በጦርነትና በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምከንያት የተጎዳውን የቱሪዝም ዘርፍ ለማነቃቃት እንዲሁም ደግሞ ከዚህ በፊት የነበረውን ልማዳዊ የቱሪዝም አሠራር ቀይሮ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግ፣ ‹‹አዲስ ዕሳቤ ለቱሪዝም›› የተሰኘ አሠራርን ወጥኖ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ሚኒስቴሩ ‹‹አዲስ ዕሳቤ ለቱሪዝም›› በሚል መሪ ቃል ከመስከረም 13 እስከ 15 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሚከበረው የዓለም ቱሪዝም ቀን ክብረ በዓል ላይ የተለያዩ ኩነቶች የሚቀርብበት መሆኑን፣ ቅዳሜ መስረም 7 ቀን 2015 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል፡፡
የቱሪዝም ሚኒስትር ናሲሴ ጫሊ (አምባሳደር) እንደገለጹት፣ በኢትዮጵያ የሚገኙ የቱሪስት መስህቦችን ለመጠቀምና በዘርፉ ላይ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት ሚኒስቴሩ አዳዲስ አሠራሮችን ዘርግቶ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡
የዘንድሮ የዓለም የቱሪዝም ቀን ሲከበር ለየት ከሚያደርገው ነገሮች መካከል መንግሥት እንደ አገር ትኩረት ከሰጣቸው አምስት ዘርፎች ውስጥ አንዱ የቱሪዝም ዘርፍ መሆኑን፣ ይህንንም ታሳቢ በማድረግ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎች መጠቀም እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ሚኒስቴሩ ባለፈው ዓመት እንደ አዲስ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ የአገር ውስጥ የቱሪዝም ንድፈ ሐሳቦችን ቀርፆ እየተንቀሳቀሰ ነው ያሉት ሚኒስትሯ፣ ይህንንም እንቅስቃሴ በመጠቀም የአገር ውስጥ የቱሪዝም ዕድገት ማሳደግ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚከበረው የዓለም ቱሪዝም ቀን ላይ በርካታ ኩነቶች የሚቀርቡበት እንደሆነ ገልጸው፣ ‹‹እነዚህን ኩነቶች ለማኅበረሰቡና ለቱሪስቶች በማሳየት ተግባራዊ ይደረጋል፤›› ሲሉ አክለው ገልጸዋል፡፡
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ከሚሰጠው አገልግሎት ባለፈ የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆን የተለያዩ ጥናቶች እየተደረጉ መሆኑን፣ ጥናቱና ዲዛይኑ ካለቀ በኋላ ለኢንቨስትመንት ክፍት እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡
ሚኒስቴሩ ከተለያዩ ቦታዎች ከተውጣጡ ተቋማት በጋራ በመሆን ጥናቱን እንደሚያደርግ የገለጹት አምባሳደሯ፣ ‹‹ይህም ከተጠናቀቀ በኋላ ባለሀብቶችን በመጋበዝ ቦታው ላይ ኢንቨስት አድርገው የተለያዩ ሥራዎች እንዲሠሩ ይደረጋል፤›› ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ በተለያዩ ቦታዎች ላይ የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎች በፀጥታ ምክንያት ችግር እያስተናገዱ መሆኑን፣ ይህንንም ለመቅረፍ ሚኒስቴሩ የተለያዩ ጥናቶችንና ዕቅዶችን በማዘጋጀት ወደ ሥራ መግባቱን አብራርተዋል፡፡
ጉዳት የደረሰባቸውንም የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች ላይ ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍ ተቋሙ ከብሔራዊ ባንክ ጋር በቅንጅት እየሠራ እንደሆነና ባንኩም የራሱ የሆነ መመርያ በማውጣት ዘርፉን እየደገፈ ነው ብለዋል፡፡
በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ከቦታ ቦታ ተዘዋውረው የሚጎበኙ ቱሪስቶች ቁጥር መቀነሱን፣ ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት ዘርፉ እንደ አዲስ በማገገም ከዘርፉ አመርቂ ውጤት እየተገኘ መሆኑን አክለዋል፡፡
የቱሪዝም ዘርፉን በቴክኖሎጂ የታገዘ ለማድረግ ከባንኮች ጋር ሆነ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተሠራ መሆኑን ያስታወሱት ሚኒስትሯ፣ በተለይም የቱሪዝም ዘርፉ ላይ እንደ አዲስ ፖሊሲዎችን በመከለስ ሰፊ እንቅስቃሴ መጀመሩን ጠቁመዋል፡፡
‹‹የዘንድሮው የዓለም ቱሪዝም ቀን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሲከበር የክልሉ ባህላዊ ትውፊቶች፣ ታሪካዊና ባህላዊ የሆኑ ቦታዎች የሚጎበኙበት ይሆናል፤›› ያሉት የክልሉ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ምስኪያ አብደላ ናቸው፡፡
በክብረ በዓሉ ላይም የክልሉ ባህላዊ የትንፋሽ ሙዚቃ መሣሪያን ለዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ የተጀመረበት ሒደትን ለማኅበረሰቡ የምናሳይ ይሆናል በማለት ኃላፊዋ ገልጸዋል፡፡
ለሦስት ቀናት በሚከበረው በዓል ላይ የዕደ ጥበብ ውጤቶች፣ ባህላዊ ምግቦች፣ የታላቁ ህዳሴ ግድብ እውነታዎች የሚታይበት በቂ የሆነ ዝግጅት ክልሉ ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡
የዓለም የቱሪዝም ቀን በአገር አቀፍ ደረጃ ለ35ኛ ጊዜ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ43ኛ ጊዜ ‹‹አዲስ ዕሳቤ ለቱሪዝም›› በሚል መሪ ቃል በኢትዮጵያ በተለያዩ ቦታዎች ተከብሮ እንደሚውል ተገልጿል፡፡