‹‹ጦርነቱ በአጭሩ ካልቆመ ማዕቀብ አንዱ አማራጭ ይሆናል››
የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ
በአሸናፊ እንዳለና በሲሳይ ሳህሉ
ለሦስተኛ ጊዜ ያገረሸውን የሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት የሰላም መፍትሔ ለመስጠት በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት መካከል መተማመን መጥፋቱ፣ እንዲሁም የውጪ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት መኖሩ አዳጋች እንዳደረገው የአሜሪካ መንግሥት ገለጸ፡፡
ከሳምንታት በላይ በአፍሪካ ቀንድ ቆይታ ያደረጉትና የኢትዮጵያና የትግራይ ባለሥልጣናትን ቢያንስ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ጥረት ሲያደርጉ የነበሩት የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሀመር፣ ያለውጤት ወደ አገራቸው መመለሳቸውን ትናንት ሐሙስ በሰጡት የበይነ መረብ ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ጥያቄና መልስ ላይ ተናግረዋል፡፡
በሁለቱ መካከል በጂቡቲ ድርድር ስለመደረጉ የተጠየቁት አምባሳደር ሀመር ‹‹ጠለቅ ያለ መልስ መስጠት አልችልም›› ያሉ ሲሆን በአፍሪካ ኅብረት በኩል አሁንም ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
የአሜሪካ መንግሥትና ተመድ የኤርትራ ጦር ከጦርነቱ እንዲወጣ የጠየቁ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ሕወሓትን እያገዙ መሆናቸውን ሲገልጽ ቆይቷል፡፡
ሦስተኛው ጦርነት ከመጀመሩ ሳምንታት ቀደም ብሎ ሕወሓት መሠረታዊ አገልግሎቶች ካልተጀመሩ ሌላ ዙር ጦርነት ለማድረግ ከፍተኛ ዝግጅት ሲያደርግ እንደነበረ አምባሳደር ሀመር ገልጸዋል፡፡ የፌዴራል መንግሥት በበኩሉ መሠረታዊ አገልግሎቶቹን ለመጀመር የደኅንነት ዋስትና ጥያቄ ማንሳቱን ልዩ መልዕክተኛው አክለው ገልጸዋል፡፡
‹‹በአገልግሎቶቹ አጀማመር ሁኔታ (Modality) ላይ ተጨማሪ ንግግር ያስፈልግ ነበር፡፡ ይህ በሒደት እንዳለ ግን አላስፈላጊ ጦርነት በመሀል ተጀመረ፤›› ብለዋል ልዩ መልዕክተኛው፡፡ ሕወሓት አደራዳሪ ሆነው በአፍሪካ ኅብረት በተሾሙት ኦባሳንጆ ላይ የሚያቀርበውንም የኢተዓማኒነት ክስ እንደማይጋሩት ልዩ መልዕክተኛው ተናግረዋል፡፡
ለሦስተኛ ጊዜ ወደ አፍሪካ ቀንድ የተላኩት የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ማይክ ሀመር፣ ኢትዮጵያውያን እየተሰቃዩበት የሚገኘው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት እንዲያበቃ በአፍሪካ ኅብረት የተጀመረውን ሰላማዊ ድርድር ሒደት እንደግፋለን ብለዋል፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ሦስተኛው ዙር ጦርነት ከመጀመሩ በፊት ወደነበረበት ተመልሶ፣ የተኩስ አቁም ስምምነት ተደርሶ የሰላም ድርድሩ እንደገና እንዲጀመር አሁንም ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ተነግሯል፡፡
‹‹ሁለቱም አካላት ጠንካራ ድርድር ለማድረግ ፍላጎት አላቸው፡፡ ነገር ግን በሁለቱ መካከል በቂና ጠንካራ መተማመን ለመፍጠር ተጨማሪ ሥራ ይፈልጋል፡፡ ሁለቱ አካላት ካሉበት ‹ያለመግባባት› ሁኔታ ወጥተው በየደረጃው ወደ ተኩስ አቁም ከዚያም ወደ ድርድር እንዲሄዱ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረግን ነው፡፡ መፍትሔው ግን ከራሳቸው ከኢትዮጵያውያን መምጣት አለበት፤›› ብለዋል ልዩ መልዕክተኛው፡፡
ይሁን እንጂ የጦርነቱ ተሳታፊዎች በአጭሩ ወደ ሰላማዊ መፍትሔ የማይሄዱ ከሆነ፣ አሜሪካ ማዕቀቦችን ለመጣል እንደማታመነታ አምባሳደሩ አልሸሸጉም፡፡
‹‹ወደ ሰላማዊ መፍትሔ እንዲመጡ የተለያዩ አማራጮችን እየተጠቀምን ነው፡፡ ቅድሚያ ሰጥተን ከዓለም አቀፍና ማኅበረሰቡ ጋር እየሠራን ያለነው በሁለቱ መካከል እምነት መፍጠር ነው፡፡ እሱ ካልተሳካ ግን ማዕቀብ ከመጣል አናመነታም፤›› ብለዋል፡፡
በወዳጅነት ላይ የተመሠረተ የአሜሪካ ፖሊሲ መኖሩን የሚናገሩት ልዩ መልዕክተኛው፣ የሚጫወቱት ሚና ዋነኛ ማጠንጠኛው የኢትዮጵያውያን አንድነትና የድንበር ሉዓላዊነት መሆኑን በመግለጽ፣ ዓላማችን ሰላማዊ መንገዶችን ማፈላለግ ብሎም በድርቅ እየተጎዱ ላሉ ዜጎች ጭምር የሰብዓዊ ዕርዳታ አግልግሎት ተደራሽ እንዲሆን ማድረግ ነው ብለዋል፡፡
‹‹ከኢትዮጵያ ጋር ታሪካዊና ስትራቴጂካዊ የሆነ ወዳጅነት ስላለን ሁለቱም በጦርነት ውስጥ የገቡ ወገኖች በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት ለተጀመረው የአደራዳሪነት ሚና አሜሪካ የምታደርገውን አስተዋጽኦ በሁለቱ ወገኖች ዘንድ ተዓማኒነት ይኖረዋል ብለን እናስባለን፤›› ብለዋል፡፡
አምባሳደሩ የአሜሪካ ሚና ለኢትዮጵያውያን የተሻለውን ተስፋ የመፍጠርና ከባድና አስቸጋሪ የሆነውን የፖለቲካ ሁኔታ በድርድር እንዲፈቱ ማስቻል መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አክለውም የኤርትራ በጦርነቱ መሳተፍ ሁኔታውን የበለጠ እንደሚያባብሰውና እንደሚያቀጣጥለው አስረድተዋል፡፡
በጦርነት ሁለቱም አካላት ድል አያመጡበትም፣ ስለዚህ ዋነኛ ማጠንጠኛ መሆን ያለበት ጦርነቱ ቆሞ የሰብዓዊ ዕርዳታ ተደራሽነቱን ማረጋገጥ፣ በትግራይ ክልል ያለውን መሠረታዊ አገልግሎት ወደ ሥራ ማስገባትና የፖለቲካ ጥያቄዎች ላይ ኢትዮጵያውያን ራሳቸው ድርድር ማድረግ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
በቀጣይ ቀናት ከአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ከኦሌሴጉን ኦባሳንጆ ጋር ድርድሩ እንዴት መጀመር እንዳለበት ተጨማሪ የዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ ለአፍሪካ ኅብረት ድጋፍ የሚያደርጉ አስተባባሪዎች የተካተቱበት ውይይት በቀጣይ በአሜሪካ ኒዎርክ ከተማ እንደሚካሄድ ተናግረዋል፡፡
በጦርነት ውስጥ የገቡት ሁለቱ ወገኖች ከዓለም አቀፍ ተቋማት የሚቀርቡ የድጋፍ ድምጾችን መቀበል በቻሉ ቁጥር ወደ መፍትሔውና ድርድሩ የመግባት ዕድል እንዳላቸው ሁሉ ማድመጥ ካልቻሉ ግን ጦርነቱን የማስቀጠል ዕድላቸው እየጨመረ እንደሚሄድ ተናግረዋል፡፡