕዘናት የሚገኙት የቱሪዝም መስህቦች በሚገባ ከተሠራባቸው፣ ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ የቱሪስቶች መዳረሻ ትሆናለች፡፡ ከሞራልና ከሥነ ምግባራዊ እሴቶች ያፈነገጡ ሌብነቶችንና ዝርፊያዎችን በቁርጠኝነት ማስቆም የሚቻል ከሆነ፣ በኢትዮጵያ ማኅበራዊ ፍትሕ በማስፈን በፍጥነት ከድህነት ወለል ውስጥ ለመውጣት የሚያስቸግር ነገር አይኖርም፡፡ ኃላፊነት የማይሰማቸው የመንግሥት ሹማምንትና የአልጠግብ ባይ ነጋዴዎች ቁርኝነት እንዲበጠስ ከተደረገ፣ ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ፍትሐዊ የግብይት ሥርዓት ይፈጠራል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ እነዚህ ችግሮች ሚሊዮኖችን እየፈተኑም ነው፡፡ ነገር ግን ችግሮቹ በዙ ተብሎ እጅን አጣጥፎ መቀመጥ አይቻልም፣ አያዋጣም፡፡ የሚያዋጣው ችግሮቹ የሚቃለሉበትንና እስከወዲያኛው የሚወገዱበትን መፍትሔ መፈለግ ነው፡፡ ችግሮች መሀል ሆኖ ከመተከዝና ምን ይሻላል ብሎ ከመቆዘም ችግሮቹ በራሳቸው ጊዜ ይዘው የመጡትንም አጋጣሚ መጠቀም ይገባል፡፡ የብዙ አገሮች ልምድ የሚያሳየው በርካታ ፈጠራዎች የተገኙት በችግሮች ምክንያት ነው፡፡ ለዚህም ነው ‹‹ችግር የፈጠራ እናት ናት›› የሚባለው፡፡ ኢትዮጵያ ከገባችበት ጦርነት ውስጥ በፍጥነት እንድትወጣና ከሚያሰናክሏት ፈተናዎች እንድትገላገል፣ በሁሉም መስክ የተሰማሩ ልጆቿ ችግር ፈቺ መፍትሔዎች ላይ ማተኮር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ መተማመንና መደማመጥ ያስፈልጋል፡፡ ቅራኔ የሚያባዙ ጉዳዮች ላይ ሳይሆን ልዩነቶችን በማቀራረብ ለአገር ጥቅም ለመሥራትና ለመነጋገር ይተኮር፡፡ ከጠላትነት ይልቅ ወዳጅነትን የሚያበረታቱ ጉዳዮች ይብዙ፡፡ በጥላቻ፣ በቂም በቀል፣ በመገፋፋትና በመጠፋፋት ላይ የተመሠረቱ ዕሳቤዎች ይወገዱ፡፡ ከመጠን ያለፈ ራስ ወዳድነትና አድሎኛነት ተወግዶ እርስ በርስ መተሳሰብ ይለመድ፡፡ ችግሮች ሲያጋጥሙ ተባብሮ መፍትሔ መፈለግ የሚቻለው ጥላቻ ሲወገድ ነው፡፡

አሁንም እንደገና ማሳሰብ የሚያስፈልገው ሕግና ሥርዓት እንዲኖር ነው፡፡ ሕግና ሥርዓት በአስተማማኝ ሁኔታ ለማስፈን የተቋማት ግንባታ ላይ ማተኮር ያስፈልጋል፡፡ ተቋማት በጠንካራ አመራር፣ በብቁ ባለሙያዎች፣ በሠለጠኑ ሠራተኞችና ዘመኑ ባፈራቸው ቴክኖሎጂዎች ሳይደራጁ ስለሕግና ሥርዓት መነጋገር አይቻልም፡፡ ጠንካራ ተቋማት ሲኖሩ ኢኮኖሚው የሥርዓተ አልበኞች መጫወቻ አይሆንም፣ የግብይት ሥርዓቱ መረን አይለቀቅም፣ የጥቁር ገበያ ተዋንያን እንዳሻቸው እየፈነጩ ዋጋ ተማኝ አይሆኑም፣ ሸማቾች ለአልጠግብ ባይ ነጋዴዎች አይጋለጡም፣ በአጠቃላይ በኢኮኖሚው ውስጥ የሚስተዋሉ አሻጥሮችና ክፋቶች አገርን ችግር ውስጥ አይጥሉም ነበር፡፡ በተጨማሪም ተቋማት ሲጠናከሩ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ስለሚከበሩ በጥጋበኞች ምክንያት ማንም ሰው አይጎሳቆልም፣ አድሎአዊና አግላይ ብልሹ አሠራሮች አይሰፍኑም፣ የሕዝብና የመንግሥት ሀብትን ተደራጅተው የሚዘርፉ ሌቦች አይበረክቱም፡፡ ሕግና ሥርዓት እየተጣሰ ጥቂቶች ብዙኃንን መጫወቻ አያደርጉም፡፡ ስለዚህም የሕግ የበላይነት የሰፈነበት ሥርዓት ለመገንባት የሚያስችል መሠረት መጣል የሚቻለው፣ ጠንካራ ተቋማትን በመገንባት ከብልሹ አሠራሮች በመገላገል ነው፡፡ ብልሹ አሠራሮች እንዲወገዱ ሕግና ሥርዓት ይከበር!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

በኦሮሚያ ክልል በስድስት ከተሞች የተዋቀረውን ሸገር ከተማን የማደራጀት ሥራ ተጀመረ

በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ ስድስት ከተሞች የተዋቀረው ሸገር ከተማን...

የኦሮሞን ሕዝብ ታሪክ አልባ በማድረግ ታሪክ አይሠራም

በኢተፋ ቀጀላ​​  ከዛሬ ሃምሳ ዓመት ወዲህ ከተፈጠሩት የኦሮሞ ድርጅቶች መካከል ከኢጭአት በስተቀር፣...

ኢትዮጵያ በትክክለኛ ግንዛቤ ላይ የተመሠረተ ሕገ መንግሥት ማበጀት እንደሚገባት ማሳሰቢያ ተሰጠ

የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ከተረቀቀበት ጊዜ አንስቶ ለተለያዩ ጥያቄዎችና ሐሳቦች...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ኢዜማ ከለቀቁ አባላት ግማሽ ያህሉ የዲሲፒሊን ችግር የነበረባቸው ናቸው አለ

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) በቅርቡ ከፓርቲው አባልነት ለቀናል...

የአዲስ አበበ መምህራን ማኅበር የደመወዝ ጥያቄው ምላሽ ካላገኘ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚያቀርብ አስታወቀ

የአዲስ አበባ መምህራን ማኅበር ለረጅም ዓመት ያገለገሉ መምህራን ደመወዝና...

ኢሰመኮ በዩኒቨርሲቲዎች የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ጉዳይ የሚመራበት የጽሑፍ ፖሊሲ አለመኖሩን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች...

ንግድ ባንኮች በከፍተኛ የገንዘብ እጥረት ውስጥ መሆናቸው ተገለጸ

‹‹የገንዘብ እጥረት የሚገጥመው ያለውን ሀብት የማስተዳደር ችግር ስላለ ነው›› የኢትዮጵያ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሕገ መንግሥት ለማሻሻል ባህሪን መግራት ያስፈልጋል!

በሥራ ላይ ያለው አወዛጋቢ ሕገ መንግሥት ከፀደቀበት ከ1987 ዓ.ም. ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ወቀሳዎችና ተቃውሞዎች ይቀርቡበታል፡፡ ከተቃውሞዎቹ መካከል በሕገ መንግሥቱ መግቢያ ላይ ኢትዮጵያዊነትን...

የፖለቲካ ምኅዳሩ መላሸቅ ለአገር ህልውና ጠንቅ እየሆነ ነው!

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምኅዳር ከዕለት ወደ ዕለት የቁልቁለት ጉዞውን አባብሶ እየቀጠለ ነው፡፡ በፖለቲካ ፓርቲዎች የእርስ በርስ ግንኙነትም ሆነ በውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲ የሚታየው መስተጋብር፣ ውል አልባና...

የመኸር እርሻ ተዛብቶ ቀውስ እንዳይከሰት ጥንቃቄ ይደረግ!

ክረምቱ እየተቃረበ ነው፡፡ የክረምት መግቢያ ደግሞ ዋናው የመኸር እርሻ የሚጀመርበት ጊዜ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከእርሻው ክፍለ ኢኮኖሚ 70 በመቶ ያህሉን የሰብል ምርት የምታገኘው በመኸር እርሻ...