Saturday, March 2, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በመንግሥት ተቋማት የተከማቹ አገልግሎት የማይሰጡ ንብረቶች የሚሸጡበት ዋጋ ተከለሰ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ያገለገለ ማሽነሪና ተሽከርካሪ በኪሎ በ51 ብር ለብረት ፋብሪካዎች እንዲሸጥ ተወስኗል

በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የተከማቹ ቁርጥራጭ ብረታ ብረቶች፣ የማያገለግሉ ተሽከርካሪዎችና ማሽነሪዎች ለብረት አቅላጭ ኢንዱስትሪዎች የሚሸጡበት ዋጋ ተከለሰ፡፡ 

ሪፖርተር የተመለከተውና ለፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች የተላለፈው ሰነድ እንደሚያሳየው፣ የገንዘብ ሚኒስቴር በሰኔ ወር 2014 ዓ.ም. ሁሉም የፌዴራል መንግሥት ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች ያለ አገልግሎት የተከማቹ ቁርጥራጭ ብረታ ብረቶች፣ የማያገለግሉ ተሽከርካሪዎችና ማሽነሪዎች ለብረታ ብረት አቅላጭ ኢንዱስትሪዎች የሚተላለፍበት ዋጋ መወሰኑን ያስታውሳል፡፡ ነገር ግን የንብረቶቹን የወቅቱ ዋጋ የገበያ ጥናት በማካሄድ፣ ቀደም ሲል ለብረት አቅላጭ ኢንዱስትሪዎች በኪሎ የሚተላለፉበትን ዋጋ በአዲስ መተካቱ ታውቋል፡፡

ያገለገሉ የተሽከርካሪ መለዋወጫዎች በኪሎ 21.15 ብር የሚቀርቡበት ዋጋ በ51.25 ብር የተተካ ሲሆን፣ በውዳቂ ብረታ ብረትነት የሚወገዱ ተሽከርካሪዎችንና ማሽነሪዎች ደግሞ ይሸጡበት ከነበረው 31.18 ብር የ39.1 በመቶ የዋጋ ማስተካከያ ተደርጎባቸው በ51.25 ብር በኪሎ ይሸጣሉ ተብሏል፡፡

ከዚህ ቀደም ቁርጥራጭ የሆኑ ስቲል ብረታ ብረቶችን በኪሎ 29.30 ብር እንዲያስረክቡ የተገለጸላቸው መሥሪያ ቤቶች በአዲሱ ማስተካከያ በ64 ብር ሲያስረክቡ፣ በኪሎ 21.25 ብር ሲሸጡ የቆዩትን የካስት አይረን ብረቶች ደግሞ በ51.75 እንዲሸጡ መወሰናቸው ተመልክቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በኪሎ 108.65 ብር ይሸጡ ተብሎ ዋጋ የወጣላቸው ቁርጥራጭ አልሙኒየሞች፣ ከመስከረም 12 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በ120 ብር እንዲሸጡ ተወስኗል፡፡

ከአገልግሎት ውጪ የሆኑ ተሽከርካሪዎች ለብረት አምራች ኢንዱስትሪዎች በሽያጭ እንዲተላለፉ መንግሥት መወሰኑ፣ የብረት አምራች ፋብሪካዎችን የግብዓት እጥረት በከፍተኛ መጠን የሚያቃልል መሆኑን ለፋብሪካዎቹ ምደባውን የሚያደርገው የማዕድን ሚኒስቴር አስታውቋል።

ቁርጥራጭ ብረቶቹና የማያገለግሉ ተሽከርካሪዎቹ ለፋብሪካዎቹ ያለ ጨረታ በመነሻ ዋጋ በቀጥታ እንዲወስዱ የገንዘብ ሚኒስቴር በወሰነው መሠረት፣ የፋብሪካዎችን የማምረት አቅም ባገናዘበ መልኩ ድልድል የሚያካሄድ መሆኑን የማዕድን ሚኒስቴር ገልጿል፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴር በበኩሉ አገሪቱ ባጋጠማት የውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት አንዳንድ የብረት አቅላጭ ኢንዱስትሪዎች ጥሬ ዕቃ ከውጭ ገዝተው ማስገባት ስለልቻሉ፣ በአገር ውስጥ የሚገኘውን ውዳቂ ብረታ ብረት ለእነሱ ማቅረብ የኢንዱስትሪዎቹን የግብዓት ችግር በተወሰነ ደረጃ የሚያቃልል ከመሆኑም በላይ፣ አገሪቱ ያላትን ውስን የውጭ ምንዛሪ ሀብት በቁጠባ መጠቀም የሚያስችል መሆኑን አስታውቋል፡፡

የቁርጥራጭ ብረታ ብረቶችን አወጋገድና አፈጻጸም በተመለከተ ተገቢውን ክትትል በማድረግ የአፈጻጸም ሪፖርት እንዲያደርግ የተገለጸለት የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሰጠኝ ገላን ለሪፖርተር እንዳስረዱት፣ ከዚህ ቀደም ባለሥልጣኑ የቁርጥራጭ ብረቶች መሸጫ ዋጋ አጥንቶ ረቂቁን በገንዘብ ሚኒስቴር ስር የማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴን ለሚያስተባብር ኮሚቴ ቀርቦ ነበር፡፡ ከዚህ ቀደም ለብረታ ብረት ፋብሪካዎች በፌዴራል መሥሪያ ቤቶች የተከማቹና አገልግሎት የማይሰጡ ብረታ ብረቶች በጨረታ ይሸጡ እንደነበር የገለጹት የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ፣ ከዚህ በኋላ በማዕድን ሚኒስቴር በሚደረግ ድልድል መሠረት የሚሰጣቸው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ መሠረታዊ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪዎች ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ሙሉጌታ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በመንግሥት በኩል ቁርጥራጭ ብረትን በቀጥታ ግዥ እንዲሸጥ የተወሰደው ዕርምጃ የሚበረታታ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም የብረት ኢንዱስትሪዎቹ በተናጠል የመንግሥት ተቋማት በሚያወጧቸው ጨረታዎች በመሳተፍ በተበጣጠሰ መንገድ የሚያገኙትን ግብዓት፣ ተቀናጅቶ መቅረቡ ጥቅሙ በርካታ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የማዕድን ሚኒስቴር በመንግሥት ተቋማት የተከማቹና አገልግሎት የማይሰጡ ብረታ ብረቶች ለሁሉም የብረት አምራች ፋብሪካዎች ለብረት አምራች ኢንዱስትሪዎች በሽያጭ በሚተላለፉበት ድልድል ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር፣ ከብረት አምራች ፋብሪካዎች ጋር የውይይት መድረክ አዘጋጅቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች