- ከ600 ሺሕ በላይ ሰዎች ኤችአይቪ ቫይረስ በደማቸው መኖሩ ተገልጿል
ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች፣ እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች የሚከሰቱት አደጋዎች የሚያደርሷቸው ጉዳቶች የኅብረተሰብ ጤና ከፍተኛ ችግሮች መሆናቸውን ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ እነዚህን ችግሮች ለመከላከልና ለመቆጣጠር ፍቱንነታቸው የተረጋገጡ መድኃኒቶች አቅርቦት መኖር የግድ ነው፡፡ አልፎ አልፎ ግን አቅርቦቱ በልዩ ልዩ ተግዳሮቶች ተተብትቦ ይስተዋላል፡፡
ተግዳሮቶቹም አንዳንድ መድኃኒቶች በአገር ውስጥ በገበያ አለመኖራቸው፣ ያሉትም ቢሆኑ ዋጋቸው ሰማይ ጥግ መድረስና ከታካሚዎች አቅም በላይ ሆኖ መገኘት፣ ሳይጠቀሱ የማይታለፉ ችግሮች ናቸው፡፡ ገበያውን ያጥለቀለቁትና ፍቱንነታቸው ያልተረጋገጡ ኮንትሮባንድ መድኃኒቶችም ፈተና ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አብድልቃድር ገልገሎ (ዶ/ር)፣ የአቅርቦት ችግር መኖሩን ያምናሉ፡፡ እንደ ዋና ዳይሬክተሩ እምነት ዘርፉ ከፍተኛ ገበያ ያለው ቢሆንም የተመዘገበ አቅራቢ ቁጥር ግን በጣም ውስን ነው፡፡ ይህም ሁኔታ ሊያጋጥም የቻለው የአቅርቦት ሰንሰለቱ በባህሪው ውስብስብና የተሳለጠ ባለመሆኑ ነው፡፡
ይህ ዓይነቱም አካሄድ ተወዳዳሪ የሆኑ አቅራቢዎችን ለማፍራት መሰናክል መሆኑን አብድልቃድር (ዶ/ር) ገልጸው፣ ከዚህ ችግር ለመላቀቅ መፍትሔው ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትና ከአቅራቢዎች ጋር ያለውን ግንኙነት ማጠናከር መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት መስከረም 6 ቀን 2014 ዓ.ም. ለሁለተኛ ጊዜ ባካሄደው ዓለም አቀፍ የመድኃኒትና ሕክምና መሣሪያ አቅራቢዎች ጉባዔ ላይ ዋና ዳይሬክተሩ እንደገለጹት፣ በአገልግሎት መዘርዘር ውስጥ ከተካተቱ 1020 ፈዋሽነታቸው ከተረጋገጡ መድኃኒቶች መካከል ከ970 በላይ በሆኑት ላይ በተካሄደው ዳሰሳ 257 ወይም 25 በመቶ የሚሆኑ መድኃኒቶች ምንም ዓይነት የተመዘገቡ አቅራቢዎች የላቸውም፡፡ ከዚህም ሌላ 231 ወይም 23 በመቶ መድኃኒቶች ያላቸው አቅራቢ አንድ ብቻ መሆኑን ዳሰሳው ያሳያል፡፡
ባለፉት ዓመታት አገልግሎቱ ከአቅራቢዎች ጋር የነበረው ግንኙነት ከገዥና ሻጭ ያለፈ እንዳልነበር፣ አሁን ግን ይህ ዓይነቱን መስተጋብር ያሻሽላል ተብሎ የታመነበት ተነሳሽነት (ኢንሼቲቭ) እና ፕሮጀክት ተቀርጾ ለተግባራዊነቱ ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ በመከናወን ላይ እንደሆነ ነው የተናገሩት፡፡
መንግሥት የመድኃኒት አቅርቦትን ለመደገፍ እያደረገ ያለውን ማበረታቻ ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት በኢትዮጵያም ሆነ በቀጣናው መድኃኒት በማስገባትና በመላክ ሥራ የተሰማሩ ድርጅቶች ወደ አምራች ዘርፍ እንዲቀላቀሉ ዋና ዳይሬክተር ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ ከ4,000 በላይ ለሚሆኑ የጤና ተቋማት ፍቱንነታቸው የተረጋገጡ መድኃኒቶችን በማቅረብ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት የተቋቋመው በ1939 ዓ.ም. መሆኑን ከዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡
የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት አስተዳደር ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሔራን ገርባ በበኩላቸው ባለሥልጣኑ ከፍተኛ የሆነ የማሻሻያ ሥራዎችን በማከናወን ላይ መሆኑን፣ በማሻሻያ ሥራዎቹ ውስጥ ከተካተቱትም መካከል የመድኃኒት መቆጣጠሪያ (ቴስቲንግ) ላቦራቶሪ እንደሚገኝበት አስረድተዋል፡፡
የጤና ሚኒስትር ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) በመድኃኒት አቅርቦት ላይ የታየውን ችግር ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየት የጋራ መፍትሔ ማምጣት በእጅጉ አስፈላጊ መሆኑን በተወካያቸው አማካይነት ባስተላለፉት መልዕክት ላይ ገልጸዋል፡፡
በሌላ ዜና በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2021 ያለው የኤችአይቪ የሥርጭት ምጣኔ 0.93 በመቶ እንደሆነና 617,921 የሚሆኑ ኤችአይቪ ቫይረስ በደማቸው ይገኛል ተብሎ እንደሚገመት የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
በሚኒስቴሩ የኤችአይቪ ኤድስና የቫይራል ሄፒታይተስ በሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር አስተባባሪ ወ/ሮ ምርቴ ጌታቸው እንዳስታወቁት፣ ከተጠቀሰው አኀዝ ውስጥ ኤችአይቪ ቫይረስ በደማቸው መኖሩን የሚያውቁት 84 በመቶ ናቸው፡፡
የኤችአይቪ ቫይረስ መጠን ልኬትና ለኤችአይቪ ተጋላጭ የሆኑ ጨቅላ ሕፃናት ምርመራ ላይ ያተኮረ ዓመታዊ የአፈጻጸም ግምገማ ሲካሄድ የተገኙት አስተባባሪዋ፣ የፀረ የኤችአይቪ ሕክምና አገልግሎት ከሚወስዱ 360,020 ከሚሆኑ ተገልጋዮች የቫይረስ ምጣኔ ምርመራ ተሠርቶ፣ 96.2 በመቶ የሚሆኑት በደማቸው የሚገኘው የቫይረስ መጠን ዝቅተኛ ወይም ከ1000 ኮፒ/ ሚሊ እንደነበር አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ እንደ አገር የተቀበለችውን የዓለም አቀፍ የ2030 የኤችአይቪ ቫይረስ ሥርጭትን ለመቀነስ የተቀመጠውን ግብና የሦስቱን ዘጠና አምስትን ግብ ለማሳካት በትብብርና በቅንጅት መሠራት እንዳለበት ማሳሰባቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡