Friday, June 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህልምልክቶች በሥዕል ገበታ

ምልክቶች በሥዕል ገበታ

ቀን:

ታሪክ፣ የፖለቲካ ርዕዮት፣ የማኅበረሰብ ባህልና ቅርስ በምልክቶች ይቀመጣሉ፡፡ የአሁን ትውልድ አኗኗርና አስተሳሰብ ያለፉት ዘመናት አባቶች ነፀብራቆች የሚገለጹት በምልክቶች ነው፡፡

ያለፉትም፣ አሁንም ያሉት፣ ለወደፊት የሚሠሩ ክንውኖች ወይም ተግባሮች ለቀጣዩ ዘመን ለምልክትነት ይቀመጣሉ፡፡ ምልክት በብዙ ነገሮች ይገለጻሉ፡፡ ለምሳሌ ሕመሞች የሚለዩት በሚያሳዩት ምልክት ነው፡፡ ያለፉት ነገሥታትና መሪዎች ዓርማቸው፣ ርዕዮታቸውን የሚገለጹበትም እንዲሁ በምልክት ነው፡፡ በኪነ ሕንፃ፣ በሐውልት፣ በሥነ ጽሑፍ፣ በሥዕልና በሌሎች ዘርፎች ይገለጻሉ፡፡ ሰዎች ወይም ማኅበረሰቦች የራሳቸውን አሻራ በምልክት የሚያስቀምጡት በተለያዩ ነገሮች ነው፡፡

ሠዓሊ ዳዊት ገረሱም የራሱን ምልክት ለማኖር በፈንድቃ ባህል ማዕከል የሥዕል ዓውደ ርዕይ አዘጋጅቷል፡፡

- Advertisement -

ሠዓሊው 19 የሥዕል ሥራዎችን ያቀረበ ሲሆን የዓውደ ርዕዩ ስያሜ ‹‹ምልክት›› ይሰኛል፡፡ የቀረቡት ሥዕሎችም በአመዛኙ ያለፉት ዘመናት የፖለቲካዊና ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎችን የሚያስቃኙ ናቸው፡፡

‹‹በዚህ የሥዕል ዓውደ ርዕይ ላካትታቸው ያሰብኳቸው ሥዕሎች ባለፉት አምስት ዓመታት የሠራኋቸው የጥበብ ሥራ ውጤቶቼን የሚያጠቃልሉ ናቸው። በባህልና በቴክኖሎጂ የበለፀጉ የጥበብ ሥራዎችን ለመሥራት መተግበሪያዎችን በመጠቀምና ሥዕሎችን በመቀየር መረጃን በአዲስ መንገድ ለማስተላለፍ የመጠቀም ትልቅ ፍላጎት አለኝ፤›› ያለው ሠዓሊው፣ ሒደቱ የሚከናወነው ስማርት ስክሪን በመጠቀም ምሥሎችን ቆራርጦ በመሥራት እንደሆነ፣ የአሁኑ ሥራውም የኢትዮጵያን ታሪክ የተንተራሱ ማንነትና ዘመናዊነትን፣ ሃይማኖትንም  የሚያስቃኝ መሆኑን ገልጿል።

የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለምን፣ ሃይማኖትና ከተማን የሚገልጹ ምልክቶችን በቀለሞች በማጣመርና በዲጂታል መተግበሪያዎች በመጠቀም መሥራቱን አመልክቷል፡፡

ለዓውደ ርዕይ የቀረቡት ሥራዎች የሥዕልና የፎቶግራፍ ጥምር ሥራዎች ሲሆኑ፣ ለዓውደ ርዕይ ለማብቃት ሦስት ዓመታት ወስደዋል፡፡

ለሥዕሉ የተጠቀመባቸው ግብዓቶች የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ቁሶችን መሆናቸውን ሠዓሊ ዳዊት ተናግሯል፡፡

ከቀረቡት ሥዕሎች አንዱ ወጣት ሲሆን ይህም የሰው ልጅ ምልክት መሆኑን፣ በጥልቀት ሲመረመር ደግሞ አፍሪካዊ መሆኑ ተናግሯል፡፡ ሌላው ሥራ የነፃነት ሐውልት የተሰኘው ሲሆን ነፃነት ዋጋ የተከፈለበት መሆኑን በምልክትነት መቀመጡን ያስረዳል፡፡

ምልክት ማለት ቀጥተኛ ግንኙነት ወይም ስሜት ሳይኖረው ለመጠቀም የሚያስችል መሆኑን ያስረዳው ሠዓሊው፣ ፍላጎትና ጥላቻ ሳይኖርም ለምልክትነት የተቀመጡ ነገሮች ሰዎች ሲያዩት አዕምሮአቸው የሚነግራቸው ነገሮች መኖራቸውንም ያብራራል፡፡ በዓውደ ርዕዩ የቀረቡ ሥዕሎች ተመልካቾች ለማሳመን ወይም እንዲቀበሉት ሳይሆን፣ ራሳቸውም የምልክቱ ምልክት መሆናቸውን እንዲረዱ ነው ሲሉ አስረድቷል፡፡

ከጊዜ፣ ከሁኔታ፣ ከሥርዓት ጋር የተያያዙ ምልክቶች በሥዕሉ መካተቱን የገጸው ሠዓሊው አንዱ ማሳያ ‹‹አህያ›› ተብሎ የተሠየመው ይገኝበታል፡፡ ይህም ተመልካቾች ሲያዩት በማኅበረሰቡ ውስጥ የተሰጠው ቦታ እንዳለ እንዲረዱት መሆኑን ተናግሯል፡፡

ተመልካቹ በ‹‹አህያ›› የተሰየመውን ሥዕል ሲያይ የሚሰጠው የራሱ ምልክት ይኖራል ብሎ እንደሚያምን ገልጿል፡፡

ሠዓሊው አያይዞም ‹‹ለእኔ አህያ የሚገርምና የሚደንቅ እንስሳ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ሌሎች ተመልካቾች ደግሞ ለሥዕሉ የሚሰጡት ስያሜና ሁኔታ የሆነ ማኅበረሰብ እሳቤ ምልክት መሆኑ ሊሆን ይችላል፤›› ብሏል፡፡

በሥዕል ሥራዎቹ ለማስተማር የሚፈልገው ነገር እንደሌለ የገለጸው ሠዓሊ ዳዊት፣ ነገር ግን ሐሳብ ለማካፈልና ለማንፀባረቅ መሞከሩን ገልጿል፡፡

ሠዓሊው ሁኔታዎች፣ ነገሮች፣ ሒደቶችና ሐሳቦች ስለማያልቁ ሥራዎቹም ቀጣይነት እንዳለው ሳይገልጽ አላለፈም፡፡

ሠዓሊ ዳዊት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአለ የሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት ትምህርቱን አጠናቋል፡፡ ሥዕልና ፎቶግራፍን በማጣመር ተፈጥሯዊ የሆኑ ሐሳቦችን የሚያንፀባርቁ ሥራዎችን በመሥራትም ይታወቃል፡፡

ሠዓሊ ዳዊት የግል ሥራዎቹን ሲያቀርብ ለ16ኛ ጊዜ ሲሆን፣ በተጨማሪም የቡድን የሥዕል ዓውደ ርዕይ ላይ በአገር ውስጥ ከአገር ውጪ አቅርቧል፡፡

የሥዕል ዓውደ ርዕዩ ከመስከረም 9 እስከ መስከረም 30 ለተመልካች ክፍት መሆኑንም ተናግሯል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...