Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

አንሸነፍም!

ሰላም! ሰላም! እንደምን ሰንብታችኋል ውድ ወገኖቼ፡፡ አዲሱ ዓመትስ እንዴት ይዟችኋል፡፡ አዲስ ዓመት ሲጀመር በተስፋ ስለሆነ ፍቅርን ማስቀደም ጠቃሚ ነው፡፡ ‹‹በአዲስ ዓመት የሰው ፍቅር ይስጥህ…›› ይላሉ አዛውንቱ ባሻዬ ሲመርቁ። እንዴት ያለ ምርቃት መሰላችሁ? ችግሩ የዚህ አገር ሰው ሲሞቱ እንጂ ሲኖሩ፣ ሲያጡ እንጂ ሲያገኙ አያፈቅርም። ‹‹ከበጣም መጥፎ፣ መጥፎ ይሻላል…›› ይባል ነበር አሉ ድሮ፡፡ የድሮ ነገር በትዝታ የሚቆዝሙ ያሉትን ያህል፣ ድሮ ለምን ስሙ ተነሳ ብለው የሚከፋቸው እንዳሉ ብዙ ጊዜ ታዝቤያለሁ፡፡ እርግጥ ነው የበፊትና የአሁኑ ትውልድ በየራሳቸው ምህዋር ውስጥ ሆነው የየራሳቸው ምልከታ ይኖራቸዋል። በዚህ መሀል ግን መረሳት የሌለበት የአሁኑንም ሆነ የበፊቱን የሚያገናኘው አንድ ነገር ነው። እሱም የጋራ አገር ይባላል፡፡ ለዚህም ነው ከጠብ ይልቅ የፍቅር አዝመራ የሚያስፈልገው። ፍቅርና መተሳሰብ እንደ ጥላቻና በቀል በቅስቀሳ መነሳሳት ቢችሉ ኖሮ ዓለም ምን ትመስል ነበር? የዘመናችን ሰዎች ይህንን እየረሱ ይመስላል፡፡ ለጊዜያዊ ፍቅር ብን ብለው የሚያከነፍሱ ትንሽ ነገር ሲፈጠር የጠብ እሳት ተሸክመው ለመዞር ማንም አይቀድማቸውም፡፡ በአዲስ ዓመት ፍቅር ይሰበክ ሲባል እኮ የጠብ ግድግዳ ይፍረስ እየተባለ ነው፡፡ ሰሚ ካለ!    

ታዲያ መወደድና መከበር የታደሉትን ልብ ብለን ካየናቸው ከሕዝብ ልብ ሳይጠፉ ዘወትር እንደታሰቡ ይኖራሉ፡፡ በሕይወትም በሕልፈትም ውስጥ ሆነው ማለት ነው፡፡ አታዩም እንዴ ለምናከብራቸውና ለምንወዳቸው እንዴት እንደምንሆን? በእንዲህ ያለው ሰሞን ደግሞ ጨዋታና አሉባልታው ይገሽብና አንዱን ሰምታችሁ ሳትጨርሱ አንዱ ይጀመርላችኋል። ‹‹እንኳንስ ዘንቦብሽ›› ነዋ የእኛ ነገር። እና አንዱ ምን አለኝ መሰላችሁ? ‹‹በጣም የሚገርመኝ ኢትዮጵያን የምታህል አገር የወላድ መካን ትመስል በሰይጣን መንፈስ ስትታመስ ማየት በጣም ያናድዳል…›› ሲለኝ አባባሉ በጣም ቢያናድደኝም፣ እውነት መሆኑን መዋጥ ስለነበረብኝ በዝምታ ተቀበልኩት፡፡ የአንዳንዱ ሰው አስተያየቱና ፍርዱ ባይጥመን እንኳ፣ እውነታ ውስጡ ካለ በፀጥታ የማዳመጥ ወኔ ቢኖረን እኮ ፍቅር እኛ ዘንድ አትቀዘቅዝም ነበር። ‹‹አይ አንበርብር ከእውነት ጋር እየተላተምን መሰለኝ በጭፍን ድጋፍና በጭፍን ጥላቻ የፅንፈኝነት አዘቅት ውስጥ የምንወድቀው…›› ብሎ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ አዲስ አጀንዳ ሲያቀብለኝ ፈገግ አልኩ። ማንም የፈለገውን የማሰብ፣ የመናገርና የማብራራት መብት እንዳለው እያወቅንም ቢሆን ለማዳመጥ ያለን ፍላጎት በያዝነው አቋም ላይ መመሥረቱ ግርም ይለኛል፡፡ እኔ በበኩሌ የማንንም መብት ለመገደብ ፍላጎቱም ሥልጣኑም የለኝም፡፡ የሚነገረውን ሁሉ በማዳመጤ ግን ተጠቃሚ እሆናለሁ ብዬ አምናለሁ፡፡ ነፃ ውይይት ወይም ክርክር ከሌለ ዕውቀት ከየት ይገኛል? ከየትም!

ውዷ ማንጠግቦሽ እንኳ፣ ‹‹ሰማህ የሰው ልጅ በነፃነት መኖር ሲጀምር ሐሳቡ የበሰለ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ጽንፈኝነትና ጭፍንነት የነፃነት ዕጦት ምልክቶች ናቸው…›› ስትለኝ ነበር የሰነበተችው። የጭፍን ተቃውሞና የጭፍን ፍቅር አካሄድ ምን ያህል እንደከፋ ስረዳ ሥጋት ይነግሥብኛል። ከምሁሩ የባሻዬ ልጅ ጋር እንደገና ስንገናኝ ነገሩን ባነሳበት፣ ‹‹አሁንስ ነፍሴን እየቀፈፋት ያለው ነገር ይኼ የጭፍንነት ችግር ነው። ችግሩ የሚመነጨው ደግሞ ከመታፈን ነው…›› አለኝ፡፡ ስንደማመጥ ከጨዋታችን ቁም ነገር እንደሚወለደው ሁሉ፣ ስንከባበርና ሌላው የሠራውን ሥራ ዋጋ ስንሰጥ የታሪክ ቅብብሎሹ እየሰመረ ይሄዳል። መከባበርና ዕውቅና መሰጣጣት የሚመጣው አንዱ የሌላኛውን ነፃነትና መብት ሲያከብር ነው፡፡ ‹‹ጭፍን ድጋፍና ጭፍን ተቃውሞ ነፃ ያልወጣ አዕምሮ መገለጫ ነው…›› ያለኝ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ነው፡፡ የነፃነትን ዋጋ በገንዘብና በጌጣጌጥ ባንተምነውም ነፃነትን ለማግኘት የሚከፈለው መስዋዕትነት በትዕግሥት የታጀበ መሆን እንዳለበት አይጠፋኝም፡፡ ቆይ ቆይ በዚህ ዘመን እየወጡ ያሉትን የፖለቲከኞችን መጻሕፍት ዓይታችኋል? በደላላ አቅሜ ባለ ማስተርሶችና ባለ ፒኤችዲዎች የጻፉዋቸውን ገዝቼ እያነበብኩ ነበር፡፡ ጎበዝ በእኛ ባልተማርነውና በተማሩት መካከል ያለው ልዩነት የሰማይ ያህል ነው ብዬ ሳስብ ለካ ጎረቤት ኖረናል? ድሮ ድሮ ፍቅር እስከ መቃብርና አልወለድምን በማንበብ ጀምሬ ብዙ ባልገፋም በመጠኑ አንብቤያለሁ፡፡ ለካ አላውቅም ስል ብዙ አውቅ ኖሯል? የባለ ማስተርሶቹና የባለ ፒኤችዲዎቹ መጻሕፍት ከፊደል ግድፈት እስከ ሐሳብ አለመቀናጀት ድረስ ስህተት በስህተት መሆናቸው ቢገርመኝ ምሁሩን የባሻዬን ልጅ፣ ‹‹ምንድነው ችግሩ?›› ስለው፣ ‹‹የፈረደበት የትምህርት ጥራት ችግር ነው…›› ብሎኝ አስደነገጠኝ፡፡ ትምህርት በመካከላችን ያለውን ልዩነት ማሳየት ካልቻለ የት ልንደርስ ይሆን? እንጃ!

ጨዋታ ካነሳን አይቀር ሰሞኑን ስለፌስቡክ የገጠመኝን ባጫውታችሁ አይከፋም። ጃክሮስ አካባቢ ፅድት ያለ ቪላ ቤት ለማከራየት አስቀድሞ ነግሮኝ ለነበረ ደንበኛዬ ደውዬ አሳወቅኩት። ቤቱን መጥቶ እንዲያየው አካባቢውን ነገርኩት። አንዳንዴ በቤት ጉዳይ ላይ እንደኛ ደላላ  ሆናችሁ የቀጠራችሁት ሰው ተጣድፎ በቀጠራችሁት ሰዓት ሲመጣ ስታዩ ቀጠሮ ባለማክበር የምንታማው ሐሜት አይገባችሁም። መዘግየትና መክሸፍ ከኑሯችን እስከ ታሪካችን በየት በኩል እንደሚከሰቱ ማወቅ ያምራችኋል። አምሯችሁ ይቀራል እንጂ የኅብረተሰብ ሥነ ባህሪ ጥናትና ምርምር ድምፁ በማይሰማበት አገር ማን መልስ ይሰጣችኋል? ይኼንንም በትምህርት ጥራት ችግር አሳበን እንለፈው? በነገራችን ላይ ይህ የትምህርት ጥራት ጉዳይ እኔን የሚያሳስበኝ ለአገሬ ካለኝ ፍቅር ነው፡፡ ጥራት ያለው ትምህርት ስላጣን መሰለኝ ሰላምን ገፍተን ግጭት ውስጥ የምንዳክረው፡፡ በፈጠራችሁ ይሁንባችሁና ሰው ካላበደ ወይም በዕውቀት ማነስ ካልሆነ በስተቀር እንዴት ጦር ሰባቂ ይሆናል ብላችሁ ታምናላችሁ፡፡ እኔ በበኩሌ በሚገባ የተማረና የሠለጠነ ሰው ከጦርነት ይልቅ ለሰላም ቅድሚያ እንደሚሰጥ ነው የምገነዘበው፡፡ አዛውንቱ ባሻዬ፣ ‹‹ልጅ አንበርብር እንኳን ጦርነት ለመቀስቀስ ተሳዳቢ ለመሆን የምንዳረገው እኮ ዕውቀት ሳይኖረን ሲቀር ነው፡፡ ሐሳቡን በቅጡ ሰድሮ ማስረዳት የሚያቅተው የሚቀናው ዱላ ወይም ስድብ ነው…›› ሲሉኝ፣ ‹‹ከአህያ ጋር የዋለች ጊደር እርግጫ ነው ተምራ የምትመጣው›› የተባለው ትዝ ብሎኝ ሳቅኩኝ፡፡ አንዳንዴ እንሳቀው እንጂ!

 እና ደንበኛዬ ከተፍ ሲል ፍጥነቱ እያስደነቀኝ ዘመናዊውን ቪላ ቤት አስጎበኘው ጀመር። ግቢውን ከቃኘ በኋላ ቪላው ውስጥ ሊገባ ሲል ስልኩ ጮኸ። ከአሁን አሁን ስልኩን ትቶ ቤቱን መጎብኘቱን ይቀጥላል ብዬ ብጠብቅ ቀጥ ብሎ ቆመ። ‹‹ምን ነው ችግር አለ?›› አልኩት ቢጨንቀኝ። ቀና ብሎ ሲያየኝ አጠገቡ ሰው መኖሩ ትዝ አለው መሰል፣ ‹‹ምን ልበላት?›› አለኝ ዓይን ዓይኔን እያየ። ‹‹ማንን?›› አልኩት ሰውዬው በአንዴ የት ሄዶ ነው እያልኩ (ዕድሜ ለቴክኖሎጂ ሰው ሁሉ ቀስ በቀስ ያለ ቪዛ በኔትወርክ ለጉድ ይበረዋል)፡፡ ለካስ የማያውቃት ኮረዳ በፌስቡክ የጋብቻ ጥያቄ እያቀረበችለት ኖሯል። የአንዳንዱን ሰው ውሳኔና ድፍረት ስታዩ ትበረግጋላችሁ። ለነገሩ ከመደበኛው መንግሥት የግለሰብ ‹‹መንግሥታት›› ስለበዙ ምንም የሚገርም ነገር የለውም። እናም የጋብቻ ጥያቄ በፌስቡክ ያውም ላይቭ (በቻት) መሆኑን ስሰማላችሁ ጮክ ብዬ፣ ‹‹ጉድ በል የአገሬ ሰው…›› አልኩ የዘመኑ አያያዝ እጅግ አስፈርቶኝ። ‹‹የአማርኛውን ነው የእንግሊዝኛውን ጉድ ነው በል የምትለኝ?›› አለኝ ደንበኛዬ መልሱን የነገርኩት መስሎት። ስንግባባ ሁለታችንም የሳቅ አምሮታችንን ተወጣነው። ሌላ ሌላውን ነው እንጂ መወጣት ያቃተን፡፡ ሰውየው ለካ ከጋብቻ ጥያቄ አቅራቢዋ የበለጠ ጮሌ ኖሮ በሽሙጥ መልክ አፉን እያጣመመ፣ ‹‹ይኼኔ ቤሳ ቤስቲን ባይኖረኝ ዞር ብላም አታየኝም ነበር…›› ብሎ ስልኩን ወደ ኪሱ ሲከተው፣ እኔ ደግሞ ያለፈውን ዘመን የጋብቻ ጥያቄ ወግና ሥርዓት እያስታወስኩ በሐሳብ ጭልጥ ብዬ ነበር፡፡ ጉድ እኮ ነው! 

‹‹በዚህ ዓይነትማ ጥሪውንና ግብዣውን ጭምር ‘ቻት’ ተክቶት ማረፉ ነው…›› ብዬ ለአንድ ደላላ ወዳጄ ስለደንበኛዬ ገጠመኝ ባጫውተው፣ ‹‹ማን ያውቃል በዚህ አስቂኝ ዘመን ወግና ሥርዓቱ ከመንገድ ሊቀር ተቃርቦ ይሆናል…›› አለኝ። ትንሽ ቆይቶ በምርጫ ጊዜም ለቆጠራና ለትዝብት አሻፈረኝ ባዩ ሲያይል ድምፅ በኮሮጆ መስጠት ተረስቶ ‘ኦንላይን’ በ‘ላይክ’ የሚሆንበት ዘመን ይመጣም ይሆናል…›› እያለኝ ተሳሳቅን፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ደግሞ በዚህ ዘመን በቴክኖሎጂ መሣሪያዎች ጉድ ሲጎለጎል ነው የምናየው። ከዴሞክራሲ ተቃርነው በዴሞክራሲ ጥም ተቃጥለው አልበርድ ያሉ አብዮቶችን ዜና ሆኗል የምናዳምጠው። በአንድ በኩል መንግሥታት ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚታገሉና ዋስ ጠበቃ እንደሚሆኑ ሲደሰኩሩ፣ በጎን ዜጎቻቸውን ሲሰልሉ፣ ሲያፍኑና ሲያስሩ የድኅረ ኢንተርኔቱን ትውልድ እንዳልቻሉት ያሳዩናል። የዓለም ፖለቲካና አካሄድ አልገባ ሲለኝ ደላላ እንጂ ፖለቲከኛ አለመሆኔን ለራሴ አስረድቼ ወደ ኑሮዬ እመለሳለሁ። ሥጋትና ተስፋ የነገው ኑሮዬና ቤቴ ላይ ዕጣ ሲጣጣሉ ሳይ ደግሞ መልሼ የጣልኩትን አነሳ እጀምራለሁ። ‘ስትሄድ ስከተላት’ ማለት ይኼ አይደል ታዲያ፡፡ አወይ ፖለቲካ!

እስኪ ደግሞ የሳምንት ሰው ይበለን። ከመሰነባበታችን በፊት ግን አንድ የኮንስትራክሽን አስመጪና ሻጭ የሆነ ደንበኛዬ ጠርቶኝ ሄጄ ያወጋነውን ላውጋችሁ። ከመድረሴ፣ ‹‹እንኳን ለአዲሱ ዓመት አደረሰህ፣ እንዲሁም ደስ አለህ አንበርብር…›› አለኝ። ‹‹በአምላክህ ምን ተገኘ?›› ስለው፣ ‹‹የሁለት አኃዝ የኢኮኖሚ ዕድገታችን በአዲሱ ዓመት ይቀጥላል…›› አለኝ እየሳቀ። ‹‹የጠራኸኝ ለሥራ መስሎኝ?›› አልኩት ኮስተር ብዬ። በእውነት ሰው ታጥቆ ይኼን ያህል ነቆራ ላይ እንደ ዘመተው ሥራ ላይ ቢዘምት ምን ነበረበት? ‹‹ለሥራው ትደርስበታለህ ሦስት አዳዲስ ማሽኖች አስገብቻለሁ መተንፈሻ ነው የምታጣው…›› ካለኝ በኋላ፣ ‹‹ስለሁለት አኃዝ ዕድገታችን ስናገር ለምን ተበሳጨህ?›› ብሎ ጠየቀኝ። ‹‹ወሬህ ሳይሆን አነጋገርህ ደስ ስላላለኝ ነው…›› አልኩት ፊት ለፊት። ‹‹እኔም የማየውን ነው የነገርኩህ። የነገሮች ማነፃፀሪያና መለኪያው የበጋው ስንዴ ልማት እንደሆነ ተደርጎ ነው የሚወራው። ይብላኝ ለእኛ ለሰነፎቹ እንጂ ልማቱ በዚህ ከቀጠለ በአዲሱ ዓመት ስንዴ ኤክስፖርት በማድረግ ታሪክ እንሠራለን። አንዳች ነገር ባለበት በማይቀጥልበት ዓለም ቶሎ ተሽቀዳድመን የልማቱን ልጓም መጨበጥ ከቻልን፣ የአገራችንን ሰላም በአስተማማኝ ካስጠበቅንና እርስ በርስ ከተፋቀርንና ከተሳሰብን ድህነትን ደህና ሰንብት ማለታችን አይቀርም….›› አለኝና አዳዲስ ያስቀመጣቸውን ማሽኖች ፎቶ ያሳየኝ ጀመረ። ዓይኔ ፎቶዎቹ ላይ ልቤ አባባሉ ላይ ቀረ። ዓይንና ልብ የተራራቁበት ጊዜ ስንቱን ያሳየን ይሆን? በጣም ብዙ!

በአዲሱ ዓመት የመጀመሪያ ሳምንት ላይ ሆነን መልካም ነገሮችን ስንመኝ፣ በዙሪያችን ያሉ አሳዛኝ ነገሮችንም ለመቀየር መነጋገር ይኖርብናል ባይ ነኝ፡፡ ለልማት በጋራ ተነስተን ድህነትን ታሪክ ማድረግ የምንችለው በወሬ ወይም በመፈክር እንዳልሆነ ብዙዎቻችን እንገነዘባለን፡፡ ለምሳሌ ወንጀል በጣም እየበዛ ነው፡፡ በመሣሪያ የተደገፈ ዝርፊያ እየተካሄደ የብዙዎች ሕይወት ለአደጋ ተጋልጧል፡፡ የመኖሪያና የንግድ መደብሮች ዝርፊያ፣ የመኪና ዝርፊያ፣ ወደ ባንክ የሚገባ ገንዘብ በመሣሪያ አስገድዶ መዝረፍና ግለሰቦችን በጉልበት ወይም በማጭበርበር መዝረፍ የተለመደ የዕለት ተዕለት ድርጊት መሆኑን እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት እመሰክራለሁ፡፡ ሕግ ባለበት አገር ከፖሊስ አቅም በላይ የሚመስል ዝርፊያ በጠራራ ፀሐይ ሲከናወን ያስፈራል፡፡ አንዱ በቀደም ዕለት፣ ‹‹አንበርብር የፖሊስ የደንብ ልብስ ለብሰው የሚዘርፉ በርክተዋል…›› ሲለኝ፣ ‹‹ፖሊሶቹ ተኝተው ነው ወይስ እየተባበሩ ነው ይህ አስነዋሪ ድርጊት የሚፈጸመው…›› ነበር ያልኩት፡፡ ወገኖቼ ብዙ ብናገር ሆድ ባዶ ይቀራል ብዬ እንጂ፣ ከአሮጌው ዓመት መተላለፍ የሌለባቸው ብዙ ነገሮች እንዳሉ እናንተም ታውቃላችሁ፡፡ ‹‹ማወቁንስ እናውቃለን ብንናገር እናልቃለን›› የሚለውን የፈሪዎች አባባል ለመድገም ሳይሆን፣ ሁሉም የየራሱን ድርሻ በማዋጣት ወንጀልን በጋራ እንከላከል ለማለት ነው፡፡ ‹‹ፍቅር ሲኖረን እንኳንስ ሌባ ማንም አያሸንፈንም…›› የሚሉት አዛውንቱ ባሻዬ ናቸው፡፡ እውነት ነው በማንም አንሸነፍ! መልካም ሰንበት! 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት