Wednesday, November 29, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የሚወዳደሩ ዕጩዎች ታወቁ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ሐሙስ መስከረም 12 ቀን 2014 ዓ.ም. በሚካሄደው ምርጫ የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ሆነው ለመመረጥ ሁለት ዕጩዎች መቅረባቸውና ከምክር ቤቱ ነባር የቦርድ አባላት ውስጥ ደግሞ አብዛኞቹ በድጋሚ ለቦርድ አባልነት ለመመረጥ ዕጩ ሆነው እንደሚወዳደሩ ታወቀ፡፡

የዕጩዎቹን ማንነት ዘግይቶ ያስታወቀው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫ አመቻች ኮሚቴ፣ በዘንድሮ ምርጫ ለፕሬዚዳንትነት ታጭተዋል ብሎ ካቀረባቸው ውስጥ አሁን በኃላፊነት ላይ የሚገኙን ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ አንዱ ናቸው፡፡ ከወ/ሮ መሰንበት ጋር ተፎካካሪ ይሆናሉ ተበለው የታጩት ደግሞ አቶ ኤደኦ አብዲ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

አቶ ኤዳኦ በስማቸው የተቋቋመው ኤዲኦ ኢንተርናሽናል ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሥራ አስኪያጅ መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡ ከምክር ቤቱ ምርጫ አመቻች ኮሚቴ ያገኘነው ተጨማሪ መረጃ እንደሚያመለክተው ደግሞ፣ ለፕሬዚዳንትነትና የቦርድ አባል ለመሆን 33 ጥቆማዎች ተቀብሏል፡፡ ከዚህ ውስጥ 24ቱ መሥፈርቱን ማሟላት አለማሟላታቸውን ተጣርቶ የመጨረሻዎቹ 12 ዕጩዎች ተለይተዋል፡፡ ከ24ቱ ዕጩዎች ውስጥ አራቱ ለፕሬዚዳንትነት ተጠቁመው የነበሩ ሲሆን፣ 20ዎቹ ደግሞ ለቦርድ አባልነት የተጠቆሙ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ለፕሬዚዳንትነት ከተጠቆሙት ውስጥ ሁለቱ የተቀመጠውን መሥፈርት ሊያሟሉ ባለመቻላቸው ውድቅ መደረጋቸውን መረጃ ያመለክታል፡፡ ከቀረቡት ዕጩዎች መረዳት እንደሚቻለውም፣ የንግድ ዘርፉን በወከል የንግድ ምክር ቤቱ የቦርድ አባል ሆነው በአሁኑ ወቅት በማገልገል ላይ የሚገኙት ሰባት አባላት፣ ሐሙስ በሚካሄደው ምርጫ በቦርድ አባልነት በድጋሚ ለመመረጥ ዕጩ ሆነው ቀርበዋል፡፡ በነባሩ ቦርድ ውስጥ የነበሩና አሁን ዳግም ይወዳደራሉ የተባሉት ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ፣ አቶ ክብረት አበበ፣ አቶ ነፃነት ለሜሳ፣ አቶ በቀለ ፀጋዬና አቶ ተስፋዬ ነጋሽ ናቸው፡፡ 

ከእነዚህን ዕጩዎች ጨምሮ ለቦርድ አባልነት የመጨረሻዎቹ ዕጩዎች ሆነው ከቀረቡት 12 ተወዳዳሪዎች ውስጥ የፋይናንስ ተቋማት ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች ይገኙበታል፡፡ እነዚህም የዳሸን ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አስፋው ዓለሙ፣ የኅብረት ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መላኩ ከበደ፣ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ነፃነት ለሜሳ ናቸው፡፡ አቶ አስፋውና አቶ መላኩ ለመጀመርያ ጊዜ ዕጩ ሆነው የቀረቡ ሲሆን፣ አቶ ነፃነት ደግሞ አሁን በሥራ ላይ የሚገኘው ቦርድ አባል ናቸው፡፡ 

ንግድ ምክር ቤቱን በቦርድ አባልነት ለማገልገል ይወዳደራሉ ተብለው የታጩት ቀሪዎቹ ዕጩዎች ደግሞ አቶ ብርሃኑ ደገፋ (የዕድገት ልብስ ስፌት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሥራ አስኪያጅ)፣ ዶ/ር ጃራ ሰማ (የፊንፊኔ መካከለኛ ክሊኒክ ሥራ አስኪያጅ)፣ አቶ አበራ አበጋዝ (የኤዋይ ኖብል ኢንስፔክሸን ኤንድ ሰርቪስ ሥራ አስኪያጅ)፣ ወ/ሮ ሳራ ሰለሞን (የኢትዮ ሳሜል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሥራ አስኪያጅ)፣ አቶ ዓለማየሁ ንጋቱ ኢትአብን የሕንፃ ሥራ ተቋራጭ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሥራ አስያኪጅ)፣ ወ/ሮ ትኅትና ለገሠ (የዋሪት ሙሉ ጥላ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ)፣ ዶ/ር አህመድ አብዱራህማን (የጎልደን ብሪጅ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሥራ አስኪያጅ) እና አቶ እያሱ ኩመራ (የኢኩማ የማማከርና የሥልጠና አገልግሎት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሥራ አስኪያጅ) ናቸው፡፡ 

ንግድ ምክር ቤቱ በአጠቃላይ የሚኖሩት የቦርድ አባላት ብዛት 11 ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ ምክትል ፕሬዚዳንትና ሦስት የቦርድ አባላት ከአዲስ አበባ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የሚወኩሉ ናቸው፡፡ 

እነዚህ በቀጥታ የሚሰየሙትን የቦርድ አባላት የንግድ ዘርፍ ምክር ቤቱ ትናንት ባካሄደው ምርጫ በመምረጥ ሐሙስ ለሚካሄደው የምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባዔው ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ከንግድ ምክር ቤቱ ሕገ ደንብ ውጪ ሁለት ጠቅላላ ጉባዔዎችን ሳያካሂድ የቀረው የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት፣ ሐሙስ በሚያደርገው ጉባዔ ያለፉት ሦስት ዓመታት ዓመታዊ ሪፖርትና የውጭ ኦዲተሮችን ሪፖርት ይቀርብለታል፡፡ 

በዚህ የንግድ ምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባዔው ላይ አባላት ማብራሪያ የሚያገኙበት በርካታ ጥያቄዎች የሚቀርቡ እንደሚሆን ያነጋገርናቸው አባላት የገለጹ ሲሆን፣ የንግድ ምክር ቤቱ ሕንፃ ግንባታ መታጎል የዋና ጸሐፊ ስንብትና ሌሎች ጉዳዮች ይነሳሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ 

 

   

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች