አዲሱ ዓመት 2015 ዓ.ም. ከባተ፣ አንድ ሳምንትን ተሻግሯል፡፡ በአብዛኛው የአገሪቱ አካባቢ የክረምቱ ወቅት አብቅቶ የአበባና የነፋስ ወቅት የሆነው መፀው ሊገባም ሁለት ሳምንታትን ይጠብቃል፡፡
ከክረምት ቀጥሎ የሚመጣው የአበባው ወቅት ‹‹መፀው›› በኦሮሞ ‹‹ብራ››፣ በአማራ ‹‹ጥቢ›› በትግራይ ‹‹ቀውዒ›› በከምባታ ‹‹በሪ ወሎተ›› (ማሬ)፣ በጠምባሮ ‹‹በሪ ወሊሱ››፣ በሐላባ ‹‹ማላታ››፣ በዳውሮ ‹‹አይሌ››፣ በሐዲያ ‹‹ፌቴ›› (ብራ)፣ በባስኬቶ ‹‹ጉፃፃ›› (የአበባ ወራት)፣ በቤንች ‹‹ቤያርግ›› (አዲስ ዓመት የአደይ አበባ በብዛት የሚበቅልበት)፣ በየም ‹‹ማር››፣ በጉራጌ ‹‹ዊጠገና››፣ በቦሮ ሺናሻ ‹‹ጋሪ ዎሮ›› ወይም ‹‹ጋሮ››፣ በሌሎች ብሔረሰቦችም የተለያየ ስም እንዳላቸው ዘመን ጠቀስ ጥናቶች ይገልጻሉ፡፡
ከነዚህ ከተለያዩ ብሔረሰቦች ባህላዊ የዘመን አቆጣጠሮች መካከል በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኘው ቦሮ ሺናሻ የአዲስ ዓመት መቀበያ ክብረ በዓልን ‹‹ጋሪ- ዎሮ›› ብሎ ይጠራዋል፡፡ በአጭሩም ‹‹ጋሮ›› በማለትም ይጠራል፡፡

‹‹የጋሪ-ዎሮ ወይም ጋሮ በዓል አከባበር በቦሮ ሺናሻ ብሔረሰብ›› በሚል ርዕስ የጻፉት የባህል ባለሙያው አቶ አበበ ጥላሁን (የሀብከ) እንደገለጹት፣ የ‹‹ጋሪ-ዎሮ›› ወይም ‹‹የጋሮ›› በዓል የቦሮ-ሺናሻ ማኅበረሰብ ከሚያከብራቸው ታላላቅ በዓላት ውስጥ አንዱና የዘመን መለወጫ በዓል በመሆኑ በድምቀት ይከበራል፡፡ በዓሉ የሚከበረው በመስከረም ምድሩ በአደይ አበባ ሸብርቆና ክረምቱ አልቆ መፀው ወቅት ሲገባ ነው። የማክበሪያው ቦታም በየቤቱና በብሔረሰቡ አባቶች በብሔረሰቡ ቋንቋ ‹‹ጋ-ሪ ጀባ›› በሚባል ቦታ ሲሆን፣ በዓሉ በዘፈቀደ የሚከበርበት ሳይሆን በአባቶች ተመርቆና በባህሉ መሠረት ተባርኮ ነው፡፡
ለበዓሉ ዝግጅት የሚደረገው ከነሐሴ ጀምሮ ሲሆን ይህን በተመለከተ በበዓሉ ይዘት ያተኮሩ ሦስት ዓይነት ዘፈኖች ይዘፈናሉ። እነዚህም በዘፈን ወቅቶች የተከፈሉ ናቸው፡፡
ከሐምሌ ወር መጨረሻ አካባቢ ጀምሮ እስከ በዓሉ ዋዜማ (መስከረም አጋማሽ) አካባቢ፣ እንዲሁም እስከ በዓሉ ዕለትና ከበዓሉ በኋላ እስከ ሁለት ሳምንት ድረስ ከወቅቶቹ ጋር የሚሄድ ባህላዊ ጭፈራ ዓይነተኛ መለያው ነው፡፡ በዘመን መለወጫ በዓሉ ዕለት አዳዲስ (እሸት) ለምግብነት የደረሱ የእህል ዓይነቶች በሙሉ በዚሁ በአንድነት በሚከበረው ቦታ ቀርበው በአባቶች ተመርቆ እንዲቀመሱ ተደርጎና ምርቃቶች ተካሂደው ሁሉም የብሔረሰቡ አባላት ያለምንም ልዩነት በድምቀት ያከብሩታል፡፡ በዚሁ ባህላዊ ጭፈራ ወቅት የወጣቶቹ ጭፈራ የሚያጠነጥነው ‹‹አዲስ ዘመን መጣልን፣ ጨለማን ጥለን አለፍን›› በሚሉትና እንዲሁም አዲስ ዓመት ደረሰልን፣ ችግራችን ተወገደ፣ ዓይናችን በራ፣ አዲስ ዘመን ተቀበልን በማለት ነው።
ሌላው የበዓሉ አከባበር አካል የሆነው የብሔረሰቡ አባላት በየቤታቸው እንደየ አቅማቸው አስፈላጊውን የምግብና መጠጥ ዝግጅት በማድረግ በዓሉን በደማቅ ሁኔታ የሚያከብሩበት ሒደት መሆኑን አቶ አበበ ያብራራሉ፡፡ የ‹‹ጋ-ሮ›› ሥነ ሥርዓት ከመፈጸሙ በፊት መስከረም 16 ምሽት ለደመራ የሚሆን ከ4 እስከ 12 እርጥብ እንጨት ጐረምሶች ‹‹እንኳን ለአዲስ ዓመት አደረሰን›› በማለት በየቤታቸው ያስገባሉ፡፡ ይህም በብሔረሰቡ ቋንቋ ‹‹ጋ-ር ጊንድ ጌዳ›› ይባላል፡፡ ከዚህም ጎን ለጎን በአንድ ላይ ተሰብስቦ በሚከበረው ቦታ ላይ በታዋቂ ሽማግሌዎች ምረቃ ደመራው ይተከላል፡፡
በመቀጠልም በየቤቱ ቤተ ዘመዶች ከታላቃቸው ቤት በመጀመር ‹‹የአባቴ አምላክ ካለፈው ዓመት ለዘንድሮ አድርሷልና ለዘንድሮ ያደረሰን ደግሞ ለአዲሱ ዓመት እንኳን በሰላም አደረሰን›› በማለት የሙታን አያታቸውንና አባታቸውን አምላክ በመጥራት በቤቱ ውስጥ ለዚህ የመለማመኛና የምርቃት ሥርዓት የተዘጋጀውን ‹‹ጭምቦ›› የሚባል የምግብ ዓይነት በትንሹ በመቁረስ ወደ መሬት በመጣልና ቦርዴውንም በትንሹ መሬት ላይ በመድፋት ይለማመናሉ፡፡ ይህም በብሔረሰቡ ቋንቋ ‹‹ሚሽ ቂራ›› ይባላል፡፡ በመቀጠል መላ ቤተሰብ በሚገባ የተዘጋጀውን ጭምቦ ተሰባስበው በአንድ መሶብ ዙሪያ ይመገባሉ፡፡
በዚህ ወቅት የተጣላ የቤተሰብ አባል ካለ ተፈልጎ እርቅ እንዲፈጸም ተደርጎ በዓሉን አብሮ ያከብራል፡፡ በእርቅ ወቅትም ጥፋተኛ ተለይቶ ተበዳዩን እንዲክስና ተበዳዩም ይቅር እንዲልለት ይደረጋል፡፡
በነጋታው (በመስከረም 17) ንጋት ከዘጠኝ እስከ ዐሥር ሰዓት ገደማ የተደመረው ደመራ በሀገር ሽማግሌዎች ምረቃ ይለኮሳል፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ዘመድ አዝማድ ሲገናኝና ወደ አንዱ ቤት ሲገባ እንደየአካባቢው ‹‹ወርገወ›› ወይም ‹‹ዎሮ-ዎሮ›› ሲል መላሽ/ባለቤቶች ደግሞ ‹‹ዎሮ-ቦሬ›› ይላሉ፡፡ ትርጉሙም ‹‹እንቁጣጣሽ እንኳን ደህና መጣሽ›› እንደ ማለት ያህል ነው፡፡
ደመራው ከተለኮሰበት ቦታ ለተከታታይ ቀናት ይጨፈራል፡፡ በመስከረም 18 ማታ 10፡00 ሰዓት ገደማ የሀገር ሽማግሌዎቹ በመሰብሰብ ‹‹ለአዲሱ ዓመት ያደረሰን አምላክ ለመጪው ዓመትም በሰላም ያድርሰን፣ ዓመቱ የሰላም፣ የደስታና የፍሥሐ ዘመን ይሁንልን፣ ምርቱ ረድዔትና በረከት ይኑረው፣ ሀብትና ወረት ይለምልም ወዘተ.›› በማለት ቀደም ሲል በዋዜማው በምረቃ የከፈተው በዓል በምረቃ ይጠናቀቃል፡፡
እንደ የባህል ባለሙያው አቶ አበበ አገላለጽ፣ በብሔረሰቡ ሁለት ዓይነት የበዓሉ አከባበር ያለው ሲሆን የመጀመሪያው መላ ማኅበረሰቡ፣ በአንድ ላይ በመሰባሰብ በተመረጠው የ‹‹ጋ-ሮ›› ቦታ የሚከበር አከባበር ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በዋዜማው የተጀመረው መገናኘት ከበዓሉ በኋላም እስከ ሁለት ሳምንት በሚዘልቅ ጊዜ የብሔረሰቡ አባላት ዘመድ አዝማዳቸውን በመጥራት በየቤታቸው በመሆን በድግስ የሚያከብሩት ክብረ በዓል ነው፡፡
በዚህ ክብረ በዓል ባህላቸውንና ወጋቸውን ለትውልድ ያስተላልፋሉ፣ የብሔረሰቡ አባቶችና እናቶች፣ ወጣቶችና ሕፃናት በዓሉን በጋራ በማክበር የአብሮነት ባህላቸውን ያሳድጋሉ፡፡ የተጣላን በማስታረቅና በማግባባት ማኅበራዊ ግንኙነታቸውን ያጠናክራሉ፡፡ በተለይም ወጣቶች ማኅበራዊ ጉዳዮቻቸውን ለምሳሌ ያህል የትዳር ጓደኞቻቸውንና ፍቅረኞቻቸውን ለመምረጥ ዕድል የሚያገኙበት ነው፡፡ አጥኚው እንደገለጹት፣ የዘመን መለወጫ በዓሉ የፍስሐ ቀን ሆኖ የሚከበረው ለሰው ልጅ ብቻ አይደለም፡፡ በዕለቱ ላሞች አይታለቡም፣ ጥጆች እንዲጠቡ ይደረጋል! አሞሌ ጨው ይሰጣቸዋል!