የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ውስጥ የተሳተፉ አካላት በሙሉ፣ የጦር ወንጀሎች መፈጸማቸውን ለማመን የሚያስችል በቂ ምክንያት ማግኘቱን አስታወቀ፡፡
በተመድ የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ የተቋቋመው ኮሚሽኑ፣ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነትን አስመልክቶ ሰኞ መስከረም 9 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጣው የመጀመርያ ሪፖርቱ፣ የፌዴራል መንግሥት ኃይሎች በሰብዕና ላይ የተፈጸመ ወንጀል አከናውነዋል ብሎ ለማመን የሚያስችል በቂ ምክንያት ማግኘቱን ገልጿል፡፡
ኮሚሽኑ በሁለት ወራት ውስጥ በተመረጡ ጉዳዮች ላይ ባደረገው ምርመራ፣ በጦርነቱ ውስጥ የተሳተፉት የፌዴራል መንግሥት፣ የትግራይ ኃይልና የኤርትራ መንግሥት የንፁኃን ግድያ፣ ወሲባዊ ጥቃትና ሰብዓዊነትን የማዋረድ ወንጀሎችን እንደፈጸሙ ለማመን እንደቻለ አስረድቷል፡፡ በተጨማሪም የፌዴራል መንግሥትና የትግራይ ኃይል ‹‹ሆን ብለው›› በንፁኃን ሰዎችና ንብረቶች ላይ ጥቃት ፈጽመዋል ብሏል፡፡
የፌዴራል መንግሥት ‹‹የዜጎችን ረሃብ እንደ ጦርነት መሣሪያ›› ተጠቅሟል ለማለት የሚያስችል በቂ ምክንያት እንዳገኘ ኮሚሽኑ በሪፖርቱ ጠቅሷል፡፡ ኮሚሽኑ የፌዴራል መንግሥት ኃይሎች በትግራይ ተወላጆች ላይ ፈጽመዋል ያላቸውን እንደ ከፍርድ ውጪ ያለ ግድያ፣ አስገድዶ መድፈርና ፆታዊ ጥቃት ጠቅሶ፣ ‹‹የፌዴራል መንግሥት በሰብዕና ላይ የተፈጸመ ወንጀል›› ስለማከናወኑ በቂ ማስረጃ ስለማግኘቱ በሪፖርቱ አካቷል፡፡
የኮሚሽኑ ሪፖርት እንደሚያስረዳው የምርመራ ሥራው የተከናወነው ከሰኔ ወር አጋማሽ ጀምሮ ሲሆን፣ ባጋጠሙት ተግዳሮቶች የተነሳ ምርመራውን ለማከናወን የተፈቀዱለት ሁለት የሙሉ ጊዜ መርማሪዎች ብቻ ናቸው፡፡
የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽነሮች ምርመራውን ሲያከናውኑ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የፌዴራል መንግሥት ባለሥልጣናት፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ ምሁራንና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ያነጋገሩ መሆናቸውንና ከሕወሓት አመራሮች ጋር ደግሞ በርቀት መነጋገራቸውን ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡
ኮሚሽነሮቹ ወደ ኢትዮጵያ በመጡ ጊዜ ከአዲስ አበባ ውጪ ለመሄድ አልተፈቀደላቸውም ነበር፡፡ በተመሳሳይ ምርመራው ሲካሄድ በሱዳንና በጂቡቲ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ለማነጋገር ጠይቀው፣ አገሮቹ እንዳልፈቀዱላቸው በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡ በዚህም ምክንያት ምርመራው ሲደረግ ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸው 185 ተጎጂዎች፣ ምስክሮችና መረጃ ሰጪዎችን ማግኘት የቻሉት ‹‹በርቀት ቃለ መጠይቅ›› መሆኑን የኮሚሽኑ ሪፖርት ያብራራል፡፡
ሪፖርቱ እንደሚገልጸው ኮሚሽኑ ምርመራውን ለማድረግ ካለበት የሀብት ማነቆ አኳያ፣ ሪፖርቱን በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ሲል፣ ምርመራውን ያደረገው በተመረጡ ክስተቶችና ጉዳዮች መሆኑን አስታውቋል፡፡
በዚህም መሠረት ኮሚሽኑ የመረጣቸው ክስተቶች፣ ‹‹በመቀሌ ከተማ በንፁኃን ሰዎችና ንበረቶች ላይ የተካሄደ የከባድ መሣሪያ ድብደባ፣ የቆቦና የጭና ግድያዎችና በደደቢት የሚገኝ የተፈናቃዮች ካምፕ ላይ የተፈጸመ የድሮን ጥቃት›› መሆናቸውን በሪፖርቱ ላይ አሥፍሯል፡፡ ከክስተቶች በተጨማሪ፣ ‹‹አስገድዶ መድፈርና ፆታዊ ጥቃት›› እና ‹‹የሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽነት ክልከላና ማስተጓጎል›› በርዕሰ ጉዳይነት መርጦ ምርመራ ማድረጉን አስታውቋል፡፡
የኮሚሽኑ ሪፖርት፣ ‹‹በመቀሌ ከተማ በንፁኃን ሰዎችና ንብረቶች ላይ የተካሄደ የከባድ መሣሪያ ድብደባ›› በተመለከተ ኅዳር 19 ቀን 2013 ዓ.ም. በመከላከያ ሠራዊት የተፈጸመ ነው ብሏል፡፡ የመከላከያ ሠራዊት አባላት መቀሌ ከተማን ከተቆጣጠሩበት እስከ ወጡበት ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም. ባለው የሰባት ወራት ጊዜ ውስጥ ከፍርድ ውጪ ግድያ፣ አስገድዶ መድፈርና ሌሎች የፆታዊ ጥቃት ዓይነቶች እንዲሁም ዝርፊያ ‹‹ሲያከናውኑ ነበር›› የሚል ክስ አቅርቧል፡፡
የ‹‹ቆቦና የጭና ግድያዎች››ን በተመለከተ ደግሞ የትግራይ ኃይሎች ከነሐሴ 2013 እስከ መስከረም 2014 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ ‹‹ንፁኃንን ሲገድሉ፣ አስገድዶ መድፈር ሲፈጽሙ፣ ዝርፊያ ሲያከናውኑና መሠረተ ልማቶችን ሲያወድሙ›› እንደነበር ሪፖርቱ ይገልጻል፡፡
በሦስተኛነት የተጠቀሰውን፣ ‹‹በደደቢት የሚገኝ የተፈናቃዮች ካምፕ ላይ የተፈጸመ የድሮን ጥቃት›› በተመለከተ ድርጊቱን የፈጸመው ‹‹የመከላከያ ሠራዊት›› እንደሆነ ያስታወቀው ሪፖርቱ፣ በዚህም ምክንያት 60 ንፁኃን ሰዎች ተገድለዋል ብሏል፡፡ ታኅሳስ 29 ቀን 2014 ዓ.ም. ተፈጽሟል በተባለው በዚህ የድሮን ጥቃት መሠረተ ልማቶች መውደማቸውን ሪፖርቱ አስረድቷል፡፡
ኮሚሽኑ በጦርነቱ የተፈጸሙ አስገድዶ መድፈርና ፆታዊ ጥቃትን በተመለከተ ምርመራ ማደረጉን የሚያስረደው ሪፖርቱ፣ በማጠቃለያው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ የኤርትራ መከላከያ ሠራዊትና ፋኖ አስገድዶ የመድፈርና የፆታዊ ጥቃት ድርጊቶችን ‹‹በስፋት›› ሲፈጽሙ እንደነበር ጠቅሷል፡፡ በትግራይ ኃይሎች በአንፃሩ የተፈጸሙ አስገድዶ መድፈርና ፆታዊ ጥቃት ‹‹አነስተኛ መጠን›› ያላቸው ናቸው ብሏል፡፡
ሪፖርቱ ‹‹የሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽነት ክልከላና ማስተጓጎል›› በሚል በተመረጠው ርዕሰ ጉዳይ ላይ ኮሚሽኑ፣ የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ‹‹ወደ ትግራይ ክልል ሰብዓዊ ድጋፍ እንዳይደርስ የተቀናጀ ዕርምጃ ወስደዋል፤›› ሲል ክስ አቅርቧል፡፡
እነዚህን የምርመራ ውጤቶች የዘረዘረው የኮሚሽኑ ባለ 19 ገጽ ሪፖርት በማጠቃለያው ላይ ባስቀመጣቸው ምክረ ሐሳቦች፣ ሁሉም አካላት ምርመራ አድርገው ወንጀል ፈጻሚዎችን ለፍትሕ እንዲያቀርቡ ጠይቋል፡፡
በተጨማሪም ሁሉም ኃይሎች ጦርነቱን ለማቆምና ለድርድር ቁርጠኛ እንዲሆኑ ምክረ ሐሳብ አቅርቧል፡፡