Wednesday, November 29, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለውጭ ባንኮች የፀደቀው ፖሊሲ ብዥታ እንደፈጠረበት የመድን ሰጪዎች ማኅበር ገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የውጭ ባንኮች እንዲገቡ በቅርቡ ያፀደቀው የፖሊሲ ማዕቀፍ መግለጫ፣ የኢንሹራንስ ዘርፉን ያላካተተ ሆኖ በመቅረቡ ግርታ እንደፈጠረበትና ይህንንም ለማጥራት ማብራሪያ እንደሚጠይቅ የኢትዮጵያ መድን ሰጪዎች ማኅበር አስታወቀ፡፡ 

የማኅበሩ ቦርድ በዚሁ ጉዳይ ላይ በመወያየት ባሳለፈው ውሳኔ፣ መንግሥት የፋይናንስ ዘርፉን ለውጭ ኩባንያዎች እንደሚከፍት ካስታወቁበት ጊዜ ጀምሮ ውሳኔው ኢንሹራስ ኩባንያዎችንም የሚመለከት እንደሚሆን ታሳቢ የተደረገ ቢሆንም፣ የተወሰነው ውሳኔ ግን ባንክን ብቻ የሚመለከት ሆኖ መገኘቱ ብዥታ እንደፈጠረበት አመልክቷል፡፡  

የኢትዮጵያ የኢንሹራስ ኢንዱስትሪ ገበያ ልክ እንደ ባንክ ለዓለም አቀፍ ውድድር ክፍት መሆን አለመሆኑን በማወቅ ላይ የመንግሥትን አቋም ለማወቅ ከብሔራዊ ባንክ ገዥ ጋር ለመነጋገር የማኅበሩ ቦርድ ስምምነት ላይ ደርሷል፡፡  

በዚሁ የቦርዱ ውሳኔ መሠረት ጥያቄያቸውንም ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በማቅረብ የማኅበሩ አመራሮች ከብሔራዊ ባንክ ለመነጋገር ይፈልጋሉ፡፡ የኢንሹራስ ኢንዱስትሪው ልክ እንደ ባንክ እንደሚከፈት ምንም ጥርጥር ያልበራቸው መሆኑን የሚገልጹት የኢንዱስትሪው ባለሙያዎች፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ ባንክ ብቻ ሆኖ ሲመጣ አስደንግጦናልም በማለት ገልጸዋል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ ያነጋገርናቸው የኢትዮጵያ መድን ሰጪዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ያሬድ ሞላም፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ እስከተሰማ ድረስ ባንክን ብቻ ይሆናል ብለው እንዳላሰቡ ገልጸዋል፡፡ ይህ ለምን እንደሆነና ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው ሳይጠቀስ መታለፉ ለእሳቸውም ግርታ እንደፈጠረባቸው ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ ማኅበራቸውም በጉዳዩ ላይ እንደሚወያይ ያስገደደው ውሳኔው የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው ይመልከት፣ አይመልከት ምንም የሚገልጸው ነገር ባለመኖሩ ነው ብለዋል፡፡ ለባንክ ሲፈቀድ ኢንሹራንስም የሚመለከት ይሆናል የሚል ዕሳቤ ቢኖርም፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ ግን ምንም የሚገልጸው ነገር ያለመኖሩ የግድ ማብራሪያ መጠየቅ አስፈልጓል ተብሏል፡፡   

ማኅበሩ የውጭ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ ይፈቀድላቸዋል የሚል ዕምነት ይዞ ቢቆይም፣ አሁን ላይ ጥርጣሬ ውስጥ ገብቷል። ማኅበሩ ከጥቂት ወራት በፊት ይህንኑ የተመለከተ ጥያቄ ለመንግሥት አቅርቦ አዎንታዊ መልስ በማግኘቱ የውጭ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ ገበያ ይገባሉ የሚል እምነት ይዞ እንደነበረ አቶ ያሬድ ይገልጻሉ፡፡ 

ከጥቂት ወራት በፊት የፋይናንስ ተቋማትን በተመለከተ በተደረገ ውይይት ላይ ማኅበሩ ጠይቋቸው ከነበሩ ሦስት ዋና ዋና ጥያቄዎች መካከል አንዱ የኢንሹራንሶች ገበያው ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት መደረግ አለበት የሚል ነበር። በወቅቱ በመድረኩ ተሳታፊ የነበሩት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ በሰጡት ምላሽ፣ ጥያቄው ተቀባይነት እንደሚኖረው ገልጸው ነበር፡፡   

ይሁን እንጂ በቅርቡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የውጭ የፋይናንስ ተቋማት እንዲገቡ የሚፈቅድ የፖሊሲ ማዕቀፍ ማፅደቁን አስመልክቶ ያወጣው መግለጫ ኢንሹራንስ ዘርፍን የሚጠቅስ ባለመሆኑ፣ ማኅበሩ የማብራሪያ ጥያቄ እንዲያነሳ አስድዶታል። እንደ ማኅበሩ ገለጻ የውጭ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ ገበያ እንዲገቡ መፍቀድ የኢትዮጵያን የኢንሹራስ ኢንዱስትሪ ጠንካራና ተወደዳሪ ያደርገዋል።

በመሆኑም ማኅበሩ፣ የመንግሥት የፖሊሲ አውጪዎች የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪውን ሳይዘነጉ በፖሊሲ ማዕቀፉ ውስጥ ማካተታቸውን ማረጋገጥ እንደሚፈልግ አስታውቋል። ሁለተኛው የማኅበሩ ጥያቄ በፋይናንስ ዘርፉ የተለያዩ ሪፎርሞች እየተደረጉ ቢሆንም፣ የሪፎርሙ አጀንዳ እስካሁን ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው ላይ ያልደረሰ በመሆኑ ይህም ታሳቢ እንዲደረግ የሚጠይቅ ነው፡፡  

ሪፎርሙ ባንኮች ላይ በተወሰነ ደረጃ የተሠራበት ቢሆንም፣ የኢንሹራንስ ዘርፉ አካባቢ ግን እስካሁን ባለመድረሱ ሪፎርሙ የኢንሸራንስ ዘርፉንም እንዲመለከት ማኅበሩ ፍላጎት እንዳለው አስታውቋል፡፡  

የማኅበሩ አባላት አቋም ይዘው እንዲተገበር የሚጠይቁት ሌላው ነጥብ፣ የኢንሹራንስ ንግድ ሥራ የራሱ ፍልስፍናና የአሠራር ባህሪያት ያሉት በመሆኑ፣ ይህንን ያገናዘበ ዘርፉን የሚያስተዳድርና የሚቆጣጠር ራሱን የቻለ የኢንሹራንስ ኮሚሽን እንዲቋቋም የሚጠይቅ ነው። ማኅበሩ እንዲቋቋም የሚጠይቀው ኮሚሽን ከብሔራዊ ባንክ ወጪ ሆኖ የኢንሹራንስ ዘርፉን ለብቻው የመቆጣጠርና የመምራት ሥልጣን እንዲኖረው ጭምር ነው። በዚህ ጉዳይ ላይም ቀደም ብሎ በተደረገው የባለድርሻ አካላት የውይይት መድረክ ላይ የተሳተፉት የገንዘብ ሚኒስትሩ አዎንታዊ ምላሽ ሰጥተው ነበር።

‹‹ኢንሹራንስ ለኢኮኖሚው ያለውን ጠቀሜታ በሚገባ እንረዳለን፡፡ ያቀረባችሁትን ጥያቄ በቅርቡ ተመልክተን ተገቢውን ምላሽ እንሰጣለን፤›› በማለት ምላሽ መስጠታቸውን አቶ ያሬድ አስታውሰዋል፡፡ ስለዚህ ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው እንዲህ ያሉ ጥያቄዎች ያሉትና የውጭ ኢንሹራንስን ኩባንያዎችም ወደ ገበያው እንዲገቡ የሚፈልግ በመሆኑ፣ መንግሥት ባፀደቀው ፖሊሲ ውስጥ ኢንሹራንሱን ዘርፉ እንዲያጠቃልል መደረግ አለበት ብለዋል።

የውጭ ባንኮች እንዲገቡ የተሰጠው ውሳኔ ኢንሹራስን ያለማካተቱ እንደ ማኅበር አስደንግጦናል የሚሉት አቶ ያሬድ፣ አሁንም ቢሆን መንግሥት ይህንን ጉዳይ ችላ ይለዋል ብለው አያምኑም፡፡ ከባንክ ይልቅ የውጭ ኢንሹራስ ኩባንያዎችን ለማስገባት የተመቻቸ ነገር ያለ በመሆኑ፣ ፖሊሲ አውጪዎች ይህንንም ታሳቢ ማድረግ እንደሚገባ ያነጋገርናቸው የዘርፉ ባለሙያዎች ጠቅሰዋል፡፡ አቶ ያሬድም፣ ገበያው ዝም ብሎ ይከፈት የሚል ዕሳቤ እንደሌላቸው ገልጸው፣ አከፋፈቱ ደረጃ በደረጃ መሆን እንዳለበት ጠቁመዋል። ምክንያቱም ከትግበራው በፊት ምክክር ያስፈልጋል፡፡ የሌሎች አገሮችን ተሞክሮና የኢንዱስትሪውን ባህሪ በማየት ፖሊው ሊቀረፅ እንደሚገባ የተናገሩት አቶ ያሬድ፣ ሒደቱ አገሪቱንም ሆነ የአገር ውስጥ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው ሳይጎዳ ምን ዓይነት መንገድ መከተል እንደሚገባ ማጤንና መመካከር እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል። በዚህ ረገድ ያለውን የሌሎች አገሮች ጥሩ ተሞክሮዎችን ይዞ ለመሄድ ተነጋግሮ መሥራት የሚያስፈልግ ቢሆንም፣ የፀደቀው ፖሊሲ የኢንሹራንስ ዘርፉን ሳይጠቅስ ማለፉ ግን ብዥታ ስለፈጠረ መጀመርያ ይህንን ነገር ማስተካከል እንደሚገባ ሳያመለክቱ አላለፉም፡፡ 

የማኅበሩ ቦርድ በዚሁ ጉዳይ አጀንዳ ይዞ ተነጋግሮበት አቋም የያዘውና በጉዳዩ ላይ ከብሔራዊ ባንክ ጋር ለመነጋገር የሚሻውም መንግሥት የውጭ ባንኮች ይግቡ ሲል ኢንሹንሱን እንዳይረሳ ለመጠየቅ ነው ብለዋል፡፡ ኢንሹራንስ ዘርፍ በሥራ ባህሪው ዓለም አቀፍ ይዘት እንዳለው የሚናገሩት ያሉት አቶ ያሬድ፣ በሥራ ላይ ያለው የኢንሹራንስ ዘርፍን የሚገዛው የሕግና የፖሊሲ ማዕቀፍ ዓለም አቀፍ ይዘት ያለውና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሆኑ የኢንሹራስ ኩባንያዎችን በጠለፋ ዋስትና ሥርዓት ከኢትዮጵያ የኢንሸራንስ ኩባንያዎች ጋር እንደሚያስተሳስራቸው አስረድተዋል። በመሆኑም የውጭ ፋይናንስ ተቋማትን ወደ ኢትዮጵያ የማስገባት ሒደት የኢንሹራንስ ዘርፉን በማስቀደም መጀመሩ የተሻለ ይሆናል የሚል እምነት አላቸው፡፡  

ለምሳሌ የህዳሴ ግድብ 95 በመቶ የሚሆነው ዋስትና በውጭ የጠለፋ መድን ሰጪዎች የተሸፈነ ሲሆን፣ የአገር ውስጥ የኢንሹራስ ኩባንያዎች ድርሻ አምስት በመቶ ብቻ እንደሆነ ጠቅሰዋል። ከዚህ ሌላ እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድና ትልልቅ ሜጋ ፕሮጀክቶች የመድን ሽፋን ሁሉ አብዛኛው የሚሸፈነው በውጭ የጠለፋ መድን ሰጪ ኩንያዎች ነው፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ የሚሸጠው የቤትም ሆነ የተሽከርካሪ የኢንሹራስ ሽፋን በተፈጥሮው ለንደንም ሆነ ኒዮርክ ከሚሸጠው አንድ ዓይነት በመሆኑ የኢንሹራንስ ዓለም አቀፋዊነት በግልጽ የሚታወቅ ነው ብለዋል።

የኢንሹራንስ ሽፋን የመስጠት ሥራን አንድ ተቋም የሚሸከመው ሳይሆን፣ ድንበር ዘለልና የውጭ ኩባንያዎች የሚያሳትፍ በመሆኑ የውጭ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች በቅድሚያ እንዲገቡ መፍቀድ ተገቢ ሆኖ ሳለ በዝምታ መታለፉ ቅር ማሰኘቱ አይቀርም ይላሉ፡፡ የውጭ ኩባንያዎች መግባት በአገር ውስጥ የኢንሹራንስ ዘርፍ ላይ ውድድር እንደሚያመጣ ግልጽ ቢሆንም፣ እንደ አገር ሲታሰብ የውጭ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ኢትዮጵያ መግባት ትልቅ ጥቅም እንዳለው ገልጸዋል።

የውጭ ኢንሹራንሶች መግባት መሠረታዊ ነው ተብሎ የሚታመነው የዕውቀትንና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ማስገኘቱም ባሻገር የአገር ውስጥ ኩባንያዎች ማቅረብ ያልቻሉትን ለምሳሌ የሕይወት ኢንሹራንስ ሥራ ላይ ቢገቡ ኢንዱስትሪው ላይ ትልቅ ለውጥ የሚያመጡ ስለመሆኑ ስለሚታመን እንደሆነም አስረድተዋል፡፡ 

እስካሁን ኢትዮጵያ የሕይወት ኢንሹራንስ እጅግ አነስተኛ ሽፋን ያለው ሲሆን፣ በአገር ውስጥ ኩባንያዎች ማሳደግ ስላልተቻለ፣ ቢያንስ በዚህ ዘርፍ ገብተው እንዲሠሩ መፍቀድ ኢንዱስትሪው ላይ የሚፈጥረው መነቃቃት ቀላል አይሆንም፡፡  

እነዚህ የውጭ ኩባንያዎች በሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍ ውስጥ ገብተው ከሠሩ ብዙዎችን ከመድረስ ባሻገር ለቁጠባ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ መንግሥት ይህን ሁሉ ታሳቢ ማድረግ አለበት፡፡ የአንድ አገር ኢኮኖሚ ዕድገት ይበልጥ ትርጉም የሚሰጠው የሕይወት ኢንሹራንስ አብሮ ሲያድግ ነውና ለውጭ ኢንሹራስ ኩባንያዎች የኢትዮጵያ በር ቢፈከት የሚጠቀመው አገር ስለመሆኑ አቶ ያሬድ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከዓለም ተገልላ ልትቀር አትችልምና ለባንክ ተብሎ እየተደረገ ያለው ዝግጅት ኢንሹራንሱንም አካትቶ ከወዲሁ ሥራው ቢጀመር መልካም መሆኑን በመጥቀስም የውጭ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች መግባት ግድ የሚልበት ሌላ ምክንያት አለ ይላሉ፡፡

ይህም የውጭ ባንኮች ሲገቡ ለሚያበድሩት ገንዘብ ማስያዣ ባይጠይቁ ኢንቨስት ለማድረግ ቦታና ንብረት ዋስትና መጠየቃቸው አይቀርም፡፡ ስለዚህ ለአገልግሎታቸው የሚመጥን ኢንሹራንስ የሚፈልጉ በመሆኑ፣ ይህንን ሊያሟላልን የሚችል ኩባንያ እንሻለን ሊሉ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ መንግሥት ሁለቱን ዘርፎች ነጣጥሎ ከመፍቀድ ለሁሉም በሩን ክፍት ማድረግ በብዘ መልኩ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል፡፡ 

በኢትዮጵያ ውስጥ 18 የኢንሹራስ ኩባንያዎች እየተንቀሳቀሱ ሲሆን፣ በ2014 የሒሳብ ዓመት በጥቅል ያሰባሰቡት የዓረቦን መጠን 16.74 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች