ከመገናኛ ወደ ሲኤምሲ ለመጓዝ ልንሳፈር ታክሲ በመጠበቅ ላይ ነን። በዚህ ጊዜ የማንጠብቀው ነገር ቢኖር አለመጠበቅን ራሱን እየሆነ የመጣ ይመስላል። ዕጦት ጀርባችንን እያጎበጠው ብንቸገር ይኼው የተረጂነት መንፈስ ጎዳናውን አጥለቀለቀው። ለማኙ ምነው ታክሲ በሆነ ብለን እስክንመኝ ድረስ ተቸግሮ ያስቸግረናል። አንዱ የመረረው ድምፁን ጮክ አድርጎ፣ ‹‹አልበዛም? በዛ፣ በጣም በዛ፣ ከመጠን በላይ በዛ…›› እያለ ይነጫነጫል። ሌላው ወይ ያለውን አውጥቶ ሰጥቶ አይፀድቅበት ወይ ሰውየውን አልደገፈው፣ ዝም ብሎ በመሀል ቤት ሐሳቡ እየዋለለ ለፍርድ ተቸግሮ ቆሟል። ለፍርድ ያልተቸገርንበት ነገር ምን አለ ዘንድሮ? እንዲህ ነው ማለት እየከበደን እጆቻችንን በአፋችን ጭነን መጨረሻውን የማንናፍቀው ከደግ እስከ ክፉ ምን አለ? ጎዳናው የውጥረት ነፍስ ዘርቷል። የማያረጁ ዕቅዶች በትውልድ ዕድሜና ዘመን መሀል እንደ ፈጣን ባቡር እየተሳቡ ይሸጋገራሉ። የነበረው ተመልሶ ሊመጣ የተሰማው ተመልሶ እንደ አዲስ ሊተረክ አዲስ ትውልድ ሕይወትን እንደ አዲስ ሊኖር ይማስናል። በትርጉም አልባነት ቁና ከንቱነት ባነፈሰን ቁጥር ራሳችንን እየጠላን የሆነውን እየታዘብን የሰማነውን እየናቅን በሕይወት መንገድ ላይ ዝንት ዓለም እንጓዛለን። እስካለን ድረስ!
‹‹ሲኤምሲ ናችሁ? ጉርድ ሾላ አልጭንም…›› እያለ ወያላው ያስገባል። ሰው አንዴ እየተግተለተለ ሲገባ ወያላው ስልብ ብሎ ጠፋ። የገባነው ገብተን ቦታ ቦታችንን ይዘን ከሞላን በኋላ ወያላውም ሾፌሩም አልመጣ ብለው መንጫጫት ተጀመረ። ‹‹ኧረ ጥሩት እባካችሁ? እንዲህ መጫወቻቸው እንሁን?›› ይላል አንድ ተሳፋሪ። ይኼኔ ተራ አስከባሪው ብቅ ብሎ፣ ‹‹ምነው አትሄዱም እንዴ?›› አለን። ነገሩ ገብቶት አውቆ ሊያደርቀን እንደሚጠይቀን ያስታውቅበታል። ‹‹የሌባ ዓይነ ደረቅ ይሉሃል እንዲህ ያለው ነው…›› ትለዋለች አንዲት ሴት በኋላ እንደሰማነው አብሯት የሚጓዘውን ባለቤቷን። ‹‹እያየኸን? እኛ እናሽከርክረው እንግዲያ?›› ብሎ አንድ ወጣት ተሳፋሪ ሲጮህበት ምንም ሳይመስለው እየገለፈጠ፣ ‹‹ኑ በሉ እዚያኛው ታክሲ ላይ። የእዚህ ታክሲ ሾፌር የለም…›› ብሎ አስወረደን። ‹‹እግዚኦ፣ ጭራሽ ብለን ብለን ዕቃ እንሁን?›› ያላሉ አብረውን ተሳፍረው ቆይተው ወደ እዚያኛው ታክሲ አብረውን የሚሻገሩ አዛውንት። ‹‹ምን እናድርግ እንደ ሰውም እንደ ዜጋም የሚቆጥረን ካጣን እኮ ቆይተናል…›› ይላቸዋል አንድ ዘናጭ ጎልማሳ። ‹‹ዜጋ? ዜግነት ከፓስፖርትና ከመታወቂያ አገልግሎት ውጪ የት የሚታወቀውን ነው የምታነሳው? ኧረ ተወኝ እባክህ፣ ይልቅ እነዚህ ቦዘኔዎች እንደ እነሱ ድድ ስናሰጣ የምንውል መስሏቸው አይደለም እንዲህ የሚጫወቱብን? ስማ አንተ…›› ብለው ወዲያው ተራ አስከባሪው ላይ መዓት ይወርዱበት ጀመር። ተናግረው ሳይጨርሱ ሌላ ተራ አስከባሪ እየደነፋ መጣ። ‹‹ማን ጫን አለህ? ለምን ተራህን አትጠይቅም መጀመርያ? ውረዱ ይኼ ተረኛ አይደለም…›› ሲል አዛውንቱ ደንግጠው ያዩት ጀመር። ‹‹ለምንድነው እንዲህ የምታንገላቱን?›› ቢለው አንዱ ወጣት ቱግ ብሎ፣ ‹‹እሰይ፣ መቼ ደልቶህ የሚያውቀውን ነው ተንገላታሁ የምትለው? ‘ሲሉ ሰምታ’ አሉ። እናንተ መብታችሁን ማስከበር የሚታያችሁ ታክሲ ተራ እንጂ በየቢሮው የሚያሰግዳችሁን አይደለም…›› እያለ ብዙ አወራብን። ‹‹በቃ እሺ ቀጣዩ የቱ ነው?›› ሲለው አንደኛው አቋርጦ ጠቆመንና ሄደን ተሳፋርን። ከጀመረ የማይለቀው ብሶተኛ እንዴት በዛ እባካችሁ!
ይህን ሁሉ ስንባባል መንገዳችን ከተጀመረ ቆይቷል። ወያላው ሒሳብ እያለ መዞሩን ከመጀመሩ ፊታቸው በውል እንዳይታዩ ፊታቸውን በነጠላቸው ጥምጥም አድርገው የሸፈኑ በዕድሜ የገፉ አንዲት እናት፣ ‹‹የቤት ኪራይ የምከፍለው አጥቼ ይኼው ተቸገርኩ። ጧሪ የለኝ ዘመድ የለኝ ዕርዱኝ እባካችሁ?›› ብለው ገና ከማለታቸው ወያላው፣ ‹‹እንዴ በየት በኩል አድርገው ገብተው ነው? ቅድም እዚሁ ታክሲ ውስጥ 300 ብር በመዋጮ ተሰብስቦ አልተቀበሉም?›› ሲላቸው እጅግ ተቆጥቶ፣ ‹‹ውይ ደገምኩህ? የእኔ ነገር…›› ብለው ዝም አሉ። አባባላቸው እያሳዘነን አሳቀን። ሾፌሩ ታክሲዋን እያቆመ፣ ‹‹አውርዳቸው…›› ብሎ አጭር ትዕዛዝ አስተላለፈ። ወርደው ሊሄዱ ሲሉ አንዱ አሥር ብር ሸጎጠላቸው። ድካም ከእግር እስከ ራሳቸው ወርሷቸዋል። በዚህ መሀል ለካ የቆምነው የፍሳሽ ማስተላለፊያ ፉካ ላይ ሆኖ ታክሲዋ በአንዴ በአጓጉል ሽታ ታወደች። ‹‹ፓ፣ ኧረ ሾፌር በፈጠረህ ፈቀቅ አድርገን? ኡ…ህ…ህ…›› ማለት ጀመረ ተሳፋሪው። አንድ ወጣት ተሳፋሪ፣ ‹‹አይ አዲስ አበባ እንዲህ ከላይ እስከ ታች ትበላሽ?›› ሲል አጠገቡ የተቀመጠች የዕድሜ አቻው ቀበል አድርጋ፣ ‹‹ወንድሜ እኛም እኮ ይኼን እያልን ነው ባለ በሌለ አቅማችን የፈረንሣይ ሽቶ የምንሸምተው…›› አለችው። ‹‹አሃ… ለእኛ ብለሽ?›› ሲላት እያሾፈ፣ ‹‹ታዲያስ፣ ቢያንስ እኛን ታጠኑ ብለን ነው…›› ብላው ትስቅ ጀመር። ሁለቱ ወዲያው አፍ ለአፍ ገጥመው በጨዋታቸው ሲዘልቁ አንዱ ከኋላ፣ ‹‹ገና አዲስ ዓመት ከመግባቱ?›› ብሎ እሪ ይላል። ምን እንደተቀደመ አይታወቅም፡፡ ዓይኑን የተጠራጠረ አጠገቡ የተቀመጠ ጎልማሳ፣ ‹‹ዶላር በአንዴ ዘጠናን ተሻግሮ ነው አይደል?›› ሲለው፣ ‹‹መሻገር ብቻ መሰለህ ሌላውንም አስወነጨፈው እንጂ፡፡ በ800 ሺሕ ብር ልገዛው የነበረ መኪና 1.2 ሚሊዮን ገባ እያሉ እኮ ነው…›› ብሎ ሲተክዝ ሁላችንም ወገባችንን የተመታን ይመስል ደነገጥን፡፡ መደንገጥ ይነሰን!
ታክሲዋ እየተፈተለከች ነው። ወያላው በመስኮቱ በኩል የምስኪኗን አዛውንት ቦታ በሌላ ተሳፋሪ ለመሙላት ጎዳናውን በጥሪ ያስበረግገዋል። ጉርድ ሾላን አልፈናል። አሁንም ሰው አላገኘም። ሾፌሩ በተመስጦ ታክሲዋን ወደ መዳረሻዋ ያምዘገዝጋታል። ወያላው ድንገት ለሾፌሩ፣ ‹‹አይ? በቃ እኛ እናትት ረግመውናል፣ ይኼን ቢያጆ ስንጨርስ አቁመን መቃም ነው ያለን ምርጫ…›› ብሎ ሥራ እንዲያቆሙ ምክንያት ይደረድር ጀመር። ሾፌሩ፣ ‹‹እውነትህን ሳይሆን አይቀርም። እኔምለው እርግማን ይሆን እንዴ ኑሮ እንዲህ እንዲወደድ፣ ዝርፊያው ቅጥ እንዲያጣ ያደረገው?›› ብሎ እየተሳለቀ ጠየቀው። ይኼኔ ጋቢና ከሾፌሩ አጠገቤ የተቀመጠ ተሳፋሪ፣ ‹‹የኑሮንና የዝርፊያውን ነገር ፈጣሪ አንድ ካላለልን የዘንድሮን ነገር እንጃ…›› ብሎ ከማለቱ ከእሱ አጠገብ ያለው ተሳፋሪ፣ ‹‹አንተ ደግሞ ቁርስና እራትን በኑሮ ውድነት ምክንያት እንደ ካንጋሮ እየዘለልናቸው እየዋልን የደላው የመኪና ዋጋ ጣሪያ ነካ ብሎ ያላዝንብናል…›› ብሎ ብሶቱን ዘረገፈው። ጭውውቱ ወዲያው ወደ እኛ ተዛመተ። ‹‹አሁንማ ያለው ምርጫ ማንንም መጠበቅ አይደለም፡፡ የሚያዋጣው እጅጌን ጠቅልሎ ማንኛውንም ሥራ ሠርቶ ሰው ለመሆን መነሳት ነበር…›› ሲል ጎልማሳው፣ ‹‹‘ነበር ባይሰበር’ አለ የድሮና የዘንድሮ ሰው…›› ብለው የሚናገሩት አዛውንቱ ናቸው። ‹‹አባት? የድሮ ሰውስ እሺ የዘንድሮ ሰው እንዴት ብሎ ነው ‘ነበር’ን ያወቀው?›› ስትላቸው ወይዘሮዋ፣ ‹‹ያየውን አይቶ የሰማውን ሰምቶ…›› ብለው በአጭሩ መለሱላት። ይገርማል!
ወደ መዳረሻችን ተጠግተናል። ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ቅልጥ ያለ የመኖሪያ ሠፈር እየሆነ የመጣውን ሲኤምሲን እያዩ ወጣቶቹ ተሳፋሪዎች፣ ‹አሁንማ ነዳጅ እየተገኘ ነው ይኼን የመሰለ ቤት ነው የምንሠራው…› እየተባባሉ የቤቱን ዓይነት ይጠቋቆማሉ። ‘ላም አለኝ በሰማይ ነዳጇንም አላይ’ የሚለውን ጥቅስ ወያላው እየጠቆመ ያስቀናል። ‹‹ኧረ ጎበዝ ሰሞኑን ይኼ የኑሮ ውድነት አላስቀምጠን ብሏል። ሁለት ጓደኞቼ ይኼው ከዛሬ ጀምረው የቅጥር ሥራ አቁመው የራሳቸውን ለመጀመር ተማምለዋል…›› ብሎ አንዱ የሰማውን ይተነፍሳል። ‹‹ለመሆኑ አንቺም የግል ሥራ አስበሻል?›› ይላታል አንዱ ሌላዋን። ‹‹ይሻላል ብለህ ነው? ለነገሩ አሁን ሳስበው ተቀጥሮ ከመሥራት ትንሽም ቢሆን የራስን ሥራ መክፈት ነው የሚያዋጣው…›› ስትለው አዛውንቱ፣ ‹‹እንዲህ ነው እንጂ ጀግንነት፣ በሆነ ባልሆነው ስትባክኑ ባትኖሩ ኖሮ ኑሮ ይጫወትባችሁ ነበር?›› አሉ። ታክሲዋ ዳር እየያዘች ነው። ወያላውና ሾፌሩ ሥራ አቁመው ለመቀመጥ ቸኩለዋል፣ ከጫት ጋር ስለተቃጠሩ። ወያላው ‹‹መጨረሻ›› ብሎ ራሱ መጀመሪያ ወርዶ ሲሮጥ አዛውንቱ ሁላችንንም ቃኘት አድርገው፣ ‹‹ለሥራ መነሳት ደግ ነው፣ ግን መጀመሪያ ዕቅድ ይቅደም፣ ያልታቀደ ሥራ ፋይዳ ስለሌለው ሌላው ቀስ ብሎ ይደርሳል፡፡ ሌላው ደግሞ ገንዘባችን እንደ አይስክሬም መቅለጥ ስለጀመረ ቶሎ ቶሎ ሥሩበት…›› እያሉ ቀድመውን ወረዱ። እኛም ዘንድሮ ቀለጥን ማለት ነው እያልን በየፊናችን ተጣደፍን። መልካም ጉዞ!