የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የማቋቋሚያ ካፒታል 500 ሚሊዮን ብርና ነባር ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ደግሞ በአምስት ዓመታት ውስጥ ካፒታላቸውን 500 ሚሊዮን ብር ማድረስ እንደሚኖርባቸው አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከትናንት በስቲያ ባወጣው መመርያ፣ እስካሁን 75 ሚሊዮን ብር የነበረው የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የማቋቋሚያ ካፒታል ከዚህ በኋላ 500 ሚሊዮን ብር እንዲሆን የሚያስገድድ መመርያ መስከረም 13 ቀን 2015 ዓ.ም. አፅድቋል፡፡
አሁን በሥራ ላይ ያሉትና ካፒታላቸው 500 ሚሊዮን ብር ያልደረሱ የኢንሹራንስ ኩባንያዎችም የተከፈለ ካፒታል መጠናቸውን በአምስት ዓመታት ውስጥ 500 ሚሊዮን ብር ማድረስ እንደሚኖርባቸው በመመርያው ላይ ተገልጿል፡፡
መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ አሁን በሥራ ላይ ከሚገኙ 18 የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ውስጥ የተከፈለ ካፒታላቸውን ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ያደረሱ ሰባት የኢንሹራስ ኩባንያዎች ብቻ ናቸው፡፡ አብዛኛዎቹ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በብሔራዊ ባንክ የተደነገገውን መመርያ ለማሟላት ተጨማሪ ካፒታል ማሰባሰብ ግድ የሚላቸው ይሆናል፡፡
በመመርያው ዙሪያ ያነጋገርናቸው የአልፋ ሰርተፊኬት ኮንሰልታንት ሰርቪስ ዋና ሥራ አስኪያጅና የኢንሹራንስ ባለሙያው አቶ ኢብሳ መሐመድ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ መመርያው ለኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው አስደንጋጭ ነው፡፡ አብዛኛዎቹ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ከ20 ዓመታት በላይ በኢንዱስትሪው ቆይተው የደረሱበት ካፒታል መጠን እጅግ አነስተኛ ነው፡፡ በመሆኑም በአንድ ጊዜ ከ75 ሚሊዮን ብር ወደ 500 ሚሊዮን ብር ካፒታላቸውን አድርሱ መባሉ እጅግ የሚፈትናቸው ይሆናል፡፡ ‹‹መመርያው የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪውን አቅም ያገናዘበ ነው፤›› ብለው እንደሚያምኑ የገለጹት አቶ ኢብሳ፣ በተለይ በምሥረታ ላይ ያሉ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የተጠቀሰውን ካፒታል አሟልተው ወደ ሥራ ይገባሉ ተብሎ የማይታሰብ ነው፡፡
በሥራ ላይ ያሉትም ባንኮች እ.ኤ.አ. እስከ 2027 ድረስ ባለው አምስት ዓመታት ውስጥ ካፒታላቸውን 500 ሚሊዮን ብር ለማድረስ የሚችሉበት ዕድል ባለመኖሩ፣ ያላቸው አማራጭ ውህደት ብቻ እንደሚሆንም ጠቁመዋል፡፡
ከረዥም ጊዜ አንፃር ካየነው ግን ኩባንያዎች ተዋህደው ጠንከር ያለ የኢንሹራስ ኩባንያ ለማቋቋም ዕድል ሊሰጥ ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ የውጭ የኢንሹንስ ኩባንያዎች ከገቡ ጠንካራ ተወዳዳሪ የሚሆን አገር በቀል የኢንሹራንስ ኩባንያ እንዲኖር የሚያስችል ይሆናል፡፡ አሁን ባላቸው አቅም ግን አብዛኛዎቹ የኢንሹራስ ኩባንያዎች 500 ሚሊዮን ብር ካፒታል ለመሙላት የተሰጣቸው የአምስት ዓመታት ጊዜ በቂ ነው ብለው እንደማያምኑ አቶ ኢብሳ ገልጸዋል፡፡
አንዳንድ የዘርፉ ባለሙያዎች ግን ‹‹ይህ ሲጠበቅ የነበረ ነው፤›› ብለዋል፡፡ እንዲያውም የዘገየ ስለመሆኑም ያምናሉ፡፡ የካፒታል ማደግ ተገቢ ነው ብለው ከሚያምኑት መካከል አንዱ የሆኑት ታዋቂው የፋይናንስ ባለሙያ አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ አንዱ ናቸው፡፡ ካፒታሉን ለማሟላት የተሰጠው የአምስት ዓመታት ጊዜ ረዥም ነው ብለውም ይሞግታሉ፡፡
‹‹የኢንሹንስ ኩባንያዎች ካፒታል ገና ከመነሻው ጀምሮ እጅግ በጣም ዝቅተኛ ነበር፤›› የሚሉት አቶ ኢየሱስ ወርቅ፣ ትንሽ ካፒታል ያላቸው የኢንሹንስ ኩባንያዎች የሚያገኙትን ዓረቦን ለጠለፋ መድን ሰጪ ኩባንያዎች በመሆኑ፣ ካፒታላቸው ማደግ አለበት፡፡ አሁንም ቢሆን ግን 500 ሚሊዮን ብር መሆኑ ይሻላል ነው እንጂ፣ በቂ ነው ብለው እንደማያምኑም ገልጸዋል፡፡ 500 ሚሊዮን ብር ካፒታል ለመሙላት የተሰጠው የአምስት ዓመታት ጊዜ ረዥም ነው ብለው የሚያምኑት አቶ ኢየሱስ ወርቅ፣ ‹‹የካፒታሉ ማሟያ ጊዜ ሦስት ዓመታት ቢሆን የተሻለ ነበር፤›› ይላሉ፡፡
ምክንያቱም 500 ሚሊዮን ብር ከአምስት ዓመታት በኋላ አነስተኛ ነው፡፡ በኅብረት ኢንሹራንስ በኩል ይህ መመርያ ከመውጣቱ በፊት ካፒታሉን በአንድ ቢሊዮን ብር በመጨመር ወደ 1.5 ቢሊዮን ብር ለማድረስ ማሰባቸውንም ገልጸዋል፡፡ እኛ ይህ ሕግ ይወጣል ብለን ሳይሆን መደረግ ስላለበት የምናደርገው ነው፡፡ ስለዚህ የአሁኑ የካፒታል ማሳደግ ውሳኔ ግን ተገቢ መሆኑን ያምናሉ፡፡
የአቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉን ሐሳብ የሚያጠናክሩት ሌላው የኢንሹራንስ ባለሙያ አቶ ፍቅሩ ፀጋዬ በበኩላቸው፣ አሁን የተወሰደው ውሳኔ አግባብ መሆኑን አመልክተው፣ የተጠየቀውን ካፒታል ለማሟላት አንድ ዓመት በቂ ነው ብለው ያምናሉ፡፡
ለዚህ አባባላቸው ጥሩ ምሳሌ ይሆናል ያሉት የብር የመግዛት አቅም በየጊዜው እየቀነሰ በመምጣቱ ነው፡፡ እሳቸው የሚሠሩበት የኢትዮጵያ ጠለፋ መድን አክሲዮን ማኅበር ከአምስት ዓመታት በፊት ሲቋቋም አንድ ቢሊዮን ብር ይዞ ነው፡፡ ይህ አንድ ቢሊዮን ብር በወቅቱ በዶላር ሲቀየር 50 ሚሊዮን ዶላር ነበር፡፡ አሁን የኩባንያው ካፒታል 2.5 ቢሊዮን ደርሷል፡፡ አሁን ባለው የምንዛሪ ዋጋ ሲቀየር 48 ሚሊዮን ዶላር ሆኗል፡፡ ስለዚህ የብር የመግዛት አቅም ማነስም ኩባንያዎች ካፒታላቸውን እንዲጨምሩ ማድረግ ግድ ይላል፡፡ በሌላ በኩልም ካፒታል መጨመሩ ጠንካራ ኩባንያዎች ስለሚፈጥር ውሳኔው ቢዘገይም ተገቢ ነው ብለው ያምናሉ፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ወቅት 17 የግልና አንድ የመንግሥት የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በገበያ ውስጥ ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ወደ ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው ለመግባት ሦስት የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በእንቅስቃሴ ላይ እንደነበሩም ለማወቅ ተችሏል፡፡ አማራ ባንክም ወደ ኢንሹራንስ ኩባንያ ለመግባት ፍላጎት ካላቸውና እንቅስቃሴ እያደረጉ ካሉ መካከል አንዱ ነው፡፡
የኢትዮጵያ የግል ኢንሹራንስ ኩባንያዎች በገበያ ውስጥ እንዲገቡ የሚፈቅደው ሕግ ሲወጣ፣ ኢንሹራንስ ኩባንያ ለማቋቋም የሚጠየቀው ካፒታል ሦስት ሚሊዮን ብር ብቻ ነበር፡፡ ከዚያ ካፒታሉ እየተሻሻለ 75 ሚሊዮን ብር ደርሶ ነበር፡፡