በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተቋቋመው የሚኒስትሮች ግብረ ኃይል የሕወሓ ኃይሎች በአፋርና በአማራ ክልሎች የፈጸሟቸውን ወንጀሎች አስመልክቶ ሲያደርግ የቆየውን ምርመራ ውጤት እያጠናቀቀ እንደሆነና ይፋ ሊያደርግ መሆኑን የግብረ ኃይሉ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡
የግብረ ኃይሉ የወንጀል ምርመራ ሪፖርት ይፋ ሲያደርግ የጀመርያ መሆኑን ያስታወሱት የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ ታደሰ ካሳ (ዶ/ር) በምርመራ የተዳሰሱት አካባቢዎች ላይ የተፈጸሙት ከፍርድ ውጪ የሆኑ ግድያዎች፣ አስገድዶ መድፈርና ወሲባዊ ጥቃቶች እንዲሁም ዘረፋዎችና ሌሎች ወንጀሎች በዝርዝር እንደሚቀርቡ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
እንደ ኃላፊው ገለጻ ዛሬ ይፋ የሚደረገው የምርመራ ሪፖርት፣ በምዕራፍ አንድ ምርመራ የተዳሰሱ ወንጀሎችን የሚሸፍን ነው፡፡ የዚህ ምርመራ ምዕራፍ ሁለት በመከላከያ ሠራዊት አባላት የተፈጸሙ ወንጀሎችን እንደሚሸፍን ታደሰ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡ ሦስተኛው ምዕራፍ ደግሞ ወልቃይት፣ ፀገዴ፣ ሁመራ አካባቢዎች የተፈጸሙ ወንጀሎችን እንዲሁም በጦርነቱ ምክንያት በአፋር ክልል ሳይሰበሰቡ የቀሩ መረጃዎችን የሚሸፍን እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ታደሰ (ዶ/ር)፣ ‹‹ምዕራፍ አንድ ስለተጠናቀቀ ሌሎቹን ከሚጠብቅ ራሱን ችሎ እንዲወጣ ስላሰብን ነው፤›› በማለት የመጀመርያው ምዕራፍ ምርመራ ሪፖርት ይፋ የሚደረግበትን ምክንያት አስረድተዋል፡፡
የመከላከያ ሠራዊት አባላት በአማራና አፋር ክልሎች የፈጸሟቸውን ወንጀሎች የሚመረምረው ምዕራፍ ሁለት ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን የተናገሩት ኃላፊው፣ የምዕራፍ ሁለት ምርመራ ውጤት ኅዳር ወይም ታኅሳስ ወር ላይ ይፋ ሊደረግ እንደሚችል አስታውቀዋል፡፡
የመከላከያ ሠራዊት አባላት በሁለቱ ክልሎች ፈጸሟቸው የሚባሉ ወንጀሎች አነስተኛ መሆናቸውን ገልጸው፣ ‹‹ሕወሓት ፈጸመው የተባሉ ወንጀሎች እየተመረመሩና ክስ እየተመሠረተ የራስህ ኃይል የፈጸመውን ወንጀል አለመመርመር አድሏዊ አሠራር ነው፣ መሠረታዊ መርሁ ሁሉም ተጠያቂ መሆን አለበት የሚል ነው፤›› ብለዋል፡፡
በትግራይ ክልል ውስጥ የተፈጸሙ ወንጀሎችንም በተመለከተ ሁኔታዎች ሲመቻቹ ተመሳሳይ ሒደት እንደሚቀጥል ተገልጿል፡፡
የሚኒስቴሮች ግብረ ኃይል በስሩ ካሉ አራት ኮሚቴዎች መካከል አንዱ የሆነው የምርመራና ክስ ኮሚቴ በአማራና አፋር ክልሎች ምርመራውን ሲያደርግ የነበረው 158 አባላት የምርመራ ቡድን በማሰማራት ነው፡፡ ቡድኖቹ በሁለቱ ክልሎች የተሰማሩት ዘጠኝ አካባቢዎች ተመርጠው ሲሆን ስምንቱ የሚገኙት በአማራ ክልል ነው፡፡
በአማራ ክልል ምርመራ የተደረገው በወልዲያ፣ ላሊበላ፣ ሰቆጣ፣ ጃማ ወረኢሉ፣ ደሴና ኮምቦልቻ አካባቢዎች እንዲሁም፣ ሰሜን ሸዋ ዞንና ኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ነው፡፡
በእነዚህ አካባቢዎች ለተደገው ምርመራ ከ10 ሺሕ በላይ ምስክሮች ቃለ መጠይቅ እንደተደረገላቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ማስረጃዎችንም በቪዲዮ የመቅረፅ ሥራ እንደተከናወነም ታውቋል፡፡
የግብረ ኃይሉ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ታደሰ (ዶ/ር) በምርመራው የተገኘውን ውጤት ባይገልጹም፣ በግብረ ኃይሉ ምርመራ የሕወኃትና ኦነግ ሸኔ ኃይሎች 3,598 ንፁኃን ከፍርድ ውጪ መግደላቸውን እንዳረጋገጠ፣ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል፡፡ ምርመራ በተደረገባቸው አካባቢዎች 2,212 ሰዎች አስገድዶ መድፈርና ሌሎች የወሲባዊ ጥቃቶች እንደተፈጸሙባቸው ተዘግቧል፡፡