- ሃሎ… ስብሰባ ላይ ሆኜ ነው ያላነሳሁት …በሰላም ነው?
- ሰላም ነው። ልንገርህ ብዬ ነው…
- ምንድነው ምትነግረኝ?
- ዛሬ አልመጣም፣ እንዳትጠብቀኝ ልነግርህ ነው።
- ምን ማለት ነው? ወደ አገር ቤት ልትመለስ ነው?
- እንደዚያ እንኳ አይደለም።
- እና ምን ሆነህ ነው?
- አድራለሁ።
- ምን?
- ማለቴ ሊያሳድሩኝ ነው።
- ማነው የሚያሳድርህ? የት ነው ያለኸው?
- ፖሊስ ጣቢያ ነው።
- ምን አድርገህ ነው። የትኛው ፖሊስ ጣቢያ ነው?
- መታወቂያ እንደጠፋብኝ ላስመስክር ብዬ ጠዋት የሄድኩበት ጣቢያ ነው ያለሁት።
- ምን አድርገህ ነው ከሰው ተጣላህ?
- ኧረ በጭራሽ!
- ምን ተፈጠረ ታዲያ?
- አልያዝክም ተብዬ ነው።
- ምን?
- የታደሰ መታወቂያ።
- ምን?
- አዎ። እንደዚያ ነው።
- የመጣሁት ላስመሰክር ነው ብለህ አታስረዳቸውም እንዴ?
- አልኩኝ፣ ሞከርኩ።
- እና…
- አልሆነማ!
- ምን ምላሽ ሰጡህ?
- እስኪመረመር ድረስ ነው ያሉኝ።
- እስኪመረመር ምን አሉ?
- እዚሁ እደር!
[ክቡር ሚኒስትሩ ከባለቤታቸው ጋር ስለአገር ጉዳይ እያወጉ ነው]
- እየሆነ ያለው ነገር ግራ አጋብቶኛል።
- ምኑ ነው ግራ ያጋባሽ?
- የሰሜኑ ጦርነት ሁኔታ ሊገባኝ አልቻለም።
- ለምን?
- አንደኛው ምክንያት መንግሥት ምንም ዓይነት መረጃ እየሰጠ ባለመሆኑ ነው።
- ሌላኛው ምክንያትስ?
- ሌላኛው ደግሞ ከሰሜኑ ኃይል እየወጣ ያለው ተከታታይ መረጃ ነው ግራ ያጋባኝ።
- ከሰሜኑ ኃይል የወጣው መረጃ እንዴት ግራ አጋባሽ?
- በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ የመንግሥት ወታደሮችን ደመሰስኩ ይሉና አፍታም ሳይቆዩ የሚቃረን መረጃ ያወጣሉ።
- ምን ብለው?
- በሁሉም አቅጣጫ ጥቃት ተከፈተብን። ተከበብን ይላሉ።
- እሱማ አንዱ የሚከተሉት የውጊያ ስልት ነው።
- እንዴት?
- ደመሰስን ሲሉ ደምሰስን ማለታቸው አይደለም።
- እ?
- አለን ማለታቸው ነው።
- ለማን ነው አለን የሚሉት?
- ለምዕራባውያኑ ደጋፊዎቻቸው።
- ደመሰስን ካሉ በኋላ ተጠቃን የሚሉትስ ለምንድነው?
- ተጠቃን ሲሉ ተጠቃን ማለታቸው አይደለም።
- ምን ማለታቸው ነው ታዲያ?
- ምነው ዝም አላችሁ ማለታቸው ነው።
- ማንን?
- ምዕራባዊያኑን።
- ምዕራባዊያኑ ምን እንዲያደርጉላቸው?
- በሰሜኑ ውጊያ የጦር ወንጀል ሳይፈጸም አይቀርም የሚል መግለጫ እንዲያወጡ ወይም …
- ወይም ምን?
- በሰብዓዊነት ላይ ጥቃት መፈጸሙን የሚያመላክቱ መረጃዎች እየደረሱን ብለው መግለጫ እንዲያወጡ ወይም…
- ሌላ ምን?
- የሰብዓዊ ዕርዳታ ካልገባ መቶ ሺሕ ሕዝብ በረሃብ ሊያልቅ ይችላል የሚል ሥጋት ፈጥሮብናል የሚል መግለጫ እንዲያወጡላቸው።
- ይህ ለእነሱ ምን ይጠቅማቸዋል?
- ለእነሱማ የጦርነቱ አካል ነው።
- እንዴት?
- ማዕቀብ እንዲጣል። ይህ ካልሆነላቸው ደግሞ ሌላ የሚታደጋቸው ነገር እንዲመጣ ሊሆን ይችላል።
- ምን ሊመጣ ይችላል?
- ዓለም አቀፍ ሰላም አስከባሪ።
- አሜሪካ ግን በተደጋጋሚ ስለኢትዮጵያ የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት መከበር መግለጫ እያወጣች ነው።
- እሱም የጦርነቱ አካል ነው።
- እንዴት?
- የዚህ ጦርነት መጨረሻ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነትን ይፈትናል ማለቷ ነው። በተጨማሪ ደግሞ…
- በተጨማሪ ምን?
- ይህ አደጋ ከመጣ እኔ የለሁበትም፣ ከደሙ ንፁህ ነኝ ማለቷ ነው።
- ታዲያ መንግሥት ይህንን እያወቀ ለምን ዝም አለ?
- ከባለፈው ስህተቱ ትምህርት ወስዶ።
- ምን ተማረ?
- ዝምታ።
- ዝምታ መፍትሔ ይሆናል እንዴ?
- ዝምታ ብቻውን አይደለም።
- ሌላ ምን አለ?
- ምታ በዝምታ!