- ዓምና ከቀረበው ሁለት ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ አልተሠራጨም
ለመጪው የሰብል ዘመን (2015/16 ዓ.ም.) ጥቅም ላይ የሚውል የአፈር ማዳበሪያ ግዥ ለማከናወን ዓለም አቀፍ የማዳበሪያ ግዥ ጨረታ ወጣ፡፡
ከዓለም አቀፍ የማዳበሪያ ዋጋ መናርና ከዩክሬንና ከሩሲያ ጦርነት ጋር ተያይዞ ለ2014/15 የሰብል ዘመን ጥቅም ላይ የሚውል ማዳበሪያ ግዥ ፈጽሞ ለአርሶ አደሩ ለማድረስ በብርቱ ተፈትኖ የነበረው መንግሥት፣ ካለፈው የግዥ ሒደት ተሞክሮ በመውሰድ ለመጪው የሰብል ዓመት የሚያገለግል የአፈር ማዳበሪያ በጊዜ ለማቅረብ ዓለም አቀፍ ጨረታ ማውጣቱን የግብርና ሚኒስትር ደኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
የመጪውን ምርት ዘመን የማዳበሪያ አቅርቦት ለማሳካት የማዳበሪያ ግዥ ሒደት አንዱ ክፍል የሆነው የጨረታ እንቅስቃሴ በዚህ ወቅት ወጥቷል ብለዋል፡፡
ለሰብል ዘመኑ ምን ያህል መጠን ያለው የአፈር ማዳበሪያ ለመግዛት መንግሥት እንዳቀደ ከመግለጽ የተቆጠቡት ሚኒስትር ደኤታዋ፣ የሚገዛው ማዳበሪያ ከአገሪቱ ፍላጎት ምን ያህል ነው የሚለው በቅርቡ እንደሚገለጽ ተናግረዋል፡፡
ባለፈው ዓመት ከማዳበሪያ ግዥ ጋር በተገናኘ ያጋጠመውን መስተጓጎል በተያዘው ዓመት እንዳያጋጥም መንግሥት አስቀድሞ ግዥውን ለመፈጸም ቅድመ ዝግጅት አጠናቆ ጨረታ ማውጣቱን የተናገሩት ሶፊያ (ዶ/ር)፣ የማዳበሪያ ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ በመጨመሩ ሰው ሠራሽ ማዳበሪያ ከውጭ ከማስገባት ይልቅ አርሶ አደሩ የተፈጥሮ ማዳበሪያ እንዲያዘጋጅና ሌሎች በአገር ውስጥ ካሉ ግብዓቶች መዘጋጀት የሚችሉ ፈሳሽ ማዳበሪያዎችን (በተለይም ዩሪያን በተወሰነ ደረጃ መተካት የሚችሉ) በስፋት እንዲጠቀም የማድረጉ ሥራ በተጠናከረ ሁኔታ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
በ2013 የምርት ዘመን 18 ሚሊዮን ማዳበሪያ ተገዝቶ 14.5 ሚሊዮን ያህሉ መሠራጨቱ የተገለጸ ሲሆን፣ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ደግሞ 12.9 ሚሊዮን ማዳበሪያ በግዥ፣ እንዲሁም ካለፈው የምርት ዘመን ቀሪ የሆነ 2.3 ሚሊዮን የከረመ ማዳበሪያ ጋር በድምሩ 15.2 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ቀርቦ 13 ሚሊዮን ኩንታል የሚሆነው መሠራጨቱ ታውቋል፡፡
መንግሥት ዓምና ካቀረበው ማዳበሪያ ውስጥ ሁለት ሚሊዮን ኩንታል የሚሆነው ያልተሠራጨና የተረፈ መሆኑን ተገልጾ፣ ይህ ማዳበሪያ ለመስኖ ስንዴ ምርትና ለበልግ ተጠቃሚ አርሶ አደሮች ይውላል፡፡
መንግሥት ለ2014/15 የሰብል ዘመን እንዲውል ወደ አገር ውስጥ ላስገባቸው ዩሪያ፣ ኤንፒኤስና ኤንፒኤስቢ የአፈር ማዳበሪያዎች ግዥ፣ ማጓጓዣና ሌሎች ወጪዎች ከ64.5 ቢሊዮን ብር በላይ ማውጣቱ የሚታወስ ሲሆን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት እጥረት የማዳበሪያ ዋጋ በከፍተኛ ዋጋ በመጨመሩና ይህ ጭማሪ በአርሶ አደሮች ላይ ከፍተኛ ጫና ስለሚፈጥር፣ ለማዳበሪያ ግዥ ከወጣው አጠቃላይ ወጪ 25 በመቶ ወይም 15 ቢሊዮን ብር ድጎማ መደረጉን ከዚህ ቀደም መገለጹ የሚታወስ ነው፡፡
ለአርሶ አደሩ በተለይም በቀጣይ የሚሠራጨው ማዳበሪያ በድጎማ ይቀርባል ወይ የሚለውን ዓለም አቀፉ የማዳበሪያ ዋጋ ይወስነዋል ያሉት ሶፊያ (ዶ/ር)፣ ባለፈው ዓመት የነበረው የማዳበሪያ ዋጋ ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በጣም ጨምሮ ስለነበር መንግሥት ይህንኑ ከግምት በመውሰድ በአንድ ኩንታል 1,100 ብር ድጎማ ማድረጉን አስረድተዋል፡፡
የክልሎች የማዳበሪያ ፍላጎት በዲጂታል መንገድ የሚሰበሰብ ስላልሆነ መቶ በመቶ ትክክለኛ ፍላጎት ነው ወይ የሚለው በጥያቄ ምልክት ውስጥ የሚቀመጥ ነው ያሉት ሚኒስትር ደኤታዋ፣ ፍላጎቱና አቅርቦቱ ልክ ነው የሚባለው ማዳበሪው ቀርቦ ምን ያህል ተጠቃሚው ዘንድ ደረሰ የሚለው ሲመሳከር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የፀጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ለአብነትም የምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢ ማዳበሪያ በአግባቡ መሠራጨቱን ያስታወሱት ሚኒስትር ዴኤታዋ፣ በዚህም የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች፣ የፀጥታ ኃይሎችና የግብርና ቢሮ ባለሙያዎች የከፈሉት መስዋዕትነት ዋጋ ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡
በ2014/15 የምርት ዘመን በአፈር ማዳበሪያ ማጓጓዝ ሒደት የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ባለድርሻ አካላት የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት፣ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር መስከረም 7 ቀን 2014 ዓ.ም. የዕውቅና አሰጣጥ መርሐ ግብር በስካይላይት ሆቴል ማከናወናቸው ይታወሳል፡፡