ንግድ ሚኒስቴር በወጣው የዋጋ ተመን ብቻ መሸጥ እንዳለባቸው በድጋሚ አሳሰበ
ዳንጎቴ፣ ሐበሻ፣ ናሽናልና ኢትዮ ሲሚንቶን ጨምሮ ሰባት የሲሚንቶ አምራቾች፣ በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት ረቡዕ መስከረም 4 ቀን 2015 ዓ.ም. የወጣውን ሲሚንቶ የፋብሪካ መሸጫ ዋጋ ውሳኔን በመቃወም ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ቅሬታቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ አስገቡ፡፡
ሚኒስቴሩ ያወጣው የፋብሪካ መሸጫ ዋጋ ተመን ከመስከረም 5 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ለሦስት ወራት እንደሚቆይ ያስታወቀ ሲሆን፣ ሁሉም ፋብሪካዎች ከመጋቢት ወር 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ሲሸጡበት ከነበረው ዋጋ በኩንታል በአማካይ 92 ብር ዝቅ ያደርገዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሲሚንቶ አምራቾች ማኅበር ሚኒስቴሩ ባሳለፈው ውሳኔ ላይ ለመምከር መስከረም 5 ቀን 2015 ዓ.ም. ባካሄደው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ ቀድሞ ከተጠቀሱት ጋር ኢስት፣ ኩዩና ሬድ ፎክስ ሲሚንቶን ጨምሮ ሰባት አምራች የማኅበሩ አባላት ተገኝተዋል፡፡ የተገኙት ሰባቱ አባላትም ቃለ ጉባዔው ላይ በመፈረም ተቃውሟቸውን በመግለጽ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበሩ አማካይነት ደብዳቤ ጽፈዋል፡፡ ሌሎች የማኅበሩ አባል የሆኑት ደርባ፣ ሙገር፣ ዳሸን፣ ካፒታልና ፓዬኔር ሲሚንቶ አምራቾች በስብሰባው ላይ አልተገኙም፡፡
በማኅበሩ ምክትል ሰብሳቢ አቶ መስፍን አበራ ተፈርሞ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተላከው ደብዳቤ፣ በጉባዔው የተነሱትን የዋጋ ተመኑን አካሄድ የሚመለከት አምስት ዋነኛ የማኅበሩን ቅሬታዎች ያነሳል፡፡
ከቅሬታዎቹም መካከል የዋጋ ተመኑ ሲወጣ ፋብሪካዎች ያሉበትን የቦታና የግብዓት አቅርቦት ርቀት አለመረዳት፣ የግብዓት ዋጋ በየጊዜው መናርን በተገቢው ግምት አለማስገባትና እያንዳንዳቸው ፋብሪካዎች ያለባቸውን እንደ ኃይልና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ዓይነት ልዩነት ያላቸው ወጪዎችን በአንድ ወጪ ቀመር መሣል ናቸው፡፡ በተጨማሪም እንዲህ ዓይነት ውሳኔዎች በመንግሥትና በባለሀብቱ መካከል ቅሬታን ይፈጥራል ሲልም ደብዳቤው ይገልጻል፡፡
አምራቾቹ ቅሬታቸውን ካቀረቡ በኋላም መሥሪያ ቤቱ መስከረም 9 ቀን 2015 ዓ.ም. ከሚኒስትሩ አቶ ገብረ መስቀል ጫላ ጋር ስብሰባ በመጥራት፣ ለቀጣይ ሦስት ወራት የሚቆየውን ይህንን ውሳኔ ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸው ያሳሰባቸው መሆኑን፣ የሚኒስትሩ ሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ወ/ሮ ቁምነገር ዕውነቱ ለሪፖተር ገልጸዋል፡፡
‹‹ይህንን ውሳኔ ተግራዊ በማያደርጉ ላይ ዕርምጃ ይወስዳል፡፡ ሁሉም ይህንን አዲስ የፋብሪካ ዋጋ ተግባራዊ እያደረጉ ነው፡፡ አንድ ተግባራዊ ያላደረገ ፋብሪካ ላይም ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል፤›› ሲሉ ወ/ሮ ቁምነገር አክለው ገልጸዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት የተወሰነው ይህ ውሳኔ ኢትዮ ሲሚንቶና ኢስት ሲሚንቶ በእኩል ዋጋ ኩንታል በ595.66 ብር እንዲሸጡ፣ ከፍተኛዎቹ ዋጋዎች ደግሞ ሐበሻ በ683.44 ብር፣ ሙገር በ643.95 ብር፣ ካፒታል በ633.38 ብርና ኩዩ በ628.10 ብር በእንዲሸጡ ያዛል፡፡ በሌላው ደረጃ ደግሞ ከዝቅተኛ ጀምሮ ፓዮኔር ኩንታል በ510.04 ብር፣ ዳንጎቴ በ549.49 ብር፣ ናሽናል በ561.39 ብርና ደርባ በ590.59 ብር እንዲሸጡ ያዛል፡፡
ሁሉም አምራቾች ካለፈው መጋቢት 2014 ዓ.ም. በፊት ይሸጡበት የነበረው ዋጋ ኩንታል ከ407 ብር እስከ ትልቁ 520 ብር ይሸጡ የነበረ ሲሆን፣ በዚያን ጊዜ ባደረጉት ጭማሪ ኩንታል ከትንሹ 620 ብር እስከ 790 ብር ይሸጡ እንደነበር ከሚስኒትሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ ባለፈው ሳምንት ሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ እንዲሸጡ ባወጣው ትዕዛዝ መሠረት ግን ሲሸጡበት የነበሩበትን ዋጋዎች በአማካይ ኩንታል በ92.27 ብር ዝቅ ያደርገዋል፡፡
መሥሪያ ቤቱ ይህንን ውሳኔ ቢያሳልፍም የሲሚንቶ ዋጋ መናርና አቅርቦት አለመኖር አሁንም መስተካከል አለማሳየቱ የሚታይ ሲሆን፣ ይህንንም በሚመለከት አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የአምራች ድርጅት ኃላፊ፣ ‹‹በሽታው ሌላ፣ መድኃኒቱ ሌላ፤›› ሲሉ የሚኒስትሩ ውሳኔ መፍትሔ ላይ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል አለመሆኑን አክለው ተናግረዋል፡፡
የሲሚንቶ ምርትን ማሳደግ አለመቻል፣ እንዲሁም የሚመረተውን ባለበት አለማስቀጠልና በገበያ ትስስር ውስጥ ካለው ችግር ጋር አብሮ እየተፈጠረ ያለውን ችግር ያባባሰው እንደሆነ በመግለጽ፣ እኚህ ኃላፊ በፋብሪካዎች ላይ የሚወሰደውን ዕርምጃ ኮንነዋል፡፡ ‹‹አምራቾች በግብዓት አቅርቦት እጥረት፣ ዋጋ መወደድ ምክንያትና ሌሎች በኢትዮጵያ ባሉ ችግሮች የማምረት አቅማቸው ቀንሷል፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ እንደ ኃላፊው ገለጻ፣ ‹‹እየተመረተች ያለችውንም ትንሽ ምርትም በአከፋፋዮችና በቸርቻሪዎች ከፍተኛ ዋጋ በመጨመር እየተሸጠ ነው፤›› ሲሉ በገበያ ትስስር ውስት ያለውን ችግር ተናግረዋል፡፡
ማኅበሩ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በጻፉት ደብዳቤም የፋብሪካዎች የማምረት አቅም መቀነስና የተመረተው ሲሚንቶ ከፋብሪካው ከወጣ በኋላ ወደ ገበያ የሚቀርብበት ሥርዓት ችግሮች ዋነኛ በዘርፉ ላይ ያሉ ተግዳሮቶች መሆናቸውን ገልጿል፡፡