በኢትዮጵያ የአገርና የዜጎችን ደኅንነት ለመጠበቅ ተብለው የሚወጡ አንዳንድ ሕጎች፣ ዕገዳዎች ወይም ክልከላዎች መልሰው ዜጎችን ለጉዳት ሲዳርጉ መታየታቸው የተለመደ ነው፡፡ በጊዜያዊነት ለበዓላት ወይም ለተለያዩ ሥነ ሥርዓቶች ተብለው ከሚወጡ የትራፊክ እንቅስቃሴ ክልከላዎች ጀምሮ፣ በበርካታ ጉዳዮች መልሰው በዜጎች ላይ ችግር የሚፈጥሩ ክልከላዎችን ማየት የተለመደ ነው፡፡
በቅርብ ጊዜ ከሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ወደ አዲስ አበባ በመግባት ጥቃት ሊያደርሱ የሚችሉ አጥፊዎችን ለማስቆም በሚል፣ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኞች መንገደኞች ላይ ክልከላ መደረጉ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር፡፡ መንግሥት ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ የሚሄዱ ዜጎችን ‹‹ከመንገድ መለሰ›› በሚል ከባድ ፖለቲካዊ ትችት ሲሰነዘርበት ነበር፡፡ ‹‹መንግሥት የዜጎችን በነፃነት የመንቀሳቀስና ከቦታ ወደ ቦታ የመዘዋወር ነፃነት ያክብር›› በሚል በዚህ ጉዳይ ጠንካራ ትችት ሲቀርብበትም ተስተውሏል፡፡ የኦሮሚያ ክልልም ቢሆን ከዚህ ትችት አላመለጠም፡፡
የፌዴራል መንግሥት፣ ‹‹በአዲስ አበባ ከተማ ሊቃጣ የሚችል ጥቃትን ለማስቀረት ያደረግኩት ነው፤›› ቢልም፣ ‹‹ጥፋተኞችን ነጥሎ ማደን ይቻላል፤›› የሚሉ ግን በወቅቱ ተቃውመውታል፡፡ ለሕክምና፣ ለወሊድ፣ ለለቅሶና ለሌሎች አንገብጋቢ ጉዳዮች ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ የሚሄዱ መንገደኞችን በአጠቃላይ ከመንገድ መመለስ፣ ሕጋዊም ሆነ ሞራላዊ አይደለም ያሉ ወገኖች ድርጊቱን ኮንነውታል፡፡
በመስቀል አደባባይ ለሚከበር ወይም በስታዲዮምና በአራት ኪሎ አካባቢ ለሚካሄድ ሥነ ሥርዓት ከእነዚህ ቦታዎች በእጅጉ በሚርቁ አካባቢዎች፣ የትራፊክ እንቅስቃሴ ገደብ ሲደረግ የታየባቸው አጋጣሚዎች ብዙ ናቸው፡፡ እነዚህ ዕርምጃዎች ደግሞ አንዳንዴ ለቀናት የሚጣሉ ገደቦች መሆናቸው፣ በርካታ የከተማ ነዋሪዎችን የዕለት ተዕለት ኑሮ የሚያስተጓጉሉበት አጋጣሚ በርካታ ሲሆን ይታያል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን በመጡ የመጀመርያ ወቅት ይህንን ዓይነት ዕርምጃ እንደሚቃወሙ ተናግረው ነበር፡፡ ለእሳቸውም ሆነ ለሌሎች ባለሥልጣናት ሲባል መንገድ መዘጋቱ ተገቢ አለመሆኑን በፓርላማው የተናገሩት ዓብይ (ዶ/ር)፣ ‹‹በአንድ አስፋልት መስመር (ሌን) ብቻ ከትራፊክ ነፃ ተደርጎ ሌላ እንቅስቃሴ ሳይስተጓጎል መጠቀም ይቻላል ብዬ ነበር፡፡ ነገር ግን የእኛ አገር የትራፊክ አጠቃቀም ለደኅንነት ጥበቃ አስቸጋሪ ስለሆነ ነው የተውነው፤›› በማለት ተናግረው ነበር፡፡
ጥቅል ዕርምጃዎችና ክልከላዎች መገለጫቸው የትራፊክ እንቅስቃሴ ዕገዳ ብቻ አይደለም፡፡ በተለያዩ ዘርፎች የተለያዩ ዓይነት ጅምላ ቅጣቶች መተላለፋቸው አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡ ይህ ደግሞ አገሪቱን ለከፍተኛ ማኅበራዊና ኢኮኖሚዊ ኪሳራ እንደሚዳርጋት ይነገራል፡፡
ለአብነት ያህል ከነሐሴ 2014 ዓ.ም. ጀምሮ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ የመሬትና መሬት ነክ አገልግሎቶችን ላልተወሰኑ ጊዜያት በማገዱ የተነሳ፣ ከ664 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ሳይሰበሰብ መቅረቱን በሪፖርተር መዘገቡ ይታወሳል፡፡
ልክ እንደዚህ ሁሉ የባንኮች የብድር አገልግሎት ተቋርጦ እንዲቆይ መደረጉም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን የገታ እንደነበር በርካታ ቅሬታዎች ሲሰማ ቆይቷል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የመታወቂያ ዕድሳት አገልግሎትም ሆነ አዲስ መታወቂያ የመስጠቱ ሒደት እንዲቋረጥ መደረጉ፣ ብዙዎችን ለጉዳት እየዳረገ መሆኑ ቅሬታ ይቀርብበታል፡፡ መንግሥት ሕግ የማስከበር ሥልጣኑን ተጠቅሞ ዜጎችን፣ ብሎም የአገር ደኅንነትን የማስከበር ኃላፊነት ያለበት በመሆኑ፣ አንዳንድ ዕቀባዎችን ማውጣቱ የተለመደ ነው፡፡ መንግሥት በመደበኛው ሕግ የማስበር ሥርዓት አገር መምራት የማይቻልበት ሁኔታ ሲፈጠርና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ፣ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እስከማውጣት ያሉ ዕርምጃዎችን ሊወስድ እንደሚችል ነው በሕገ መንግሥቱ ጭምር የተደነገገው፡፡
ይሁን እንጂ አሳማኝ ባልሆኑ መንገዶችና ቅሬታን በሚፈጥር ሁኔታ የዜጎችን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ መገደብ ትችት ሲቀርብበት ይታያል፡፡ በተደጋጋሚ ጊዜ ዕገዳው የሚደረግ ከሆነና የዜጎችን መሠረታዊ አገልግሎቶች የማግኘት መብት የሚጋፋ ከሆነ ዕቀባው የሕጋዊነት ጥያቄ ማስነሳቱም አይቀርም፡፡
ጠበቃና የሕግ አማካሪ አቶ በላቸው ግርማ ይህንን ዓይነቱን በዜጎች ላይ ገደብ የመጣል አሠራር፣ ‹‹ከበፊቶቹ አምባገነናዊ መንግሥታት የአሁኑ አስተዳደር የወረሰው ልማድ›› ሲሉ ይጠሩታል፡፡ የመንግሥት ኃላፊነትና ግዴታን ገደብ ከመጣል ጋር የማቆራኘት ልማድ በኢትዮጵያ መኖሩን የሚናገሩት የሕግ ባለሙያው፣ ‹‹ይህ ሁኔታ እንደ ሕግ ጥሰት አለመታየቱ ደግሞ እጅግ አሳሳቢ ነው፤›› ይላሉ፡፡
‹‹ከመሬት ተነስቶ ከዛሬ ጀምሮ ቤት መሸጥ ክልክል ነው ይሉሃል፡፡ ምን ያህል ታስቦበት ነው የሚለው አይመለስም፡፡ እንዲህ ዓይነት ገደብ ሲጣል ምን ዓይነት መብቶችን ይገድባል? ሌላ አማራጭስ የለም ወይ? አንድ ገደብ ሲጣል መሥፈርቶች አሉት? አስፈላጊ ነው ወይ? ተመጣጣኝስ ነው ወይ? እንዲጠበቅ የሚፈለገው የሕዝብና የአገር ጥቅምስ ምንድነው? የሚሉ ዝርዝር ጉዳዮች ተተንተነው ነው ዕገዳው የሚወጣው፤›› በማለት ያብራሩት አቶ በላቸው፣ በሌሎች ብዙ አገሮች ያለው የገደብ ሕጎች አወጣጥና አተገባበር ይህን መንገድ የተከተለ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
የገደብ ሕግ አወጣጥና አተገባበር የራሱ መሥፈርት ያለው የሕግ ጉዳይ ነው ቢባልም፣ በኢትዮጵያ ያለው አሠራር እነዚህን መሥፈርቶች መከተሉ ያጠራጥራል፡፡ በሕግ ትምህርቶችና ሰነዶች ላይ የወንጀል ቅጣት ዓላማዎች ሰዎችን ማስጠንቀቅ (Deterrence)፣ መካስ (Reparation)፣ መልሶ ማቋቋም (Rehabilitation) መሆኑ ተመልክቷል፡፡ የሕግና ሕግ ማስፈን ዓላማ አጥፊዎችን መቅጣት (Retribution)፣ ሌላ ጥፋት እንዳይፈጸም ማስቆም (Incapacitation)፣ እንዲሁም ፍትሕ ማረጋገጥ (Justice) የያዘ ሊሆን ይገባል ተብሎ ቢጠቀስም፣ ገደብም ሆነ ቅጣት በሕግ የሚጣለው ከእነዚህ የተለየ ዓላማ ኖሮት አለመሆኑን በዘርፉ ምሁራን ተደጋግሞ ይነገራል፡፡
ብዙ የሕግ ምሁራን እንደሚስማሙበት ከሆነ የወጡ ሕጎችና ገደቦች የተፈለገውን በጎ ዓላማ ከማሳካት ይልቅ ዜጎችን ችግር ላይ የሚጥሉ ከሆነ፣ ሕጉ ዜጎችን ጠልፎ መጣያ ሆነ እንደሚባል ይናገራሉ፡፡ አጥፊዎችን ለይቶ መቅጣትና ማስተማር የመንግሥት ግዴታ ሆኖ ሳለ፣ እንዲሁም ችግር የፈጠሩ የሕግ ክፍተቶችን መድፈን እየተቻለ መንግሥት በጥቅሉ ዕገዳዎችን ማውጣት ላይ የሚያተኩር ከሆነ፣ ሕግ የሕዝብ መገልገያ ሳይሆን የጥቂቶች መጠቀሚያ እንደሚሆን ነው ባለሙያዎቹ የሚያሳስቡት፡፡
ያለ ንግድ ፈቃድ መነገድ በአዋጅ ወንጀል ተብሎ መውጣቱን እንደ አንድ ምሳሌ የሚያወሱት ጠበቃና የሕግ አማሪ አቶ በላቸው፣ ‹‹በቀላሉ በአስተዳደራዊ ቅጣቶች ሊታለፍ የሚችለው ይህ ጥፋት በሕጉ ከ50 ሺሕ ብር የገንዘብ መቀጮ እስከ ሰባት ዓመታት በእስራት የሚያስቀጣ ተባለ፤›› ሲሉ ያብራራሉ፡፡
መንገድ ዳር በጋሪ እየገፋ ሙዝ የሚነግድ ሰው አራት ዓመትና 50 ሺሕ ብር እንደተፈረደበት እንደሚያውቁም ይናገራሉ፡፡ ይህን ዓይነት አከራካሪ የሕግ ዳኝነትና አሻሚ የሆኑ የሕግ ገደቦች ችግር ከሕገ መንግሥቱ እንደሚመነጭም ያስረዳሉ፡፡
‹‹በሕጉ መሠረት ገደብ ሊጣል ይችላል የሚሉ አንቀጾች በሕገ መንግሥቱ ላይ አሉ፡፡ ለምሳሌ የሐሳብ ነፃነት (Freedom of Expression) ላይ በእነዚህ ምክንያቶች ገደብ ሊጣል ይችላል የሚል አለ፡፡ ነገር ግን ገደቡ ማሟላት የሚገባቸውን ዝርዝር መሥፈርቶች አንቀጹ አይናገርም፤›› በማለት የሕግ ባለሙያው ያብራራሉ፡፡ ይህን ሁኔታ ደግሞ ከደቡብ አፍሪካ ሕገ መንግሥት ጋር የሚያነፃፅሩት አቶ በላቸው፣ ‹‹በእነሱ ሕገ መንግሥት ጠቅላላ ገደቦች የሚሏቸውን በማሥፈር ገደቦች ሊያሟሉ የሚገባውን መሥፈርቶች በዝርዝር አስቀምጠዋል፤›› ሲሉ የሌሎች ተሞክሮዎችን አውስተዋል፡፡
‹‹የመታወቂያ ዕድሳትም ሆነ ማውጣት ክልከላ ወይም የቤት ኪራይ ዋጋ መጨመር አይቻልም›› የሚለው ዕገዳ ዓላማቸው የሕዝብን ጥቅም ማስጠበቅ ሊሆን ይችላል፡፡ የውልና ማስረጃ አገልግሎት መገደብም ሆነ ሌሎች ክልከላዎች ከአገር ደኅንነትና ጥቅም አንፃር የሚታዩ ጉዳዮች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህ የሕግ ገደቦችና ክልከላዎች በተቃራኒ ሕዝብን ካስመረሩና የአገሪቱን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ካስተጓጎሉ ሊደረግ የሚገባው ነገር ምንድነው የሚለው ብዙ እያጠያየቀ ነው፡፡
የሕግ ባለሙያው አቶ በላቸው ግን፣ ‹‹የሚጠይቅ የለም፤›› ይላሉ፡፡ ‹‹እንዲህ ዓይነት ጉዳት ደርሶብኛል፣ ገደቡ ይነሳልኝ ብሎ መንግሥትን የሚጠይቅ አይታይም፡፡ በመንግሥትም በኩል ቢሆን ለዜጎች ከማሰብና በገደቦች ሌላ ጉዳት ይደርሳል ብሎ ከመጨነቅ ይልቅ፣ ሥልጣን ስላለ ብቻ የሚጣሉ ገደቦች ይበዛሉ፤›› በማለት ነው የሚናገሩት፡፡
በአንዳንድ የሕግ ገደቦችና ክልከላዎች የተነሳ በርካታ ተያያዥ የሥራ ዘርፎች እንቅስቃሴ ሲስተጓጎል ይታያል፡፡ በመሬት ወይም ውልና ማስረጃ አገልግሎት መታገድ የተነሳ በየአገልግሎት መስጫ ቢሮዎች በር ላይ ካሉ የኮፒና የጽሕፈት አገልግሎት መስጫዎች ጀምሮ ብዙ የመንግሥት ገቢ ይታጣል፡፡ በባንክ ብድር ክልከላ ደግሞ ብዙ የንግድና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ይስተጓጎላል፡፡
ከጥቂት ወራት በፊት እያንዳንዱ የባንክ ደንበኛ በየባንኩ እየተገኘ መታወቂያውን ወይም የግል ማኅደሩን ካላስመዘገበ የሚል ማስታወቂያ መውጣቱ ይታወሳል፡፡ በተቀመጠው ጊዜ ገደብ በየባንኩ ተገኝቶ የሚጠየቀውን የግል ማኅደር ማስመዝገብ ያልቻለ የባንክ ተገልጋይ ጊዜ ገደቡ አልፏል ተብሎ አካውንት የመታገድ ዕጣ ገጠመው፡፡ ይህ ክስተት ለጥቂት ቀናት ቢሆንም፣ በባንኮች አካባቢ የፈጠረው ግርግርና የአገልግሎት ወረፋ ቀላል አልነበረም፡፡ የጊዜ ገደቡን ማብቂያ ጊዜ ያላወቁ ደንበኞችን ግርግርና መጨናነቅ ሳይፈጠር ማስተናገድ እየተቻለ፣ ወደ አካውንት ዕገዳ መግባቱ በጊዜው ከበርካታ የባንክ ደንበኞች ቅሬታ ማስነሳቱ አይዘነጋም፡፡
‹‹መንግሥት ያለበት የአቅም ውስንነት ዜጋን ዋጋ በማስከፈል መሸፈን የለበትም፤›› የሚሉት ጠበቃና የሕግ አማካሪ አቶ በላቸው፣ አገልግሎትን በማዘመንና ዲጂታል በማድረግ አሊያም በሌላ አማራጭ ክፍተቶችን መሙላት አስፈላጊ መሆኑን ያሰምሩበታል፡፡
መንግሥት የሚያወጣቸው የሕግ ዕገዳዎችንና ክልከላዎች ዜጎችን ከማስመረር ባለፈ፣ በአተገባበር ሒደት ዕገዳዎቹን የሚቃረኑ ችግሮች እንደሚፈጥሩም ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ ‹‹መታወቂያ ማደስም ሆነ አዲስ ማውጣት አይቻልም›› የሚል ዕግድ ወጥቶ ሳለ፣ ባንኮችና ሌሎች አገልግሎት መስጫዎች የታደሰ መታወቂያ ለአገልግሎት መጠየቃቸው ዜጎችን አስመራሪ ብቻ ሳይሆን፣ መንግሥትን ትዝብት ላይ ይጥለዋል የሚሉ በርካቶች ናቸው፡፡
ከሰሞኑ በአንዳንድ ፍተሻዎችና አገልግሎት መስጫዎች የታደሰ መታወቂያ እየተጠየቁ መሆኑን በመጥቀስ፣ የፖሊስ አቋምን የተጠየቁት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ምክትል ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ፣ ተቋማቸው የመታወቂያ ጉዳይ እንደማይመለከተው ነው የተናገሩት፡፡ ለደኅንነት ሲባል ፍተሻ እንደሚካሄድ፣ መታወቂያ ያልያዘ ሰው ሲገኝም ወደ ጣቢያ በመውሰድ መታወቂያ ያልያዘበት ምክንያትን ፖሊስ እንደሚያጣራ የተናገሩት ምክትል ኮማንደር ማርቆስ፣ ከዚህ ውጪ መታወቂያ የመስጠትም ሆነ የማደስ ጉዳይ የከተማ አስተዳደሩ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡